ማርቆስ 14:53-61
ማርቆስ 14:53-61 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፤ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችም ሸንጎውን ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ አላገኙምም፤ ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፤ ምስክርነታቸው ግን አልተስማማም። ሰዎችም ተነሥተው “እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ፤ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ፤” ሲል ሰማነው፤ ብለው በሐሰት መሰከሩበት። ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተስማማም። ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ “አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው?” ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። እርሱ ግን ዝም አለ፤ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና “የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን?” አለው።
ማርቆስ 14:53-61 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፣ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከጠባቂዎቹ ጋራ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፣ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “ይህ፣ ‘የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ’ ሲል ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ፣ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፣ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድን ነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደ ገና፣ “የቡሩኩ ልጅ፣ ክርስቶስ አንተ ነህን?” ሲል ጠየቀው።
ማርቆስ 14:53-61 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችም ሸንጎውን ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤ ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም። ሰዎችም ተነሥተው፦ እኔ ይህን በእጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፈርሰዋለሁ በሦስት ቀንም ሌላውን በእጅ ያልተሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰማነው ብለው በሐሰት መሰከሩበት። ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም። ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ፦ አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው። እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና፦ የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው።
ማርቆስ 14:53-61 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስን ግን ወደ ካህናት አለቃው ቤት ወሰዱት፤ እዚያ የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና የሕግ መምህራን ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም እስከ የካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ይከተለው ነበር። እዚያም ከሎሌዎች ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና የሸንጎው አባሎች ሁሉ፥ ኢየሱስን ለማስገደል ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ግን አላገኙም። ብዙዎችም በሐሰት መስክረውበት ነበር፤ ሆኖም የምስክርነት ቃላቸው ሳይስማማ ቀረ። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “እኔ ይህን በሰው እጅ የተሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ ሌላ በሰው እጅ ያልተሠራ እሠራለሁ ብሎ ሲናገር ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ ምስክርነታቸው አልተስማማም። የካህናት አለቃውም በመካከላቸው ቆሞ፥ “ምንም አትመልስምን? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ የሚያቀርቡብህ ክስ ምንድን ነው?” ሲል ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ እንጂ ምንም መልስ አልሰጠም። የካህናት አለቃውም “የቡሩክ እግዚአብሔር ልጅ መሲሕ አንተ ነህን?” ሲል እንደገና ጠየቀው።
ማርቆስ 14:53-61 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፤ በዚያም የካህናት አለቆች፥ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ሁሉ ተሰበሰቡ። ጴጥሮስም ከሩቅ እየተከተለው፥ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ዘለቀ፤ በዚያም ተቀምጦ ከሎሌዎቹ ጋር እሳት ይሞቅ ነበር። የካህናት አለቆችና ሸንጎው በሙሉ ኢየሱስን ለመግደል ምስክር ፈለጉ፤ ነገር ግን ማግኘት አልቻሉም። ብዙዎች በሐሰት ቢመሰክሩበትም፥ ቃላቸው አንድ ሊሆን አልቻለም። አንዳንዶቹም ተነሥተው እንዲህ ሲሉ በሐሰት መሰከሩበት፤ “ይህ፥ የሰው እጅ የሠራውን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፥ በሦስት ቀን ሌላ የሰው እጅ ያልሠራውን እሠራለሁ ሲል ሰምተነዋል።” ይህም ሆኖ፥ እንኳ ምስክርነታቸው አንድ አልሆነም። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ በፊታቸው በመቆም፥ “እነዚህ በአንተ ላይ የሚመሰክሩት ምንድነው? ለምን አትመልስም?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም። ሊቀ ካህናቱም እንደገና፥ የቡሩኩ ልጅ፥ ክርስቶስ አንተ ነህን? ሲል ጠየቀው።