ማርቆስ 9:17-27
ማርቆስ 9:17-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከሕዝቡ አንዱ መልሶ “መምህር ሆይ! ድዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤ በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፤ አልቻሉምም” አለው። እርሱም መልሶ “የማታምን ትውልድ ሆይ! እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት፤” አላቸው። ወደ እርሱም አመጡት። እርሱንም ባየ ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያው አንፈራገጠው፤ ወደ ምድርም ወድቆ አረፋ እየደፈቀ ተንፈራፈረ። አባቱንም “ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ብዙ ጊዜም ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኀም ጣለው፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን፤ እርዳንም፤” አለው። ኢየሱስም “ቢቻልህ ትላለህ? ለሚያምን ሁሉ ይቻላል፤” አለው። ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ “አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው፤” አለ። ኢየሱስም ሕዝቡ እንደ ገና ሲራወጥ አይቶ ርኵሱን መንፈስ ገሠጸና “አንተ ድዳ ደንቆሮም መንፈስ፥ እኔ አዝሃለሁ፤ ከእርሱ ውጣ! ከእንግዲህም አትግባበት፤” አለው። ጮኾም እጅግም አንፈራግጦት ወጣ፤ ብዙዎችም “ሞተ” እስኪሉ ድረስ እንደ ሙት ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ቆመም።
ማርቆስ 9:17-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ ዐድሮበት ድዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ ዐረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፋጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፣ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋራ እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት።” አላቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፣ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፣ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።” ኢየሱስም፣ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን ርዳው!” በማለት ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ ወደዚያ እየተንጋጋ በሩጫ መምጣቱን ባየ ጊዜ፣ “አንተ ደንቈሮና ድዳ መንፈስ ከርሱ ውጣ! ከእንግዲህም ተመልሰህ እንዳትገባበት አዝዝሃለሁ” ብሎ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ እየጮኸ ክፉኛ ካንፈራገጠው በኋላ ከልጁ ወጣ፤ ብዙዎቹ “ሞቷል” እስኪሉ ድረስ ልጁ እንደ በድን ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ በእግሮቹ ቆመ።
ማርቆስ 9:17-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከሕዝቡ አንዱ መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ፤ በያዘውም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋም ይደፍቃል፥ ጥርሱንም ያፋጫል ይደርቃልም፤ እንዲያወጡለትም ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸው፥ አልቻሉምም አለው። እርሱም መልሶ፦ የማታምን ትውልድ ሆይ፥ እስከመቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደ እኔ አምጡት አላቸው። ወደ እርሱም አመጡት። እርሱንም ባየ ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያው አንፈራገጠው፤ ወደ ምድርም ወድቆ አረፋ እየደፈቀ ተንፈራፈረ። አባቱንም፦ ይህ ከያዘው ስንት ዘመን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም፦ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ብዙ ጊዜም ሊያጠፋው ወደ እሳትም ወደ ውኃም ጣለው፤ ቢቻልህ ግን እዘንልን እርዳንም አለው። ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ፦ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ። ኢየሱስም ሕዝቡ እንደ ገና ሲራወጥ አይቶ ርኵሱን መንፈስ ገሠጸና፦ አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ፥ እኔ አዝሃለሁ፥ ከእርሱ ውጣ እንግዲህም አትግባበት አለው። ጮኾም እጅግም አንፈራግጦት ወጣ፤ ብዙዎችም፦ ሞተ እስኪሉ ድረስ እንደ ሙት ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው ቆመም።
ማርቆስ 9:17-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከሕዝቡም መካከል አንዱ፥ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “መምህር ሆይ፥ ድዳ በሚያደርግ መንፈስ የተያዘውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በሚነሣበትም ጊዜ ይጥለዋል፤ አፉም ዐረፋ እየደፈቀ ጥርሶቹን ያፋጫል፤ ሰውነቱም ደርቆ እንደ በድን ይሆናል፤ ርኩሱንም መንፈስ እንዲያስወጡለት ደቀ መዛሙርትህን ጠይቄአቸው ነበር፤ ነገር ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የማታምኑ ሰዎች! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” እነርሱም ልጁን ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩሱም መንፈስ ኢየሱስን ባየ ጊዜ ወዲያው ልጁን ጥሎ አንፈራገጠው፤ ልጁም በመሬት ላይ እየተንከባለለ ዐረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፥ “ይህ በሽታ ከጀመረው ምን ያኽል ጊዜ ነው?” ሲል ጠየቀው። አባትየውም እንዲህ አለ፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው። ሊገድለውም እየፈለገ ብዙ ጊዜ በእሳትና በውሃ ውስጥ ይጥለዋል፤ ግን አንዳች ነገር ማድረግ ብትችል እባክህ እዘንልን! እርዳንም!” ኢየሱስም “ብትችል” ትላለህን? “ለሚያምን ሰው ሁሉ ነገር ይቻላል!” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፥ “ማመንስ አምናለሁ፤ ግን ማመን በሚያቅተኝ ነገር ሁሉ ደግሞ አንተ እርዳኝ!” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ እየተራወጡ ሲመጡ አየ፤ ርኩሱንም መንፈስ “አንተ ድዳና ደንቆሮ መንፈስ ከልጁ እንድትወጣ ወደ እርሱም ተመልሰህ እንዳትገባ አዝሃለሁ!” ብሎ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ልጁንም በጣም ካንፈራገጠው በኋላ ወጣ፤ ልጁም ልክ እንደ በድን በመሆኑ ብዙዎቹ የሞተ መሰላቸው። ኢየሱስ ግን የልጁን እጅ ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ።
ማርቆስ 9:17-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ ርኩስ መንፈስ አድሮበት ዲዳ የሆነውን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼዋለሁ፤ በተነሣበት ጊዜ ሁሉ ይጥለዋል፤ አረፋ ይደፍቃል፤ ጥርሱንም ያፏጫል፤ ሰውነቱም ይደርቃል፤ ርኩስ መንፈሱን እንዲያስወጡት ደቀ መዛሙርትህን ጠየቅኋቸው፤ እነርሱ ግን አልቻሉም።” ኢየሱስም መልሶ፥ “የማታምን ትውልድ ሆይ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጁን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው። ሰዎቹም ወደ እርሱ አመጡት፤ ርኩስ መንፈሱም ኢየሱስን ባየው ጊዜ ልጁን ወዲያውኑ አንዘፈዘፈው፤ እርሱም መሬት ላይ ወድቆ በመንፈራገጥም አረፋ ይደፍቅ ጀመር። ኢየሱስም የልጁን አባት፥ “ከያዘው ስንት ጊዜው ነው?” ብሎ ጠየቀው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “ከሕፃንነቱ ጀምሮ ነው፤ ሊገድለው ፈልጎ ብዙ ጊዜ እሳትም ውስጥ ውሃም ውስጥ፥ ይጥለዋል፤ የሚቻልህ ከሆነ ራራልን፤ ርዳንም።” ኢየሱስም፥ “የሚቻልህ ከሆነ አልህ? ለሚያምን ሰው ሁሉም ነገር ይቻላል” አለው። ወዲያውኑ የልጁ አባት፥ “አምናለሁ፤ አለማመኔን አይተህ እርዳኝ” በማለት ጮኸ። ኢየሱስም ሕዝቡ ወደዚያ እየተንጋጋ በሩጫ መምጣታቸውን ባየ ጊዜ፥ “አንተ ደንቆሮና ዲዳ መንፈስ ከእርሱ ውጣ! ከእንግዲህም ተመልሰህ እንዳትገባበት አዝዤሃለሁ” ብሎ ርኩሱን መንፈስ ገሠጸው። ርኩሱም መንፈስ እየጮኸ ክፉኛ ካንፈራገጠው በኋላ ከልጁ ወጣ፤ ብዙዎች “ሞቷል” እስኪሉ ድረስ ልጁ እንደ በድን ሆነ። ኢየሱስ ግን እጁን ይዞ አስነሣው፤ ልጁም ተነሥቶ ቆመ።