ማርቆስ 6:1-13
ማርቆስ 6:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና “እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን?” አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ኢየሱስም “ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም፤” አላቸው። በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር። ዐሥራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ፤ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፤ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤” አለ። “በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፤ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል፤” አላቸው። ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፤ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።
ማርቆስ 6:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገዛ አገሩ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በደረሰ ጊዜ፣ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ የሰሙትም ብዙ ሰዎች ተደነቁ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድን ነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይደረጋሉ? ይህ ዐናጺው አይደለምን? የማርያም ልጅ፣ የያዕቆብ፣ የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት። ኢየሱስም፣ “ነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ መካከልና በራሱ ቤት ብቻ ነው” አላቸው። እዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወሱ በቀር ምንም ታምራት ሊሠራ አልቻለም፤ ባለማመናቸውም ተደነቀ። ከዚያም ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በቀር፣ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ትርፍ እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቈዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁ ወይም የማይሰማችሁ ከሆነ፣ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ በዚያ አራግፋችሁ ውጡ።” እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።
ማርቆስ 6:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚያም ወጥቶ ወደ ገዛ አገሩ መጣ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በሆነ ጊዜ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ ብዙዎችም ሰምተው ተገረሙና፦ እነዚህን ነገሮች ይህ ከወዴት አገኛቸው? ለዚህ የተሰጠችው ጥበብ ምንድር ናት? በእጁም የሚደረጉ እንደነዚህ ያሉ ተአምራት ምንድር ናቸው? ይህስ ጸራቢው የማርያም ልጅ የያቆብም የዮሳም የይሁዳም የስምዖንም ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ በዚህ በእኛ ዘንድ አይደሉምን? አሉ፤ ይሰናከሉበትም ነበር። ኢየሱስም፦ ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ዘመዶቹ ከገዛ ቤቱም በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው። በዚያም በጥቂቶች ድውዮች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር፥ ተአምር ሊያደርግ ምንም አልቻለም። ስለ አለማመናቸውም ተደነቀ። በመንደሮችም እያስተማረ ይዞር ነበር። አስራ ሁለቱንም ወደ እርሱ ጠራ ሁለት ሁለቱንም ይልካቸው ጀመር፥ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፥ ለመንገድም ከበትር በቀር እንጀራም ቢሆን ከረጢትም ቢሆን መሐለቅም በመቀነታቸው ቢሆን እንዳይዙ አዘዛቸው። በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ አለ። በማናቸውም ስፍራ ወደ ቤት ብትገቡ ከዚያ እስክትወጡ ድረስ በዚያው ተቀመጡ። ከማይቀበሉአችሁና ከማይሰሙአችሁ ስፍራ ሁሉ፥ ከዚያ ወጥታችሁ ምስክር ይሆንባቸው ዘንድ ከእግራችሁ በታች ያለውን ትቢያ አራግፉ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ በፍርድ ቀን ይቀልላቸዋል አላቸው። ወጥተውም ንስሐ እንዲገቡ ሰበኩ፥ ብዙ አጋንንትንም አወጡ፥ ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።
ማርቆስ 6:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ አገሩ መጣ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። በሰንበት ቀን በምኲራብ ማስተማር ጀመረ፤ ብዙ ሰዎች በዚያ ተገኝተው ይሰሙት ነበር፤ እነርሱም “ይህ ሰው ይህን ሁሉ ነገር ከየት አገኘው? ምን ዐይነት ጥበብ ተሰጥቶታል? እነዚህንስ ተአምራት የሚያደርገው እንዴት ነው?” እያሉ ይደነቁ ነበር። ቀጥለውም “ለመሆኑ ይህ እንጨት ጠራቢው የማርያም ልጅ አይደለምን? የያዕቆብ፥ የዮሳ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚህ ከእኛ ጋር አይደሉምን?” እያሉ በመናቅ ሳይቀበሉት ቀሩ። ኢየሱስ ግን፥ “ነቢይ በሌሎች ዘንድ ይከበራል፤ በገዛ አገሩ፥ በዘመዶቹና በቤተ ሰቡ መካከል ግን ይናቃል፤” ሲል መለሰላቸው። በዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወስ በቀር ሌላ ተአምር ማድረግ አልቻለም። ሕዝቡ ሳያምኑ በመቅረታቸው እጅግ ተገረመ፤ ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው፤ ለመንገዳቸው ከበትር በቀር እንጀራም ሆነ ከረጢት፥ ገንዘብም በመቀነታቸው እንዳይዙ አዘዛቸው። እንዲህም አላቸው፤ “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀጠባብ እንኳ አትልበሱ፤ በማናቸውም ስፍራ ወደ አንድ ሰው ቤት ስትገቡ፥ ያንን ስፍራ እስክትለቁ ድረስ በዚያው ቈዩ፤ ሰዎች በማይቀበሉአችሁና በማይሰሙአችሁ ቦታ ሁሉ የእግራችሁን አቧራ አራግፉና ከዚያ ወጥታችሁ ሂዱ፤ ይህም ለእነርሱ የማስጠንቀቂያ ምስክር ይሆንባቸዋል።” የተላኩትም ከዚያ ወጥተው፥ ሰዎች ሁሉ ንስሓ እንዲገቡ አስተማሩ። ብዙ አጋንንትንም አስወጡ፤ ብዙ ሰዎችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።
ማርቆስ 6:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገዛ አገሩ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ሰንበትም በደረሰ ጊዜ፥ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ የሰሙትም ብዙ ሰዎች ተደነቁ። እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይደረጋሉ ይህ ዐናጢው አይደለምን? የማርያም ልጅ፥ የያዕቆብና የዮሳ፥ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት። ኢየሱስም፥ “ነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፥ በዘመዶቹ መካከል በቤተሰቡ ዘንድ ብቻ ነው” አላቸው። እዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወሱ በስተቀር ምንም ታምራት ሊሠራ አልቻለም፤ ባለማመናቸውም ተደነቀ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር። ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። ይህንንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በስተቀር፥ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቆዩ፤ የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁና የማይሰማችሁ ከሆነ፥ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ከእግራችሁ ሥር ያለውን ትቢያ በዚያ አራግፉ፤ ይህም ምስክር ይሆንባቸዋል።” እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።