ማርቆስ 5:22-34
ማርቆስ 5:22-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢያኢሮስ የተባለ ከምኵራብ አለቆች አንዱ መጣ፤ ባየውም ጊዜ በእግሩ ላይ ወደቀና “ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት፤” ብሎ አጥብቆ ለመነው። ከእርሱም ጋር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም። ከዐሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፤ ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤ የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች “ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ፤” ብላለችና። ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ፤ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች። ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ “ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው?” አለ። ደቀ መዛሙርቱም “ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ ‘ማን ዳሰሰኝ?” ትላለህን?” አሉት። ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር። ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም “ልጄ ሆይ! እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሽ፤” አላት።
ማርቆስ 5:22-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከምኵራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው ወደዚያ መጥቶ ስለ ነበር፣ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሮቹ ላይ ወድቆ፣ “ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና ድና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው። ኢየሱስም ዐብሮት ሄደ። ብዙ ሕዝብም ዙሪያውን እያጨናነቀው ተከተለው። ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት በዚያ ነበረች፤ በብዙ ባለመድኀኒቶች ዘንድ በመንከራተት ያላትን ሁሉ ብትጨርስም፣ ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፣ ከበስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤ ምክንያቱም፣ “እንደ ምንም ብዬ ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” የሚል እምነት ነበራት። የሚፈስሰው ደሟም ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ መገላገሏም በሰውነቷ ታወቃት። ወዲያውኑ ኢየሱስ፣ ኀይል ከርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዘወር በማለት፣ “ልብሴን የነካው ማን ነው?” አለ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፣ ‘ማን ነው የነካኝ?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። ሴትዮዋም ምን እንደ ተደረገላት ባወቀች ጊዜ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም፣ “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ዕረፊ” አላት።
ማርቆስ 5:22-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢያኢሮስ የተባለ ከምኵራብ አለቆች አንዱ መጣ፤ ባየውም ጊዜ በእግሩ ላይ ወደቀና፦ ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት ብሎ አጥብቆ ለመነው። ከእርሱም ጋር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም። ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤ የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች፦ ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ብላለችና። ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች። ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ፦ ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው? አለ። ደቀ መዛሙርቱም፦ ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ፦ ማን ዳሰሰኝ ትላለህን? አሉት። ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር። ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም፦ ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት።
ማርቆስ 5:22-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እዚያም ከምኲራብ አለቆች አንዱ የነበረ፥ ኢያኢሮስ የተባለ ሰው ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ሥር ወድቆ “ትንሽዋ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናት፤ እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር እባክህ መጥተህ እጅህን ጫንባት!” ሲል አጥብቆ ለመነው። ኢየሱስም አብሮት ሄደ፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት በዙሪያው ያጣብቡት ነበር። ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም እየመታት የምትሠቃይ አንዲት ሴት ነበረች። ከሐኪም ወደ ሐኪም በመሄድ ብዙ ተሠቃይታና ገንዘብዋንም ሁሉ ጨርሳ ነበር። ነገር ግን እየባሰባት ሄደ እንጂ ምንም አልተሻላትም። እርስዋም የኢየሱስን ዝና ሰምታ ስለ ነበር በሚጋፋው ሕዝብ መካከል ከበስተኋላው መጥታ ልብሱን ነካች። ይህንንም ያደረገችው፦ “ልብሱን እንኳ ብነካ እድናለሁ፤” በሚል እምነት ነበረ። የሚፈሰው ደምዋም ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሕመምዋም እንደ ዳነች በሰውነትዋ ተሰማት። ኢየሱስም ወዲያውኑ ኀይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐወቀ፤ ወደ ሕዝቡም ዘወር ብሎ፦ “ልብሴን የነካ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “ሕዝቡ እየተጋፋ ሲከተልህ እያየህ፥ ‘ማን ነው የነካኝ?’ ትላለህን?” አሉት። እርሱም ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዘወር ብሎ ተመለከተ። ሴትዮዋ ግን በእርስዋ የሆነውን በማወቅዋ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች በፊቱ ወድቃ እውነቱን ሁሉ ነገረችው። እርሱም “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሺ፤” አላት።
ማርቆስ 5:22-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከምኲራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው፥ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቆ፥ “ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው። ኢየሱስም አብሮት ሄደ። ብዙ ሕዝብም እያጨናነቀው ተከተለው። ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረችም ሴት በዚያ ነበረች፤ በብዙ ባለ መድኀኒቶችም ዘንድ ብዙ ተሠቃይታ፥ ያላትን ሁሉ ጨረሰች እንጂ አልተሻላትም ነበር፤ እንዲያውም ሕመሙ ብሶባት ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፥ ከበስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤ ምክንያቱም፥ “እንደ ምንም ብዬ ልብሱን እንኳ ብነካ ይፈውሰኛል” በማለት ነበር። የሚፈሰው ደሟ ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ እንደዳነች በሰውነቷ ታወቃት። ኢየሱስም ወዲያውኑ ኃይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዞሮ፥ “ልብሴን የነካ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ደቀ መዛሙርቱም፥ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፥ ‘ማን ነው የነካኝ?’ ትላለህን? አሉት።” እርሱም ይህን ያደረገችው ማን እንደ ሆነች ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። ሴትዮዋም የተደረገላትን በማወቅዋ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም፥ “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሺ” አላት።