ማርቆስ 3:7-21
ማርቆስ 3:7-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባህር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገ ሰምተው ብዙ ሰዎች ከይሁዳ ከኢየሩሳሌምም ከኤዶምያስም ከዮርዳኖስ ማዶም ከጢሮስና ከሲዶና ምድርም ወደ እርሱ መጡ። ሰዎቹም እንዳያጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ ስለዚህም ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እንዲዳስሱት ይወድቁበት ነበር። ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” እያሉ ጮኹ። እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው። ወደ ተራራም ወጣ፤ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ ዐሥራ ሁለት አደረገ፤ ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፤ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን። ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ዘመዶቹም ሰምተው “አበደ” ብለዋልና ሊይዙት ወጡ።
ማርቆስ 3:7-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላ የመጣ እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ የሚሠራውን ነገር የሰሙ ሰዎችም ከይሁዳ፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስ፣ በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አገር እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ ወደ እርሱ መጡ። የተሰበሰበውም ሕዝብ እንዳያጨናንቀው አነስተኛ የሆነ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ብዙዎችን ፈውሶ ስለ ነበር፣ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ ሊዳስሱት ይሽቀዳደሙ ነበር። ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ቍጥር ከፊቱ እየወደቁ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት ይጮኹ ነበር። እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጹ አጥብቆ ይገሥጻቸው ነበር። ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠራቸው፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ። ከርሱ ጋራ እንዲሆኑ፣ ለስብከትም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን ሾማቸው፤ ሐዋርያትም ብሎ ጠራቸው፤ አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤ ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖን፣ ቦአኔርጌስ ይኸውም፣ “የነጐድጓድ ልጆች” ብሎ የጠራው የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፤ እንድርያስ፣ ፊልጶስ፣ በርተሎሜዎስ፣ ማቴዎስ፣ ቶማስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣ ታዴዎስ፣ ቀነናዊው ስምዖን፣ እንዲሁም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ። ከዚያም ኢየሱስ ወደ አንድ ቤት ገባ፤ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪሳናቸው ድረስ ሕዝቡ እንደ ገና በብዛት ተሰበሰበ። ሁኔታውን የሰሙ ዘመዶቹም፣ “አእምሮውን ስቷል” በማለት ይዘውት ለመሄድ ወዳለበት መጡ።
ማርቆስ 3:7-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባህር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ እንዴት ትልቅ ነገርም እንዳደረገው ሰምተው ብዙ ሰዎች ከይሁዳ ከኢየሩሳሌምም ከኤዶምያስም ከዮርዳኖስ ማዶም ከጢሮስና ከሲዶና ምድርም ወደ እርሱ መጡ። ሰዎቹም እንዳያጋፉት ታንኳን ያቆዩለት ዘንድ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ ስለዚህም ሥቃይ ያለባቸው ሁሉ እንዲዳስሱት ይወድቁበት ነበር። ርኵሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው፦ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮኹ። እንዳይገልጡትም በጣም አዘዛቸው። ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው፥ ድውዮችንም ሊፈውሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለት አደረገ፤ ስምዖንንም ጴጥሮስ ብሎ ሰየመው፤ የዘብዴዎስንም ልጅ ያዕቆብን የያዕቆብንም ወንድም ዮሐንስን ቦአኔርጌስ ብሎ ሰየማቸው፥ የነጎድጓድ ልጆች ማለት ነው፤ እንድርያስንም ፊልጶስንም በርተሎሜውስንም ማቴዎስንም ቶማስንም የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብንም ታዴዎስንም ቀነናዊውንም ስምዖንን፥ አሳልፎ የሰጠውንም የአስቆሮቱን ይሁዳን። ወደ ቤትም መጡ፤ እንጀራም መብላት ስንኳ እስኪሳናቸው ድረስ እንደ ገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ዘመዶቹም ሰምተው፦ አበደ ብለዋልና ሊይዙት ወጡ።
ማርቆስ 3:7-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ገሊላ ባሕር ሄደ። ከገሊላና ከይሁዳ ብዙ ሰዎች ተከተሉት። ያደርግ የነበረውንም ነገር ሁሉ በሰሙ ጊዜ ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ እነርሱም ከገሊላ፥ ከይሁዳ፥ ከኢየሩሳሌም፥ ከኤዶምያስ፥ ከዮርዳኖስ ማዶ ካለው አገር፥ እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና ከተሞች የመጡ ነበሩ። ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሰዎች እንዳያጣብቡት ጀልባ አዘጋጅተው እንዲያቀርቡለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። ብዙ ሰዎችን ከበሽታ ፈውሷቸው ነበርና በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ በእጃቸው ሊነኩት ፈልገው፥ ያጨናንቁት ነበር። ርኩሳን መናፍስትም ሲያዩት በፊቱ እየተደፉ፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” እያሉ ይጮኹ ነበር። እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጡ በጥብቅ ገሠጻቸው። ኢየሱስ ወደ ተራራ በወጣ ጊዜ እነዚያን የፈለጋቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ እነርሱም ወደ እርሱ ቀረቡ። ከእርሱ ጋር እንዲሆኑ፥ ለማስተማርም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” ብሎ ሰየማቸው። አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የተመረጡትም ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት እነዚህ ናቸው፦ ጴጥሮስ ብሎ የሠየመው ስምዖን፥ ቦአኔርጌስ ወይም የነጐድጓድ ልጆች ብሎ የሠየማቸው፥ የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ፥ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ በርቶሎሜዎስ፥ ማቴዎስ፥ ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ተቀናቃኙ ስምዖን፥ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠውም አስቆሮታዊው ይሁዳ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤት ገባ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪያቅታቸው ድረስ እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። “ኢየሱስ አብዶአል” ሲባል በመስማታቸው ዘመዶቹ ሊይዙት ወደ እርሱ መጡ።
ማርቆስ 3:7-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ባሕር ፈቀቅ አለ፤ ከገሊላና ከይሁዳ የመጡም ብዙ ሰዎች ተከተሉት፤ ያደረገውን ነገር ሁሉ ሰምተው፥ ከኢየሩሳሌም፥ ከኤዶምያስ፥ ከዮርዳኖስ ማዶ፥ ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ መጡ። ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ እንዳያስጨንቁት ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው፤ ብዙ ሰዎችን አድኖ ነበርና፥ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ በእጃቸው ሊነኩት ፈልገው ያጨናንቁት ነበር። ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው፥ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” እያሉ ጮኹ። እርሱም ማንነቱን እንዳይገልጡ በጥብቅ ገሠጻቸው። ወደ ተራራም ወጣ፤ ራሱም የፈለጋቸውን ወደ እርሱ ጠራ፤ ወደ እርሱም ሄዱ። ከእርሱም ጋር እንዲሆኑና ለመስበክም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን መርጦ “ሐዋርያት” አላቸው። አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። የተመረጡት ዐሥራ ሁለቱም፦ ጴጥሮስ ብሎ የሰየመው ስምዖን፤ ቦአኔርጌስ፥ ማለትም የነጐድጓድ ልጆች ብሎ የሰየማቸው የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና የያዕቆብ ወንድም ዮሐንስን፤ እንድርያስ፥ ፊልጶስ፥ በርተሎሜውስ፥ ማቴዎስ፥ ቶማስ፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፥ ታዴዎስ፥ ቀነናዊው ስምዖን፥ እና አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ ናቸው። ከዚያም ወደ ቤት ገቡ፤ ምግብ መመገብ እንኳ እስኪያቅታቸው ድረስ እንደገና ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ። ዘመዶቹም “አእምሮውን ስቷል” ሲባል ሰምተው ሊይዙት መጡ።