ማርቆስ 5:21-43
ማርቆስ 5:21-43 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም ደግሞ በታንኳይቱ ወደ ማዶ ከተሻገረ በኋላ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ በባሕርም አጠገብ ነበረ። ኢያኢሮስ የተባለ ከምኵራብ አለቆች አንዱ መጣ፤ ባየውም ጊዜ በእግሩ ላይ ወደቀና “ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት፤” ብሎ አጥብቆ ለመነው። ከእርሱም ጋር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም። ከዐሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፤ ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤ የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች “ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ፤” ብላለችና። ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ፤ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች። ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ “ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው?” አለ። ደቀ መዛሙርቱም “ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ ‘ማን ዳሰሰኝ?” ትላለህን?” አሉት። ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር። ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም “ልጄ ሆይ! እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሽ፤” አላት። እርሱም ገና ሲናገር ከምኵራብ አለቃው ቤት ዘንድ የመጡት “ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው። ከጴጥሮስም ከያዕቆብም ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤትም መጥቶ ሰዎች ሲንጫጩና ሲያለቅሱ ዋይታም ሲያበዙ አየ፤ ገብቶም “ስለ ምን ትንጫጫላችሁ? ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም፤” አላቸው። በጣምም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናት ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞ ብላቴናይቱ ወዳለችበት ገባ። የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ፍችውም “አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ!” ነው። ብላቴናይቱም የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረችና ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ። ይህንም ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አዞአቸው “የምትበላውን ስጡአት፤” አላቸው።
ማርቆስ 5:21-43 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ እንደ ገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፣ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩ ዳርቻም እንዳለ፣ ከምኵራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው ወደዚያ መጥቶ ስለ ነበር፣ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሮቹ ላይ ወድቆ፣ “ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና ድና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው። ኢየሱስም ዐብሮት ሄደ። ብዙ ሕዝብም ዙሪያውን እያጨናነቀው ተከተለው። ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት በዚያ ነበረች፤ በብዙ ባለመድኀኒቶች ዘንድ በመንከራተት ያላትን ሁሉ ብትጨርስም፣ ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፣ ከበስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤ ምክንያቱም፣ “እንደ ምንም ብዬ ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” የሚል እምነት ነበራት። የሚፈስሰው ደሟም ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ መገላገሏም በሰውነቷ ታወቃት። ወዲያውኑ ኢየሱስ፣ ኀይል ከርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዘወር በማለት፣ “ልብሴን የነካው ማን ነው?” አለ። ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፣ ‘ማን ነው የነካኝ?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። ሴትዮዋም ምን እንደ ተደረገላት ባወቀች ጊዜ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም፣ “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ዕረፊ” አላት። ኢየሱስም በመነጋገር ላይ እያለ፣ ሰዎች ከምኵራቡ አለቃ ከኢያኢሮስ ቤት መጥተው፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከእንግዲህ መምህሩን ለምን ታደክመዋለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ሰዎቹ የተናገሩትን ችላ በማለት የምኵራቡን አለቃ፣ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው። ከጴጥሮስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤት እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ግርግሩንና ሰዎቹም ዋይ ዋይ እያሉ አምርረው ሲያለቅሱ ተመለከተ። ወደ ቤትም ገብቶ፣ “ይህ ሁሉ ግርግርና ልቅሶ ምንድን ነው? ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። ሰዎቹ ግን ሣቁበት። ሰዎቹን ሁሉ ከቤት ካስወጣ በኋላ፣ የብላቴናዪቱን አባትና እናት እንዲሁም ዐብረውት የመጡትን ደቀ መዛሙርት አስከትሎ ብላቴናዪቱ ወዳለችበት ገባ። ከዚያም የብላቴናዪቱን እጅ ይዞ፣ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ትርጕሙም፣ “አንቺ ልጅ ተነሺ” ማለት ነው። ብላቴናዪቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ ወዲያ ወዲህም ሄደች። ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር። ሰዎቹም በሁኔታው እጅግ ተደነቁ። እርሱም ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ የሚበላ ነገር እንዲሰጧትም ነገራቸው።
ማርቆስ 5:21-43 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም ደግሞ በታንኳይቱ ወደ ማዶ ከተሻገረ በኋላ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ በባሕርም አጠገብ ነበረ። ኢያኢሮስ የተባለ ከምኵራብ አለቆች አንዱ መጣ፤ ባየውም ጊዜ በእግሩ ላይ ወደቀና፦ ታናሽቱ ልጄ ልትሞት ቀርባለችና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት ብሎ አጥብቆ ለመነው። ከእርሱም ጋር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት አጋፉትም። ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ከብዙ ባለ መድኃኒቶችም ብዙ ተሠቃየች፤ ገንዘብዋንም ሁሉ ከስራ ባሰባት እንጂ ምንም አልተጠቀመችም፤ የኢየሱስንም ወሬ ሰምታ በስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ዳሰሰች፦ ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ ብላለችና። ወዲያውም የደምዋ ምንጭ ደረቀ ከሥቃይዋም እንደዳነች በሰውነትዋ አወቀች። ወዲያውም ኢየሱስ ከእርሱ ኃይል እንደ ወጣ በገዛ ራሱ አውቆ በሕዝቡ መካከል ዘወር ብሎ፦ ልብሴን የዳሰሰ ማን ነው? አለ። ደቀ መዛሙርቱም፦ ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ፦ ማን ዳሰሰኝ ትላለህን? አሉት። ይህንም ያደረገችውን ለማየት ዘወር ብሎ ይመለከት ነበር። ሴቲቱ ግን የተደረገላትን ስላወቀች፥ እየፈራች እየተንቀጠቀጠችም፥ መጥታ በፊቱ ተደፋች እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም፦ ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሽ አላት። እርሱም ገና ሲናገር ከምኵራብ አለቃው ቤት ዘንድ የመጡት፦ ልጅህ ሞታለች፤ ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ? አሉት። ኢየሱስ ግን የተናገሩትን ቃል አድምጦ ለምኵራቡ አለቃ፦ እመን ብቻ እንጂ አትፍራ አለው። ከጴጥሮስም ከያዕቆብም ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤትም መጥቶ ሰዎች ሲንጫጩና ሲያለቅሱ ዋይታም ሲያበዙ አየ፤ ገብቶም፦ ስለ ምን ትንጫጫላችሁ ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አላቸው። በጣምም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጥቶ የብላቴናይቱን አባትና እናትም ከእርሱ ጋር የነበሩትንም ይዞ ብላቴናይቱ ወዳለችበት ገባ። የብላቴናይቱንም እጅ ይዞ፦ ጣሊታ ቁሚ አላት፤ ፍችውም አንቺ ብላቴና ተነሽ እልሻለሁ ነው። ብላቴናይቱም የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ነበረችና ወዲያው ቆማ ተመላለሰች። ወዲያውም ታላቅ መገረም ተገረሙ። ይህንም ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አዞአቸው፦ የምትበላውን ስጡአት አላቸው።
ማርቆስ 5:21-43 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ በጀልባ ወደ ባሕሩ ማዶ እንደገና በተመለሰ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ በዚያ ጊዜ እርሱ በባሕሩ አጠገብ ነበር። እዚያም ከምኲራብ አለቆች አንዱ የነበረ፥ ኢያኢሮስ የተባለ ሰው ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ሥር ወድቆ “ትንሽዋ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናት፤ እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር እባክህ መጥተህ እጅህን ጫንባት!” ሲል አጥብቆ ለመነው። ኢየሱስም አብሮት ሄደ፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት በዙሪያው ያጣብቡት ነበር። ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም እየመታት የምትሠቃይ አንዲት ሴት ነበረች። ከሐኪም ወደ ሐኪም በመሄድ ብዙ ተሠቃይታና ገንዘብዋንም ሁሉ ጨርሳ ነበር። ነገር ግን እየባሰባት ሄደ እንጂ ምንም አልተሻላትም። እርስዋም የኢየሱስን ዝና ሰምታ ስለ ነበር በሚጋፋው ሕዝብ መካከል ከበስተኋላው መጥታ ልብሱን ነካች። ይህንንም ያደረገችው፦ “ልብሱን እንኳ ብነካ እድናለሁ፤” በሚል እምነት ነበረ። የሚፈሰው ደምዋም ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሕመምዋም እንደ ዳነች በሰውነትዋ ተሰማት። ኢየሱስም ወዲያውኑ ኀይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐወቀ፤ ወደ ሕዝቡም ዘወር ብሎ፦ “ልብሴን የነካ ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። ደቀ መዛሙርቱም፦ “ሕዝቡ እየተጋፋ ሲከተልህ እያየህ፥ ‘ማን ነው የነካኝ?’ ትላለህን?” አሉት። እርሱም ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዘወር ብሎ ተመለከተ። ሴትዮዋ ግን በእርስዋ የሆነውን በማወቅዋ በፍርሃት እየተንቀጠቀጠች በፊቱ ወድቃ እውነቱን ሁሉ ነገረችው። እርሱም “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሺ፤” አላት። ኢየሱስ ገና ይህን በመናገር ላይ ሳለ ከምኲራብ አለቃው ቤት የመጡ ሰዎች የምኲራብ አለቃውን፦ “ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ ስለምን መምህሩን ታደክመዋለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ይህን ሰምቶ የምኲራቡን አለቃ፦ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ!” አለው። ኢየሱስ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ፥ ከያዕቆብም ወንድም ከዮሐንስ በቀር፥ ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። ወደ ምኲራብ አለቃው ቤት በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ሰዎቹ ሲንጫጩና ሲያለቅሱ፥ ሲጮኹም ተመለከተ። ወደ ውስጥ ገብቶም፦ “ይህ ሁሉ ሁካታና ለቅሶ ስለምንድን ነው? ልጅትዋ አንቀላፍታለች እንጂ አልሞተችም፤” አላቸው። ሰዎቹም በማፌዝ ሳቁበት፤ ኢየሱስ ግን ሁሉንም ከቤት አስወጣ፤ የልጅትዋን አባትና እናት ከእርሱም ጋር የነበሩትን አስከትሎ፦ ልጅትዋ ወደነበረችበት ክፍል ገባ። የልጅትዋንም እጅ ይዞ፥ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ትርጒሙም “አንቺ ልጅ ተነሺ እልሻለሁ፤” ማለት ነው። እርስዋ የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ስለ ነበረች ወዲያውኑ ተነሥታ ወዲያና ወዲህ ማለት ጀመረች፤ ይህም በሆነ ጊዜ ሰዎቹ እጅግ ተደነቁ። ኢየሱስ ግን ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አዘዛቸውና “የምትበላውን ስጡአት!” አላቸው።
ማርቆስ 5:21-43 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስ እንደገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፥ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩም አጠገብ እንዳለ፤ ከምኲራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው፥ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቆ፥ “ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና እንድትድንና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው። ኢየሱስም አብሮት ሄደ። ብዙ ሕዝብም እያጨናነቀው ተከተለው። ለዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረችም ሴት በዚያ ነበረች፤ በብዙ ባለ መድኀኒቶችም ዘንድ ብዙ ተሠቃይታ፥ ያላትን ሁሉ ጨረሰች እንጂ አልተሻላትም ነበር፤ እንዲያውም ሕመሙ ብሶባት ነበር። ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፥ ከበስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤ ምክንያቱም፥ “እንደ ምንም ብዬ ልብሱን እንኳ ብነካ ይፈውሰኛል” በማለት ነበር። የሚፈሰው ደሟ ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ እንደዳነች በሰውነቷ ታወቃት። ኢየሱስም ወዲያውኑ ኃይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዞሮ፥ “ልብሴን የነካ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀ። ደቀ መዛሙርቱም፥ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፥ ‘ማን ነው የነካኝ?’ ትላለህን? አሉት።” እርሱም ይህን ያደረገችው ማን እንደ ሆነች ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። ሴትዮዋም የተደረገላትን በማወቅዋ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። እርሱም፥ “ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ተፈወሺ” አላት። ኢየሱስም በመነጋገር ላይ እያለ፥ ሰዎች ከምኵራብ አለቃው ቤት መጥተው የምኵራብ አለቃውን፥ “ልጅህ ሞታለች፤ ከእንግዲህ መምህሩን ለምን ታደክመዋለህ?” አሉት። ኢየሱስ ግን ሰዎቹ ያሉትን ቢሰማም የምኵራቡ ን አለቃ፥ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው። ከጴጥሮስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤት በደረሱ ጊዜ፥ ሲታወኩ፥ ሰዎቹም ሲያለቅሱና አምርረውም ሲጮኹ ተመለከተ። ወደ ውስጥ ገብቶም፥ “ይህን ያህል ለምን ትታወካላችሁ ለምን ታለቅሳላችሁ? ልጅቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። ሰዎቹም ሳቁበት። እርሱ ግን ሁሉን አስወጣ፤ የልጅቱንም አባትና እናት እንዲሁም አብረውት የመጡትን አስከትሎ ልጅቱ ወዳለችበት ገባ። ከዚያም የልጅቱን እጅ ይዞ፥ “ጣሊታ ቁሚ” አላት፤ ትርጉሙም፥ “አንቺ ልጅ ተነሺ” ማለት ነው። ልጅቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ መራመድ ጀመረች፤ ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ ሰዎቹም እጅግ በመደነቅ ተደመሙ። እርሱም ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ የሚበላ ነገር እንዲሰጧትም ነገራቸው።