ማርቆስ 5:1-20
ማርቆስ 5:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ ባሕር ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን አገር መጡ። ከታንኳይቱም በወጣ ጊዜ፥ ርኵስ መንፈስ የያዘው ሰው ከመቃብር ወጥቶ ወዲያው ተገናኘው፤ እርሱም በመቃብር ይኖር ነበር፤ በሰንሰለትም ስንኳ ማንም ሊያስረው በዚያን ጊዜ አይችልም ነበር፤ ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበርና፤ ዳሩ ግን ሰንሰለቱን ይበጣጥስ እግር ብረቱንም ይሰባብር ነበር፤ ሊያሸንፈውም የሚችል አልነበረም፤ ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን በመቃብርና በተራራ ሆኖ ይጮኽ ነበር፤ ሰውነቱንም በድንጋይ ይቧጭር ነበር። ኢየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት፤ በታላቅ ድምፅም እየጮኸ “የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ! ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ፤” አለ፤ “አንተ ርኵስ መንፈስ፥ ከዚህ ሰው ውጣ፤” ብሎት ነበርና። “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። “ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው፤” አለው፤ ከአገርም ውጭ እንዳይሰዳቸው አጥብቆ ለመነው። በዚያም በተራራ ጥግ ብዙ የእሪያ መንጋ ይሰማራ ነበርና “ወደ እሪያዎቹ እንድንገባ ስደደን፤” ብለው ለመኑት። ኢየሱስም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ገቡ፤ ሁለት ሺህም የሚያህል መንጋ ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና በባሕር ሰጠሙ። እረኞቹም ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩ፤ ነገሩም ምን እንደ ሆነ ለማየት መጡ። ወደ ኢየሱስም መጡ፤ አጋንንትም ያደሩበትን ሌጌዎንም የነበረበትን ሰው ተቀምጦ ለብሶም ልቡም ተመልሶ አዩና ፈሩ። ያዩት ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ እሪያዎቹ ተረኩላቸው። ከአገራቸውም እንዲሄድላቸው ይለምኑት ጀመር። ወደ ታንኳይቱም በገባ ጊዜ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር እንዲኖር ለመነው። ኢየሱስም አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን “ወደ ቤትህ ወደ ቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው፤” አለው። ሄዶም ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት ዐሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፤ ሁሉም ተደነቁ።
ማርቆስ 5:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ባሕሩን ተሻግረው ጌርጌሴኖን ወደሚባል አገር መጡ። ኢየሱስ ከጀልባ እንደ ወረደ፣ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ሊገናኘው ወደ እርሱ መጣ። ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ውስጥ የሚኖርና ማንም በሰንሰለት እንኳ ሊያስረው የማይችል ነበር። ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን የእጅ ሰንሰለቱን ይበጥስ፣ የእግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ማንም ይዞ ሊያቈየው የሚችል አልነበረም። በመቃብሮቹና በተራሮቹ መካከል ቀንና ሌሊት እየተዘዋወረ በመጮኽ ሰውነቱን በድንጋይ ይቈራርጥ ነበር። ይህም ሰው ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጦ ከፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት፤ በታላቅ ድምፅ ጮኾም፣ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ!” አለው። ይህንም ያለው ኢየሱስ፣ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎት ስለ ነበር ነው። ከዚያም ኢየሱስ፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። “ብዙ ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው” አለው። እርሱም ከአገር እንዳያስወጣቸውም አጥብቆ ለመነው። በአቅራቢያውም በሚገኝ ኰረብታ ላይ ትልቅ የዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። ርኩሳን መናፍስቱም ኢየሱስን፣ “ወደ ዐሣማዎቹ ስደደን፤ እንድንገባባቸውም ፍቀድልን” ብለው ለመኑት። እርሱም ፈቀደላቸው። ርኩሳን መናፍስቱም ወጥተው በዐሣማዎቹ ገቡባቸው፤ ሁለት ሺሕ ያህል ዐሣማዎችም በገደሉ አፋፍ በመንደርደር ቍልቍል ወርደው በባሕር ውስጥ ሰጠሙ። እረኞቹ ሸሽተው ሄዱ፤ ወሬውን በከተማና በገጠር አዳረሱት፤ ሕዝቡም የሆነውን ለማየት ካለበት ወጣ። ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ፣ የአጋንንት ሰራዊት ሌጌዎን ዐድረውበት የነበረው ሰው፣ ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት በዚያ ተቀምጦ አዩት፤ ፈሩም። ይህን ያዩ ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ ዐሣማዎቹም ለሕዝቡ አወሩ። ከዚያም አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ይለምኑት ጀመር። ኢየሱስ ወደ ጀልባዪቱ በሚገባበት ጊዜ፣ አጋንንት ዐድረውበት የነበረው ሰው ዐብሮት ለመሆን ለመነው። ኢየሱስ አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን፣ “ወደ ቤትህ ሂድ፣ ለዘመዶችህም ጌታ ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ያሳየህን ምሕረት ንገራቸው” አለው። ሰውየውም ሄደ፤ ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር ሁሉ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር ያወራ ጀመር፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ።
ማርቆስ 5:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ ባሕር ማዶም ወደ ጌርጌሴኖን አገር መጡ። ከታንኳይቱም በወጣ ጊዜ፥ ርኵስ መንፈስ የያዘው ሰው ከመቃብር ወጥቶ ወዲያው ተገናኘው፤ እርሱም በመቃብር ይኖር ነበር፥ በሰንሰለትም ስንኳ ማንም ሊያስረው በዚያን ጊዜ አይችልም ነበር፤ ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበርና ዳሩ ግን ሰንሰለቱን ይበጣጥስ እግር ብረቱንም ይሰባብር ነበር፥ ሊያሸንፈውም የሚችል አልነበረም፤ ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን በመቃብርና በተራራ ሆኖ ይጮኽ ነበር ሰውነቱንም በድንጋይ ይቧጭር ነበር። ኢየሱስንም ከሩቅ ባየ ጊዜ ሮጦ ሰገደለት፥ በታላቅ ድምፅም እየጮኸ፦ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር አምልሃለሁ አለ፤ አንተ ርኵስ መንፈስ፥ ከዚህ ሰው ውጣ ብሎት ነበርና። ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው አለው፥ ከአገርም ውጭ እንዳይሰዳቸው አጥብቆ ለመነው። በዚያም በተራራ ጥግ ብዙ የእሪያ መንጋ ይሰማራ ነበርና፦ ወደ እሪያዎቹ እንድንገባ ስደደን ብለው ለመኑት። ኢየሱስም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ገቡ፥ ሁለት ሺህም የሚያህል መንጋ ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና በባሕር ሰጠሙ። እረኞቹም ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩ፤ ነገሩም ምን እንደ ሆነ ለማየት መጡ። ወደ ኢየሱስም መጡ፥ አጋንንትም ያደሩበትን ሌጌዎንም የነበረበትን ሰው ተቀምጦ ለብሶም ልቡም ተመልሶ አዩና ፈሩ። ያዩት ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ እሪያዎቹ ተረኩላቸው። ከአገራቸውም እንዲሄድላቸው ይለምኑት ጀመር። ወደ ታንኳይቱም በገባ ጊዜ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር እንዲኖር ለመነው። ኢየሱስም አልፈቀደለትም፥ ነገር ግን፦ ወደ ቤትህ በቤተ ሰዎችህ ዘንድ ሄደህ ጌታ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገልህ እንዴትስ እንደ ማረህ አውራላቸው አለው። ሄዶም ኢየሱስ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት አሥር ከተማ በሚባል አገር ይሰብክ ጀመር፥ ሁሉም ተደነቁ።
ማርቆስ 5:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የገሊላን ባሕር በጀልባ ተሻግረው ወደ ጌርጌሴኖን አገር ደረሱ። ኢየሱስ ከጀልባው እንደ ወረደ አንድ በርኩስ መንፈስ የተያዘ ሰው ወዲያውኑ ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ተገናኘው። ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ይኖር ነበር፤ ማንም በሰንሰለት እንኳ አስሮ ሊያቈየው አይችልም ነበር። ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን ሰንሰለቱን እየበጣጠሰና እግር ብረቱንም እየሰባበረ ይጥል ነበር፤ ስለዚህ ይዞ ሊያቆመው የሚችል ማንም አልነበረም። ሁልጊዜም ሌሊትና ቀን ባለማቋረጥ በየመቃብር ቦታና በየተራራው ላይ እየተዘዋወረ ይጮኽ ነበር፤ ሰውነቱን በድንጋይ እየቈራረጠ ያቈስል ነበር። እርሱም ኢየሱስን በሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጠና በጒልበቱ ተንበርክኮ ሰገደለት። በታላቅ ድምፅም እየጮኸ፥ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ! አንተ ከእኔ ጋር ምን ጉዳይ አለህ? በእግዚአብሔር ስም እለምንሃለሁ፤ እባክህ አታሠቃየኝ!” አለው። ይህንንም ያለበት ምክንያት፥ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎ አዞት ስለ ነበር ነው። ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው፤ እርሱም “ብዙዎች ስለ ሆንን ስሜ ሌጌዎን ነው፤” ሲል መለሰለት። ከዚያም አገር እንዳያባርራቸው አጥብቆ ለመነው። በዚያም ስፍራ በኮረብታዎች ጥግ ብዙ የዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር፤ ስለዚህ “እባክህ ሄደን ወደ ዐሣማዎቹ እንድንገባ ፍቀድልን፤” ብለው ለመኑት፤ ኢየሱስም ፈቀደላቸው፤ ርኩሳን መናፍስቱም ከዚያ ሰው ወጥተው በዐሣማዎቹ ውስጥ ገቡ፤ በመንጋዎቹ የነበሩት ሁለት ሺህ የሚያኽሉ ዐሣማዎች ከገደሉ በመንደርደር ወርደው በባሕሩ ውስጥ ሰጠሙ። የዐሣማዎቹ እረኞች ሸሽተው ሄዱ፤ በከተማና በገጠር ወሬውን አወሩ፤ ሰዎቹም የሆነውን ነገር ለማየት ከየቤታቸው ወጡ፤ ወደ ኢየሱስም መጥተው ያ በርኩሳን መናፍስት ተይዞ የነበረው ሰው ከአእምሮው ሕመም ድኖ፥ ልብሱን ለብሶ፥ ተቀምጦም ባዩት ጊዜ ደነገጡ። ይህንንም ቀደም ብለው ያዩ ሰዎች ርኩስ መንፈስ ባደረበት ሰውና በዐሣማዎቹ የሆነውን ሁሉ አወሩላቸው። በዚያን ጊዜ የአገሩ ሰዎች ኢየሱስ ከአገራቸው ወጥቶ እንዲሄድላቸው ለመኑት። ኢየሱስ ወደ ጀልባው በመግባት ላይ ሳለ አጋንንት አድረውበት የነበረው ሰው፦ “እባክህ ልከተልህ!” ብሎ ለመነው። ኢየሱስ ግን አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን፥ “ወደ ቤትህ ሂድና ጌታ ምን ያኽል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና እንዴትስ እንደማረህ ለቤተሰብህ አውራላቸው፤” አለው። ሰውየውም ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር “ዐሥር ከተሞች” በሚባል አገር ማውራት ጀመረ፤ የሰሙትም ሁሉ ይደነቁ ነበር።
ማርቆስ 5:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከባሕሩ ማዶ ተሻግረው ጌርጌሴኖን ወደ ተባለ አገር መጡ። ኢየሱስ ከጀልባ እንደ ወረደ፥ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ከመቃብር ቦታ ወጣና ወደ እርሱ መጣ። ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ውስጥ የሚኖርና ማንም በሰንሰለት እንኳ ሊያስረው የማይችል ነበር። ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን የእጅ ሰንሰለቱን ይበጥስ፥ የእግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ማንም ይዞ ሊያረጋጋው የሚችል አልነበረም። በመቃብሮቹና በተራራዎቹ መካከል ቀንና ሌሊት እየተዘዋወረ በመጮኸ ሰውነቱን በድንጋይ ይቆራርጥ ነበር። ይህም ሰው ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጦ ከፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት፤ በታላቅ ድምፅ ጮኾም፥ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ” አለው። ይህንንም ያለው፥ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎት ስለ ነበር ነው። ኢየሱስም “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። “ብዙዎች ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው፤” አለው፤ ከሀገር ውጭ እንዳያባርራቸው አጥብቆ ለመነው። በአቅራቢያውም በሚገኝ ኰረብታ ላይ ትልቅ የዐሣማ መንጋ ይሰማራ ነበርና፤ ኢየሱስን፥ “ወደ አሣማዎቹ እንድንገባ ስደደን፤” ብለው ለመኑት። እርሱም ፈቀደላቸው። ርኩሳን መናፍስቱም ወጥተው በዐሣማዎቹ ገቡ፤ ሁለት ሺህ ያህል ዐሣማዎችም በርግገው ከገደሉ አፋፍ ወደ ባሕሩ ተወረወሩ፤ በባሕሩ ውስጥም ሰጠሙ። እረኞቹ ሸሽተው ሄዱ፤ በከተማና በገጠርም አወሩ፤ ሕዝቡም የሆነውን ለማየት መጡ። ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ፥ የአጋንንት ሠራዊት አድረውበት የነበረው ሰው፥ ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት ተቀምጦ አዩት፤ ፍርሃትም አደረባቸው። ይህንን ያዩ ሰዎችም አጋንንት ለያዘው ሰው የሆነውንና በአሳማዎቹም የተደረገውን አወሩ። ከዚያም ሀገራቸውን ለቆ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ይለምኑት ጀመር። ኢየሱስም ወደ ጀልባዪቱ በሚገባበት ጊዜ፥ በአጋንንት ተይዞ የነበረው ሰው ከእርሱ ጋር አብሮት ለመሆን ለመነው። ኢየሱስ ግን አልፈቀደለትም፤ ይልቁን፥ “ወደ ቤትህ ወደ ዘመዶችህም ሂድ፤ ጌታም ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ምሕረት እንዳሳየህ ንገራቸው” አለው። እርሱም ሄደ፤ ኢየሱስም ያደረገለትን ነገር “ዐሥር ከተማ” በተባለው አገር በየስፍራው ያበስር ጀመር፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ።