ማርቆስ 7:24-37
ማርቆስ 7:24-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚያም ተነሥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። ወደ ቤትም ገብቶ ማንም እንዳያውቅበት ወደደ፤ ሊሰወርም አልተቻለውም፤ ወዲያው ግን ታናሺቱ ልጅዋ ርኵስ መንፈስ ያደረባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ተደፋች፤ ሴቲቱም ግሪክ፥ ትውልድዋም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች፤ ከልጅዋ ጋኔን ያወጣላት ዘንድ ለመነችው። ኢየሱስ ግን “ልጆቹ በፊት ይጠግቡ ዘንድ ተዪ፤ የልጆቹን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባምና” አላት። እርስዋም መልሳ “አዎን፥ ጌታ ሆይ! ቡችሎች እንኳ ከማዕድ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ፤” አለችው። እርሱም “ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ፤ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል፤” አላት። ወደ ቤትዋም ሄዳ ጋኔኑ ወጥቶ ልጅዋም በአልጋ ላይ ተኝታ አገኘች። ደግሞም ከጢሮስ አገር ወጥቶ በሲዶና አልፎ ዐሥር ከተማ በሚባል አገር መካከል ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም ይጭንበት ዘንድ ለመኑት። ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው፤ ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ፤ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤ ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና “ኤፍታህ” አለው፤ እርሱም “ተከፈት” ማለት ነው። ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የምላሱም እስራት ተፈታ፤ አጥርቶም ተናገረ። “ለማንም አትንገሩ፤” ብሎ አዘዛቸው፤ እነርሱ ግን ባዘዛቸውም መጠን ይልቅ እጅግ አወሩት። ያለ መጠንም ተገረሙና “ሁሉን ደኅና አድርጎአል፤ ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል፤” አሉ።
ማርቆስ 7:24-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስ አገር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤት ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም እንዳያውቅበት ፈለገ፤ ሆኖም እዚያ መኖሩ ሊሸሸግ አልቻለም። ወዲያው ግን ትንሺቱ ልጇ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ወደቀች። ሴትዮዋም ግሪካዊት፣ በትውልዷም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች። እርሷም ኢየሱስ ጋኔኑን ከልጇ እንዲያስወጣላት ለመነችው። እርሱ ግን፣ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል ተገቢ ስላልሆነ፣ መጀመሪያ ልጆቹ ጠግበው ይብሉ” አላት። እርሷም መልሳ፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ ውሾችም እኮ ከገበታ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለችው። እርሱም፣ “ስለዚህ ይህን ስላልሽ ሂጂ፤ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷል” አላት። እርሷም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ ዐልጋ ላይ ተኝታ፣ ጋኔኑም ለቅቋት አገኘቻት። ከዚያም ኢየሱስ ከጢሮስ አገር ተነሥቶ፣ በሲዶና በኩል አድርጎ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር በማለፍ ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። በዚያም ሰዎች ደንቈሮና ዲዳ የሆነ አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት። ኢየሱስም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ከወሰደው በኋላ፣ ጣቶቹን በጆሮው አስገባ፤ ከዚያም እንትፍ ብሎ የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ። ወደ ሰማይም ተመልክቶ ቃተተና፣ “ኤፍታህ!” አለው፤ ይኸውም፣ “ተከፈት” ማለት ነው። ወዲያውም ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ ምላሱም ተፈትቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ። ኢየሱስ ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ሆኖም እርሱ እንዳይናገሩ ባዘዛቸው መጠን፣ ነገሩን አስፍተው አወሩት። ሕዝቡም ከመጠን በላይ በመደነቅ፣ “ያደረገው ሁሉ ጥሩ ነው፤ ደንቈሮዎች እንዲሰሙ፣ ድዳዎች እንዲናገሩ እንኳ አድርጓል” አሉ።
ማርቆስ 7:24-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚያም ተነሥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ። ወደ ቤትም ገብቶ ማንም እንዳያውቅበት ወደደ ሊሰወርም አልተቻለውም፤ ወዲያው ግን ታናሺቱ ልጅዋ ርኵስ መንፈስ ያደረባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ተደፋች ሴቲቱም ግሪክ፥ ትውልድዋም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች፤ ከልጅዋ ጋኔን ያወጣላት ዘንድ ለመነችው። ኢየሱስ ግን፦ ልጆቹ በፊት ይጠግቡ ዘንድ ተዪ የልጆቹን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባምናአላት። እርስዋም መልሳ፦ አዎን፥ ጌታ ሆይ፥ ቡችሎች እንኳ ከማዕድ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ አለችው። እርሱም፦ ስለዚህ ቃልሽ ሂጂ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል አላት። ወደ ቤትዋም ሄዳ ጋኔኑ ወጥቶ ልጅዋም በአልጋ ላይ ተኝታ አገኘች። ደግሞም ከጢሮስ አገር ወጥቶ በሲዶና አልፎ አሥር ከተማ በሚባል አገር መካከል ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። ደንቆሮና ኰልታፋም የሆነ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፥ እጁንም ይጭንበት ዘንድ ለመኑት። ከሕዝቡም ለይቶ ለብቻው ወሰደው፥ ጣቶቹንም በጆሮቹ አገባ እንትፍም ብሎ መላሱን ዳሰሰ፤ ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና፦ ኤፍታህ አለው፥ እርሱም ተከፈት ማለት ነው። ወዲያውም ጆሮቹ ተከፈቱ የመላሱም እስራት ተፈታ አጥርቶም ተናገረ። ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው እነርሱ ግን ባዘዛቸውም መጠን ይልቅ እጅግ አወሩት። ያለ መጠንም ተገረሙና፦ ሁሉን ደኅና አድርጎአል፤ ደንቆሮችም እንዲሰሙ ዲዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል አሉ።
ማርቆስ 7:24-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ በጢሮስ ከተማ አጠገብ ወዳለው መንደር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤትም ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም ሰው እንዳያውቅ ፈለገ፤ ይሁን እንጂ ሊሰወር አልተቻለውም። ልጅዋ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ ኢየሱስ ሰምታ ወዲያውኑ መጣችና በእግሩ ሥር ወደቀች። ሴትዮዋም ከሲሮፊኒቃውያን ወገን የሆነች ግሪካዊት ነበረች፤ እርስዋ ከልጅዋ ጋኔን እንዲያወጣላት ኢየሱስን ለመነችው። ኢየሱስ ግን፥ “የልጆችን ምግብ ወስዶ ለውሾች መስጠት አይገባምና እስቲ ልጆቹ አስቀድመው ይጥገቡ፤” አላት። እርስዋም “እርግጥ ነው ጌታዬ፤ ግን ውሾችም እኮ በገበታ ሥር ሆነው ልጆች ሲበሉ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ፤” ስትል መለሰችለት። ስለዚህ ኢየሱስ፥ “በዚህ አነጋገርሽ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቶአል፤ እንግዲህ ወደ ቤትሽ ሂጂ!” አላት። እርስዋም ወደ ቤትዋ በተመለሰች ጊዜ ልጅዋን ጋኔኑ ለቋት በአልጋ ላይ በደኅና ተኝታ አገኘቻት። ኢየሱስ የጢሮስን አካባቢ ትቶ ሄደ፤ በሲዶና በኩልም አድርጎ ዐሥር ከተሞች በሚባለው አገር ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። በዚያ አንድ ደንቆሮና ድዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት። ኢየሱስም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ወሰደና ጣቶቹን በሰውየው ጆሮዎች ውስጥ አገባ፤ ምራቁንም እንትፍ ብሎ የሰውዬውን ምላስ ዳሰሰ፤ ወደ ሰማይም አሻቅቦ አይቶ ቃተተና ሰውየውን “ኤፍታህ!” አለው፤ ፍቺውም “ተከፈት!” ማለት ነው። ወዲያውኑ ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ አንደበቱም ተፈታ፤ ያለአንዳች ችግርም አጥርቶ መናገር ጀመረ። ኢየሱስ ይህን ነገር ለማንም እንዳይናገሩ ሰዎቹን አዘዛቸው፤ ይሁን እንጂ፥ እንዳይናገሩ ባዘዛቸው መጠን በብዙ አብልጠው ያወሩ ነበር። የሰሙትም ሁሉ እጅግ በጣም በመደነቅ፦ “ሁሉን ነገር በመልካም አደረገ! ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፥ ድዳዎች እንዲናገሩ ያደርጋል!” አሉ።
ማርቆስ 7:24-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስ አገር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤት ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም እንዳያውቅበት ፈለገ፤ ሆኖም እዚያ መኖሩ ሊሸሸግ አልቻለም። ወዲያው ግን ትንሺቱ ልጇ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ወደቀች። ሴትዮዋም ግሪካዊት፥ በትውልዷም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች። እርሷም ኢየሱስ ርኩስ መንፈሱን ከልጇ እንዲያስወጣላት ለመነችው። እርሱ ግን፥ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል ተገቢ ስላልሆነ፥ መጀመሪያ ልጆቹ ጠግበው ይብሉ” አላት። እርሷም መልሳ፥ “አዎን፥ ጌታ ሆይ፤ ውሾችም ከገበታ በታች ሆነው የልጆችን ትራፊ ይበላሉ” አለችው። እርሱም፥ “ስለዚህ ይህን ስላልሽ ሂጂ፤ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷአል” አላት። እርሷም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ ዐልጋ ላይ ተኝታ፥ ጋኔኑም ለቋት አገኘቻት። ከዚያም ኢየሱስ ከጢሮስ አገር ተነሥቶ፥ በሲዶና በኩል አድርጎ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር በማለፍ ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። በዚያም ሰዎች ደንቆሮና ዲዳ የሆነ አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት። ኢየሱስም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ከወሰደው በኋላ፥ ጣቶቹን በጆሮው አስገባ፤ ከዚያም እንትፍ ብሎ የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ። ወደ ሰማይም ተመልክቶ ቃተተና፥ “ኤፋታህ” አለው፤ ይኸውም፥ “ተከፈት” ማለት ነው። ወዲያውም ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ ምላሱም ተፈቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ። ኢየሱስ ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ሆኖም እርሱ እንዳይናገሩ ባዘዛቸውም መጠን፥ ነገሩን አስፍተው አወሩት። ሕዝቡም ከመጠን በላይ በመደነቅ፥ “ያደረገው ሁሉ ጥሩ ነው፤ ደንቆሮዎች እንዲሰሙ፥ ድዳዎች እንዲናገሩ እንኳን አድርጓል” አሉ።