ማርቆስ 15:6-15

ማርቆስ 15:6-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ጲላጦስ በየዓመቱ በአይሁድ ፋሲካ በዓል ጊዜ እንዲፈታላቸው ሰዎቹ የጠየቁትን አንድ እስረኛ ይለቅላቸው ነበር። በዚያን ጊዜ በመንግሥት ላይ ተነሣሥተው፥ ሰው በመግደል ወህኒ ቤት የገቡ ዐመፀኞች ነበሩ፤ ከነዚህም ዐመፀኞች አንዱ በርባን የሚባለው ሰው ነበር። ሕዝቡም ወደ ጲላጦስ ቀርበው የተለመደውን ምሕረት እንዲያደርግላቸው ጠየቁት። እርሱም “የአይሁድን ንጉሥ ፈትቼ እንድለቅላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው። ይህንንም ያለው የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ስለ ነበር ነው። የካህናት አለቆች ግን፥ “በእርሱ ፈንታ በርባን ይፈታልን፤” ብለው ጲላጦስን እንዲጠይቁ ሰዎቹን አነሣሡ። ጲላጦስም፦ “ታዲያ፥ ይህን የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላድርገው?” ሲል ሰዎቹን እንደገና ጠየቀ። እነርሱም “ስቀለው!” እያሉ እንደገና ጮኹ። ጲላጦስም “ለምን? ያደረገው በደል ምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም “ስቀለው!” እያሉ አብዝተው ጮኹ። ጲላጦስ ሰዎቹን ደስ ለማሰኘት ብሎ በርባንን ፈቶ ለቀቀላቸው፤ ኢየሱስን ግን አስገረፈውና እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።

ማርቆስ 15:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በበዓል ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን እስረኛ የመልቀቅ ልማድ ነበር። በዐመፃ ተነሣሥተው ነፍስ ከገደሉ ዐመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የሚባል አንድ ሰው ነበረ። ሕዝቡም መጥተው እንደተለመደው እንዲያደርግላቸው ጲላጦስን ለመኑት። ጲላጦስም፥ “የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው፤ ምክንያቱም የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ነበር። የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ምትክ እንዲፈታላቸው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሣሡ። ጲላጦስም እንደገና፥ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። እነርሱም እንደገና፥ “ስቀለው” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፥ “ለምን? ምን የፈጸመው ወንጀል አለ?” አላቸው። እነርሱ ግን፥ “ስቀለው” እያሉ የባሰ ጮኹ። ጲላጦስም ሕዝቡን ደስ ለማሰኘት ሲል በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።