ዘኍልቍ 11:16-33
ዘኍልቍ 11:16-33 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ከእስራኤል ሽማግሌዎች፥ ለሕዝቡ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ይሆኑ ዘንድ የምታውቃቸውን፥ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፤ ወደ ምስክሩም ድንኳን አምጣቸው፤ በዚያም ከአንተ ጋር አቁማቸው። እኔም እወርዳለሁ፤ በዚያም አነጋግርሃለሁ፤ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ፤ አንተም ብቻ እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ። ሕዝቡንም በላቸው፦ ሥጋ ማን ያበላናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ በእግዚአብሔር ፊት አልቅሳችኋልና ለነገ ተቀደሱ፤ ሥጋንም ትበላላችሁ፤ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፤ ትበሉማላችሁ። አንድ ቀን፥ ወይም ሁለት ቀን፥ ወይም አምስት ቀን፥ ወይም ዐሥር ቀን ወይም ሃያ ቀን አትበሉም፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም፦ ለምን ከግብፅ አወጣኸን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ መርዝም እስኪሆንባችሁ ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ።” ሙሴም፥ “እኔ በመካከላቸው ያለሁ ሕዝብ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም፦ ሥጋን እሰጣቸዋለሁ፥ ወር ሙሉም ይበሉታል አልህ። የበሬና የበግ መንጋ ቢታረድ፥ የባሕር ዓሣ ሁሉ ቢሰበሰብ ይበቃቸዋልን?” አለ። እግዚአሔርም ሙሴን፥ “በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አትችልምን? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይም አይፈጸም እንደ ሆነ እነሆ፥ አንተ ታያለህ” አለው። ሙሴም ወጣ፤ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። እግዚአብሔርም በደመናው ወረደ፤ ተናገረውም፤ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተጨመረላቸውም። ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፤ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ዐረፈባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ፤ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ጐልማሳ ሰው እየሮጠ መጥቶ፥ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው። የሙሴ ምርጥ ባለሟል የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፥ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ ፥ ከልክላቸው” አለው። ሙሴም “የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያሳድር አንተ ስለ እኔ ትቀናለህን?” አለው። ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ። ነፋስም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ ከባሕርም ድርጭቶችን አወጣ፤ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚህ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚያ በሰፈሩ ላይ በተናቸው፤ በዚያም በሰፈሩ ዙሪያ ከፍታው ከምድር ወደ ላይ ሁለት ክንድ ነበረ። በዚያም ቀን ሁሉ፥ በሌሊትም ሁሉ፥ በነጋውም ሁሉ ሕዝቡ ተነሥተው ድርጭትን ሰበሰቡ፤ ከሁሉ ጥቂት የሰበሰበ ዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ ያህል ሰበሰበ፤ በሰፈሩም ዙሪያ ሁሉ አስጥተው አደረቁት። ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳያኝኩትም፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን እጅግ ታላቅ በሆነ መቅሠፍት አጠፋቸው።
ዘኍልቍ 11:16-33 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በሕዝቡ መካከል በመሪነትና በእልቅና ብቃት አላቸው የምትላቸውን ሰባ የእስራኤል ሽማግሌዎች አምጣልኝ፤ ካንተም ጋራ ይቆሙ ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን እንዲመጡ አድርግ። ወደዚያም ወርጄ አነጋግርሃለሁ፤ ባንተ ላይ ካለው መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ የሕዝቡንም ሸክም ብቻህን እንዳትሸከም እነርሱ ያግዙሃል። “ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ነገ ሥጋ ትበላላችሁና ራሳችሁን በመቀደስ ተዘጋጁ። “በግብጽ ተመችቶን ነበር፤ አሁን ግን ሥጋ ማን ይሰጠናል!” ብላችሁ ያለቀሳችሁትን እግዚአብሔር ሰምቷል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እናንተም ትበላላችሁ። የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ወይም ለዐምስት፣ ለዐሥር ወይም ለሃያ ቀን አይደለም፤ ነገር ግን በአፍንጫችሁ እስኪወጣና እስኪያንገፈግፋችሁ ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ፤ በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችሁ በፊቱ፣ “ለምን ከግብጽ ወጣን?” ብላችሁ አልቅሳችኋልና።’ ” ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እነሆ እኔ በስድስት መቶ ሺሕ እግረኛ መካከል እገኛለሁ፤ አንተ ደግሞ ‘ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ’ ብለሃል፤ ታዲያ ስንት የበግ፣ የፍየልና የከብት መንጋ ቢታረድላቸው ይበቃ ይሆን? በባሕር ያለው ዓሣ ሁሉ ቢያዝ ሊዳረሳቸው ይችላልን?” እግዚአብሔርም ለሙሴ፣ “በውኑ የእግዚአብሔር ክንድ ይህን ያህል ዐጭር ነውን? የነገርሁህ ቃል እውነት መሆን አለመሆኑን አሁኑኑ ታየዋለህ” ሲል መለሰለት። ሙሴም ወጣና እግዚአብሔር ያለውን ለሕዝቡ ነገራቸው፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎች ሰባውን ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ እንዲቆሙ አደረጋቸው። ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ወርዶ ተናገረው፤ በሙሴ ላይ ከነበረውም መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈሱ ባደረባቸውም ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልደገሙትም። ኤልዳድና ሞዳድ የተባሉ ሁለት ሰዎች ግን ሰፈር ውስጥ ቀርተው ነበር፤ እነርሱም ከሽማግሌዎቹ ጋራ ተቈጥረው ሳለ ወደ ድንኳኑ አልሄዱም ነበር፤ ሆኖም መንፈስ በእነርሱም ላይ ስላደረባቸው ሰፈር ውስጥ እያሉ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ወጣትም ሮጦ በመሄድ፣ “ኤልዳድና ሞዳድ ሰፈር ውስጥ ትንቢት ይናገራሉ” ብሎ ለሙሴ ነገረው። ከወጣትነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱም ተነሥቶ፣ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ፤ ከልክላቸው እንጂ” ሲል ተናገረ። ሙሴ ግን መልሶ፣ “ስለ እኔ ቀንተህ ነውን? የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፣ እግዚአብሔርም መንፈሱን ቢያሳድርባቸው ምንኛ ደስ ባለኝ!” አለ፤ ከዚያም ሙሴና የእስራኤል ሽማግሌዎች ወደ ሰፈር ተመለሱ። በዚህ ጊዜ ነፋስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ ድርጭቶችን ከባሕር ወደ ሰፈር አመጣ፤ በየአቅጣጫውም ከፍታው ሁለት ክንድ፣ ርቀቱም የአንድ ቀን መንገድ ያህል እስኪሆን ድረስ በሰፈሩ ዙሪያ ከመራቸው። በዚያ ዕለት ቀንና ሌሊቱን በሙሉ፣ በማግስቱም ሙሉውን ቀን እንደዚሁ ሕዝቡ ወጥቶ ድርጭቶች ሰበሰበ፤ ከዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ ያነሰ የሰበሰበ ማንም አልነበረም፤ የሰበሰቡትንም በሰፈሩ ዙሪያ ሁሉ አሰጡት። ነገር ግን ሥጋው ገና በጥርስና በጥርሳቸው መካከል ሳለ አላምጠው ሳይውጡት የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት ክፉኛ መታ።
ዘኍልቍ 11:16-33 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ከእስራኤል ሽማግሌዎች፥ በሕዝቡ ላይ ሽማግሌዎችና አለቆች ይሆኑ ዘንድ የምታውቃቸውን፥ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፥ ወደ መገናኛውም ድንኳን አምጣቸው፥ በዚያም ከአንተ ጋር አቁማቸው። እኔም እወርዳለሁ፥ በዚያም እነጋገርሃልሁ፥ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አደርገዋለሁ፤ አንተም ብቻ እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ። ሕዝቡንም በላቸው፦ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብፅ ደኅና ነበረልን እያላችሁ ያለቀሳችሁት ወደ እግዚአብሔር ጆሮ ደርሶአልና ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ፤ እግዚአብሔርም ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበሉማላችሁ። አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም አሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን አትበሉም፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን እግዚአብሔርን ንቃችኋልና፥ በፊቱም፦ ለምን ከግብፅ ወጣን? ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ እስኪሰለቻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ። ሙሴም፦ እኔ በመካከላቸው ያለሁ ሕዝብ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም፦ ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ አልህ። እነርሱን የሚያጠግብ የበሬና የበግ መንጋ ይታረድን? ወይስ የባሕርን ዓሣ ሁሉ ያጠግባቸው ዘንድ ይሰበሰብላቸዋልን? አለ። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በውኑ የእግዚአብሔር እጅ አጭር ሆነ? አሁን ቃሌ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደ ሆነ አንተ ታያለህ አለው። ሙሴም ወጣ የእግዚአብሔርንም ቃሎች ለሕዝቡ ነገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። እግዚአብሔር በደመናው ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አደረገ፤ መንፈሱም በላያቸው ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋል ግን አልተናገሩም። ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈር ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ የሁለተኛውም ሞዳድ ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን አልወጡም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ጐበዝ ሰው እየሮጠ መጥቶ፦ ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈር ትንቢት ይናገራሉ ብሎ ለሙሴ ነገረው። ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፦ ጌታዬ ሙሴ ሆይ፥ ከልክላቸው አለው። ሙሴም፦ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያወርድ፤ አንተ ስለእኔ ትቀናለህን? አለው። ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ። ነፋስም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፥ ከባሕርም ድርጭቶችን አመጣ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚህ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚያ በሰፈሩ ላይ በተናቸው፤ በዚያም በሰፈሩ ዙሪያ ከፍታው ከምድር ወደ ላይ ሁለት ክንድ ነበረ። በዚያም ቀን ሁሉ በሌሊትም ሁሉ በነጋውም ሁሉ ሕዝቡ ተነሥተው ድርጭትን ሰበሰቡ፤ ከሁሉ ጥቂት የሰበሰበ አሥር የቆሮስ መስፈሪያ የሚህል ሰበሰበ፤ በሰፈሩም ዙሪያ ሁሉ አሰጡት። ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳያኝኩትም፥ የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት እጅግ መታ።
ዘኍልቍ 11:16-33 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለሕዝብ አመራር በመስጠት የታወቁ ሰባ ሽማግሌዎችን ምረጥ፤ እነርሱንም ሰብስበህ ወደ መገናኛው ድንኳን አምጣቸውና በአጠገብህ ይቁሙ፤ እኔም ወደዚያ ወርጄ ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፤ ለአንተም ከሰጠሁህ መንፈስ ከፍዬ ለእነርሱ እሰጣቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ በእነዚህ ሕዝብ ላይ ያለህን ኀላፊነት በመሸከም ይረዱሃል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ይህን ሁሉ ኀላፊነት ብቻህን አትሸከምም። አሁንም ለሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ለነገ ራሳችሁን አንጹ፤ የምትበሉትም ሥጋ ይኖራችኋል፤ የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል ብላችሁ ማልቀሳችሁንና የግብጽ ምድር ይሻለን ነበር ማለታችሁን እግዚአብሔር ሰምቶአል፤ እነሆ፥ አሁን እግዚአብሔር ሥጋ ይሰጣችኋል፤ እርሱንም ትበላላችሁ። የምትበሉትም ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ለአምስት፥ ለዐሥር ወይም ለኻያ ቀን ብቻ አይደለም፤ እስኪያንገፈግፋችሁና በአፍንጫችሁ እስኪወጣ ድረስ አንድ ወር ሙሉ ትመገቡታላችሁ፤ ይህም የሚሆነው እዚህ በመካከላችሁ ያለውን ጌታ ስለ ናቃችሁና፦ ከግብጽ ባልወጣን ኖሮ መልካም ነበር በማለት ስላለቀሳችሁ ነው።’ ” ሙሴም ለእግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ እኔ ስድስት መቶ ሺህ ሕዝብ በመምራት ላይ እገኛለሁ፤ ለአንድ ወር የሚበቃ ሥጋ ልትሰጣቸው ቃል ገብተሃል፤ ታዲያ ምን ያኽል የከብትና የበግ መንጋ ቢታረድ እነርሱን ሊያጠግብ ይችላል? በባሕር ውስጥ ያለው ዓሣ ሁሉ ቢሰበሰብ ለእነርሱ በቂ ሊሆን ይችላልን?” እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የእኔ የእግዚአብሔር ኀይል ውሱን ነውን? ቃሌ በእናንተ ዘንድ የሚፈጸም ወይም የማይፈጸም መሆኑን አሁን ታያለህ!” ስለዚህ ሙሴ ወጥቶ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ከሕዝቡ መሪዎች ሰባውን በአንድነት ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ተናገረው፤ ለሙሴ ከሰጠው መንፈስ ከፊሉን ወስዶ በሰባዎቹ መሪዎች ላይ አሳደረባቸው፤ መንፈስ በወረደባቸውም ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ፤ ይህን ያደረጉት ግን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነበር። ከተመዘገቡት ከሰባው መሪዎች መካከል ሁለቱ ኤልዳድና ሜዳድ የተባሉት ወደ ድንኳኑ ሳይሄዱ በሰፈር ቈይተው ነበር፤ እዚያው በሰፈር እንዳሉ መንፈስ ወረደባቸውና እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ተናገሩ። አንድ ወጣት ወደ ሙሴ ሲሮጥ ሄዶ “ኤልዳድና ሜዳድ በሰፈር ውስጥ ትንቢት እየተናገሩ ናቸው” ሲል ነገረው። ከጐልማሳነቱ ጀምሮ የሙሴ ረዳት የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፥ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ! ከልክላቸው!” አለው። ሙሴም “አንተ ስለ እኔ ትቈረቈራለህን? እኔስ እግዚአብሔር በሕዝቡ ሁሉ ላይ መንፈሱን ቢያወርድና ሁሉም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደ ነቢያት ትንቢት ቢናገሩ ደስታዬ ነው!” አለው። ሙሴና ሰባዎቹ የእስራኤል መሪዎችም ወደ ሰፈር ተመለሱ። በድንገትም እግዚአብሔር ድርጭቶችን ከባሕር እየነዳ የሚያመጣ ነፋስ ላከ፤ ድርጭቶችም ከምድር አንድ ሜትር ያኽል ከፍ ብለው እየበረሩ መጡ፤ በሰፈሩና በሰፈሩ ዙሪያ የተከማቹበት ስፍራ የአንድ ቀን መንገድ ያኽል ነው፤ ስለዚህ በዚያን ቀንና ሌሊት፥ እንዲሁም በማግስቱ ሕዝቡ ድርጭት እያሳደዱ በመያዝ ደከሙ፤ ከዐሥር ኪሎ ግራም ያነሰ የሰበሰበ አልነበረም፤ እንዲደርቁም በሰፈር ዙሪያ አሰጡአቸው። የሚበሉት ሥጋ ገና በብዛት ሳለ፥ እግዚአብሔር በሕዝቡ እጅግ ተቈጣ፤ ብርቱ መቅሠፍትም በሕዝቡ መካከል አመጣ፤
ዘኍልቍ 11:16-33 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በሕዝቡ ላይ ሽማግሌዎችና አለቆች እንደ ሆኑ የምታውቃቸውን የእስራኤል ሽማግሌዎች የሆኑ ሰባ ሰዎች ሰብስብልኝ፤ እነርሱንም ወደ መገናኛው ድንኳን አምጣቸው፥ በዚያም ከአንተ ጋር በየቦታቸው ይቁሙ። እኔም እወርዳለሁ፥ በዚያም ከአንተ ጋር እነጋገራለሁ፥ በአንተ ካለውም መንፈስ ወስጄ በእነርሱ ላይ አኖረዋለሁ፤ አንተም ብቻህን እንዳትሸከም የሕዝቡን ሸክም ከአንተ ጋር ይሸከማሉ። ሕዝቡንም እንዲህ በላቸው፦ ለነገ ተቀደሱ፥ ሥጋንም ትበላላችሁ ምክንያቱም እንዲህ እያላችሁ ያለቀሳችሁት ለቅሶ ወደ ጌታ ጆሮ ደርሶአልና፦ ‘የምንበላውን ሥጋ ማን ይሰጠናል? በግብጽ ሳለን በዚያ ደኅና ነበርን፤’ ስለዚህ ጌታ ሥጋን ይሰጣችኋል፥ ትበላላችሁም። አንድ ቀን ወይም ሁለት ቀን ወይም አምስት ቀን ወይም ዐሥር ቀን ወይም ሀያ ቀን ብቻ የምትበሉት አይደለም፤ ነገር ግን በመካከላችሁ ያለውን ጌታን ትታችሁታልና፥ በፊቱም፦ ‘ለምን ከዚያ ከግብጽ ወጣን?’ ብላችሁ አልቅሳችኋልና በአፍንጫችሁ እስኪ ወጣ እስኪያቅለሸልሻችሁም ድረስ ወር ሙሉ ትበሉታላችሁ።” ነገር ግን ሙሴ እንዲህ አለ፦ “እኔ በመካከላቸው ሆኜ በእኔ ዘንድ ያሉት ሰዎች ሲቈጠሩ ስድስት መቶ ሺህ እግረኛ ናቸው፤ አንተም፦ ‘ወር ሙሉ የሚበሉትን ሥጋ እኔ እሰጣቸዋለሁ’ አልህ። እነርሱን የሚያጠግብ የበሬና የበግ መንጋ ይታረድላቸውን? ወይስ የባሕርን ዓሣ ሁሉ እንዲያጠግባቸው ይሰበሰብላቸውን?” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በውኑ ጌታ ለዚህ እጅ አጥሮት ነውን? አሁን ቃሌ ለአንተ ይፈጸም ወይስ አይፈጸም እንደሆነ አንተ ታያለህ።” ሙሴም ወጣ የጌታንም ቃላት ለሕዝቡ ተናገረ፤ ከሕዝቡ ሽማግሌዎችም ሰባውን ሰዎች ሰብስቦ በድንኳኑ ዙሪያ አቆማቸው። ጌታም በደመናው ውስጥ ሆኖ ወረደ፥ ተናገረውም፥ በእርሱም ላይ ከነበረው መንፈስ ወስዶ በሰባው ሽማግሌዎች ላይ አኖረ፤ መንፈሱም በእነርሱ ላይ ባደረ ጊዜ ትንቢት ተናገሩ፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተናገሩም። ከእነርሱም ሁለት ሰዎች በሰፈሩ ውስጥ ቀርተው ነበር፥ የአንዱም ስም ኤልዳድ ሲሆን የሁለተኛው ስም ደግሞ ሞዳድ ይባል ነበረ፤ መንፈስም ወረደባቸው፤ እነርሱም ከተጻፉት ጋር ነበሩ ወደ ድንኳኑ ግን ወጥተው አልሄዱም ነበር፤ በሰፈሩም ውስጥ ሳሉ ትንቢት ተናገሩ። አንድ ጐልማሳ ሰው እየሮጠ መጥቶ፦ “ኤልዳድና ሞዳድ በሰፈሩ ውስጥ ሆነው ትንቢት እየተናገሩ ናቸው” ብሎ ለሙሴ ነገረው። ከልጅነቱ ጀምሮ የሙሴ አገልጋይ የነበረው የነዌ ልጅ ኢያሱ፦ “ጌታዬ ሙሴ ሆይ! ከልክላቸው” አለው። ሙሴ ግን እንዲህ አለው፦ “የጌታ ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ ጌታም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያኖር፤ አንተ ስለ እኔ ትቀናለህን?” ሙሴም ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋር ወደ ሰፈር ተመለሰ። ነፋስም ከጌታ ዘንድ ወጣ፥ ከባሕርም ድርጭቶችን አመጣ፥ እነርሱንም የአንድ ቀን መንገድ ያህል በዚህ፥ የአንድ ቀንም መንገድ ያህል በዚያ በሰፈሩ አጠገብ በተናቸው፤ በዚያም በሰፈሩ ዙሪያ ከፍታው ከምድር ወደ ላይ ሁለት ክንድ ያህል ቈለላቸው። በዚያም ቀን ሁሉ በሌሊትም ሁሉ በማግስቱም ሁሉ ሕዝቡ ተነሥተው ድርጭትን ሰበሰቡ፤ ከሁሉ ጥቂት የሰበሰበ ዐሥር የቆሮስ መስፈሪያ የሚህል ሰበሰበ፤ በሰፈሩም ዙሪያ ሁሉ አሰጡት። ሥጋውም ገና በጥርሳቸው መካከል ሳለ ሳይታኘክ የጌታ ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፤ ጌታም ሕዝቡን እጅግ ታላቅ በሆነ መቅሠፍት መታ።