ማርቆስ 6:7-13
ማርቆስ 6:7-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዐሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ፤ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፤ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤” አለ። “በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፤ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል፤” አላቸው። ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፤ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።
ማርቆስ 6:7-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዐሥራ ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በቀር፣ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ትርፍ እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቈዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁ ወይም የማይሰማችሁ ከሆነ፣ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ በዚያ አራግፋችሁ ውጡ።” እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።
ማርቆስ 6:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አስራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፥ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፥ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ አለ። በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው። ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።
ማርቆስ 6:7-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤ ለመንገዳቸው ከበትር በቀር እንጀራም ሆነ ከረጢት፥ ገንዘብም በመቀነታቸው እንዳይዙ አዘዛቸው። እንዲህም አላቸው፤ “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀጠባብ እንኳ አትልበሱ፤ በማናቸውም ስፍራ ወደ አንድ ሰው ቤት ስትገቡ፥ ያንን ስፍራ እስክትለቁ ድረስ በዚያው ቈዩ፤ ሰዎች በማይቀበሉአችሁና በማይሰሙአችሁ ቦታ ሁሉ የእግራችሁን አቧራ አራግፉና ከዚያ ወጥታችሁ ሂዱ፤ ይህም ለእነርሱ የማስጠንቀቂያ ምስክር ይሆንባቸዋል።” የተላኩትም ከዚያ ወጥተው፥ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ አስተማሩ። ብዙ አጋንንትንም አስወጡ፤ ብዙ ሰዎችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።
ማርቆስ 6:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህንንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በስተቀር፥ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቆዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁና የማይሰማችሁ ከሆነ፥ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ከእግራችሁ ሥር ያለውን ትቢያ በዚያ አራግፉ፤ ይህም ምስክር ይሆንባቸዋል።” እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።