ናሆም 1:7-15
ናሆም 1:7-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር መልካም ነው፥ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፣ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል። ስፍራዋን ግን በሚያጥለቀልቅ ጎርፍ ፈጽሞ ያጠፋታል፥ ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል። በእግዚአብሔር ላይ የምታስቡት ምንድር ነው? እርሱ ፈጽሞ ያጠፋል፥ መከራም ሁለተኛ አይነሣም። እርስ በእርሳቸው እንደ ተመሰቃቀለ እሾህ ቢሆኑ፥ በመጠጣቸውም ቢሰክሩ እንደ ደረቅ ገለባ ፈጽመው ይጠፋሉ። በእግዚአብሔር ላይ በክፉ የሚያስብ፥ ክፋትን የሚመክር፥ ከአንተ ዘንድ ወጥቶአል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ኃይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑ እንዲሁ ይቈረጣሉ፥ እርሱም ያልቃል። እኔም አስጨንቄሃለሁ፥ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ አላስጨንቅህም። አሁንም ቀንበሩን ከአንተ እሰብራለሁ፥ እስራትህንም እበጥሳለሁ። እግዚአብሔርም ከስምህ ማንም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይዘራ ስለ አንተ አዝዞአል፣ ከአምላኮችህ ቤት የተቀረጸውንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል አጠፋለሁ። አንተም የተጠቃህ ነህና መቃብርህን እምሳለሁ። እነሆ፥ የምስራችን የሚያመጣ ሰላምንም የሚያወራ ሰው እግር በተራሮች ላይ ነው! ይሁዳ ሆይ፥ አጥፊው ፈጽሞ ጠፍቶአልና፥ ከእንግዲህም ወዲህ በአንተ ዘንድ አያልፍምና ዓመት በዓሎችህን አድርግ፥ ስእለቶችህን ክፈል።
ናሆም 1:7-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር መልካም ነው፤ በጭንቅ ጊዜም መሸሸጊያ ነው። ለሚታመኑበት ይጠነቀቅላቸዋል፤ ነነዌን ግን፣ በሚያጥለቀልቅ ጐርፍ ያጠፋታል፤ ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል። በእግዚአብሔር ላይ ምንም ቢያሤሩ፣ እርሱ ያጠፋዋል፤ መከራም ዳግመኛ አይነሣም። በእሾኽ ይጠላለፋሉ፤ በወይን ጠጃቸውም ይሰክራሉ፤ እሳትም እንደ ገለባ ይበላቸዋል። ነነዌ ሆይ፤ በእግዚአብሔር ላይ የሚያሤር፣ ምናምንቴ ክፉ መካሪ፣ ከአንቺ ዘንድ ወጥቷል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ምንም ኀይለኞችና ብዙዎች ቢሆኑም፣ ይቈረጣሉ፤ ይጠፋሉም። ይሁዳ ሆይ፤ ከዚህ በፊት ባስጨንቅህም፣ ከእንግዲህ አላስጨንቅህም። አሁንም ቀንበራቸውን ከዐንገትህ ላይ አንሥቼ እሰብራለሁ፤ የታሰርህበትንም ሰንሰለት በጥሼ እጥላለሁ።” አንቺ ነነዌ፤ እግዚአብሔር ስለ አንቺ እንዲህ ብሎ አዝዟል፤ “ስም የሚያስጠራ ትውልድ አይኖራችሁም፤ በአማልክታችሁ ቤት ያሉትን፣ የተቀረጹትን ምስሎችና ቀልጠው የተሠሩትን ጣዖታት እደመስሳለሁ፤ መቀበሪያህን እምስልሃለሁ፤ አንተ ክፉ ነህና።” እነሆ፤ የምሥራች የሚያመጣው፣ ሰላምን የሚያውጀው ሰው እግር፣ በተራሮች ላይ ነው፤ ይሁዳ ሆይ፤ በዓላትህን አክብር፤ ስእለትህንም ፈጽም፤ ከእንግዲህ ምናምንቴ ሰዎች አይወርሩህም፤ እነርሱም ፈጽመው ይጠፋሉ።
ናሆም 1:7-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ቸር ነው፤ በመከራ ጊዜም ጠንካራ መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚተማመኑትን ሁሉ ይንከባከባል። ተቃዋሚዎቹን በኀይለኛ ጐርፍ ያጥለቀልቃቸዋል፤ ጠላቶቹንም ወደ ጨለማ ያሳድዳቸዋል። እናንተ በእግዚአብሔር ላይ የምታሤሩት ለምንድን ነው? እርሱ እናንተን እስከ መጨረሻው ይደመስሳችኋል፤ ዳግመኛም በእርሱ ላይ መነሣሣት ከቶ አትችሉም። እናንተ ሰካራሞች! እርስ በርሱ የተያያዘ እሾኽና ድርቆሽ በእሳት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ፥ እናንተም እንዲሁ ትጠፋላችሁ። የነነዌ ሕዝብ ሆይ! በእግዚአብሔር ላይ ሤራ የሚያሤርና ክፉ ምክር የሚመክር ሰው ከመካከላችሁ ተነሥቶአል። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለይሁዳ እንዲህ ይላል፦ “አሦራውያን ኀይለኞችና ቊጥራቸው የበዛ ቢሆንም እንኳ ተደምስሰው እንዳልነበሩ ይሆናሉ። ሕዝቤ ሆይ! ከዚህ በፊት መከራ ያጸናሁባችሁ ቢሆንም እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን አላደርግባችሁም። አሦራውያን በእናንተ ላይ የጫኑትን የጭቈና አገዛዝ አስወግዳለሁ፤ እናንተን ያሰሩበትንም እግር ብረት እሰብራለሁ።” እግዚአብሔር ስለ አሦራውያን የሰጠው ፍርድ እንዲህ የሚል ነው፦ “ከእንግዲህ ወዲህ ስማችሁን የሚያስጠራ ተተኪ ዘር አይኖራችሁም፤ በአማልክታችሁ ቤተ መቅደስ የሚገኙትን የተቀረጹ ምስሎችንና ቀልጠው የተሠሩ ጣዖቶችን አጠፋለሁ፤ እናንተም ዋጋ ቢሶች ስለ ሆናችሁ የመቃብር ጒድጓድ እምስላችኋለሁ።” እነሆ መልካም ዜናን የሚያበሥር፥ ሰላምንም የሚያውጅ መልእክተኛ በተራሮች ላይ እየመጣ ነው። የይሁዳ ሕዝብ ሆይ! ክፉዎች ጠላቶችህ ፈጽሞ ስለ ተደመሰሱ ከእንግዲህ ወዲህ አገርህን ከቶ አይወሩአትም! ስለዚህ ዓመት በዓሎችህን በደስታ አክብር! ስእለትህንም ለእግዚአብሔር ስጥ!