ማርቆስ 13:14-37 - Compare All Versions
ማርቆስ 13:14-37 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
“ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ፤ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፤ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዐይነት ይሆናልና። ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ። በዚያን ጊዜም ማንም ‘እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፤’ ወይም ‘እነሆ፥ ከዚያ አለ፤’ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፤ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። “በነዚያ ቀኖች ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያትም ኀይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኀይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል፤ ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። “ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን አያልፍም። “ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፤ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ። እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ። ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።”
ማርቆስ 13:14-37 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
“ ‘የጥፋት ርኩሰት’ ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤ በዕርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በእነዚያ ቀናት፣ እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ እስከ አሁን ድረስ፣ ከዚህም በኋላ ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል። “ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ሥጋ ለባሽ ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሯል። በዚያ ጊዜ ማንም፣ ‘እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው!’ ቢላችሁ ወይም፣ ‘እነሆ፤ እዚያ ነው!’ ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፣ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፣ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ። ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ። “በዚያ ጊዜ፣ ከመከራው በኋላ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፣ “ ‘ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ።’ “በዚያ ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል። እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል። “ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፣ በደጅም እንደ ሆነ ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤ ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም። “ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም። ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን ስለማታውቁ ተጠንቀቁ! ትጉ! ጸልዩም! ይህም ቤቱን ለባሮቹ ትቶ፣ እያንዳንዱን አገልጋይ በየሥራ ድርሻው ላይ አሰማርቶ፣ በረኛው ነቅቶ እንዲጠብቅ አዝዞ የሄደውን ሰው ይመስላል። “እንግዲህ የቤቱ ባለቤት በምሽት ወይም በውድቅት፣ በዶሮ ጩኸት ወይም ጎሕ ሲቀድድ እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ፤ ለእናንተ የምነግራችሁን ለሰው ሁሉ እናገራለሁ፤ ‘ተግታችሁ ጠብቁ!’ ”
ማርቆስ 13:14-37 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥ በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥ በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው። ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና። ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ። በዚያን ጊዜም ማንም፦ እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም፦ እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤ ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ። እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ። በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል። ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም። ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም። ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም። ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም። ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፥ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ። እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ። ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።
ማርቆስ 13:14-37 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
“ደግሞ መገኘት በማይገባው ስፍራ የሚያረክሰውን አጸያፊ ነገር ታያላችሁ፤ ይህንንም አንባቢው ያስተውል፤ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ምድር ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ። በቤት ጣራ ላይ ያለ ወደ ቤቱ ወርዶ ከቤቱ አንዳች ነገር ለመውሰድ ጊዜ አያጥፋ፤ በእርሻም ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ ወደ ኋላው አይመለስ። በዚያን ጊዜ ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ እመጫቶች ወዮላቸው! ይህ ሁሉ በክረምት ጊዜ እንዳይሆን ጸልዩ። በዚያን ወራት እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ መከራ ይሆናል፤ ወደ ፊትም እሱን የሚመስል ጭንቀት ከቶ አይደርስም። ጌታ እነዚያን ቀኖች ባያሳጥርማ ኖሮ ማንም መዳን ባልቻለም ነበር፤ ነገር ግን ለተመረጡት ሰዎች ሲባል እነዚያ ቀኖች ያጥራሉ። “እንግዲህ ማንም ቢሆን ‘መሲሕ ይኸው እዚህ ነው!’ ወይም ‘ያው እዚያ ነው!’ ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኞች መሲሖችና ሐሰተኞች ነቢያት ይመጣሉ፤ እነርሱ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ለማሳሳት ተአምራትና ድንቅ ነገሮችን ያደርጋሉ። ሁሉን ነገር አስቀድሜ ነግሬአችኋለሁና እንግዲህ ተጠንቀቁ! “በዚያን ጊዜ፥ ከዚያ ሁሉ መከራ በኋላ፥ ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ በሰማይ ያሉ ኀይሎችም ይናወጣሉ። ከዚያም በኋላ የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ክብር በደመና ሲመጣ ይታያል፤ መላእክቱንም ይልካል፤ እነርሱ በአራቱም አቅጣጫ ሄደው ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የሚገኙትን፥ ለእርሱ የተመረጡትን ሰዎች ይሰበስባሉ። “የበለስ ዛፍ ምሳሌ ትምህርት ይሁናችሁ፤ ቅርንጫፎችዋ ሲያቈጠቊጡና ቅጠሎችዋም ሲለመልሙ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ። እንዲሁም እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የሰው ልጅ የሚመጣበት ጊዜ በደጅ እንደ ቀረበ ዕወቁ፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ ይህ ትውልድ ከማለፉ በፊት ይህ ሁሉ ይፈጸማል። ሰማይና ምድር ያልፋሉ፤ ቃሌ ግን ጸንቶ ይኖራል። “ነገር ግን ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር ማንም የሚያውቅ የለም፤ የሰማይ መላእክትም አያውቁም፤ ወልድም አያውቅም። ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ። ይህም፥ ቤቱን ትቶ ወደ ሩቅ አገር የሄደውን ሰው ይመስላል፤ እርሱም እያንዳንዱን አገልጋይ በልዩ ልዩ የሥራ ኀላፊነት ላይ መደበ፤ ዘበኛውንም ተግቶ እንዲጠብቅ አዘዘው። ስለዚህ የቤቱ ጌታ የሚመጣበትን ጊዜ አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ምናልባትም ወደ ማታ፥ ወይም በእኩለ ሌሊት፥ ወይም ዶሮ ሲጮኽ፥ ወይም ጠዋት በማለዳ ይመጣ ይሆናል፤ በድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ትጉ። “ለእናንተ እንደ ነገርኳችሁ ለሌሎችም ሁሉ ትጉ! እላለሁ።”
ማርቆስ 13:14-37 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
የጥፋት ርኩሰት ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤ በእርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ፥ እንዲሁ ደግሞም ወደ ፊት አቻ የሌለው ታላቅ መከራ ይሆናልና። ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሯል። በዚያን ጊዜ ማንም፥ “እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው?” ቢላችሁ ወይም፥ “እነሆ፤ እዚያ ነው” ቢላችሁ አትመኑ። ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፥ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፥ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ። ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ። በዚያን ጊዜ፥ ከመከራው በኋላ ፀሓይ ትጨልማለች፥ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኋይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል። እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፥ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል። ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፥ ቅጠሏ ሲያቆጠቁጥ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፥ በደጅም እንደሆነ ዕወቁ። እውነት እላችኋለሁ፥ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤ ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም። ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያችም ሰዓት ከአብ በቀር፥ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፥ ወልድም ቢሆን፥ ማንም አያውቅም። ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፥ ጸልዩም። ይህም ቤቱን ለአገልጋዮቹ ትቶ፥ እያንዳንዱን አገልጋይ በየሥራ ድርሻው ላይ አሰማርቶ፥ በረኛው ነቅቶ እንዲጠብቅ አዝዞ የሄደውን ሰው ይመስላል። እንግዲህ የቤቱ ባለቤት በምሽት ወይም በውድቅት፥ በዶሮ ጩኸት ወይም ጎሕ ሲቀድ እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤ ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ለእናንተ የምነግራችሁን ለሰው ሁሉ እናገራለሁ፤ ተግታችሁ ጠብቁ።