ማርቆስ 12:38-44

ማርቆስ 12:38-44 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ሲያስተምር እንዲህ አለ፦ “ረጃጅም ልብስ ለብሰው ወዲያና ወዲህ መዞርን፥ በገበያም የክብር ሰላምታ መቀበልን ከሚወዱ ከሕግ መምህራን ተጠንቀቁ፤ እነርሱ በምኲራብ የክብር ወንበርን፥ በግብዣም የክብር ስፍራን ለማግኘት ይመርጣሉ። ለታይታ በሚያቀርቡት ረጅም ጸሎት እያመካኙ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ቤት ይበዘብዛሉ፤ ስለዚህ እነርሱ የባሰ ፍርድ ይደርስባቸዋል።” ኢየሱስ በምጽዋት መቀበያ ሣጥን ፊት ለፊት ተቀምጦ ሳለ ሕዝቡ በሣጥኑ ውስጥ ገንዘብ ሲጨምሩ ያይ ነበር፤ ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ ይጨምሩ ነበር፤ አንዲት ድኻ መበለትም መጥታ ሁለት ሳንቲም የሚያኽል የናስ ገንዘብ በዚያ ውስጥ ጨመረች። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ በሣጥኑ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሰዎች ሁሉ አብልጣ የጨመረች ይህች ድኻ መበለት ናት። ሌሎቹ ሁሉ የሰጡት ካላቸው ሀብት የተረፋቸውን ነው፤ እርስዋ ግን ድኻ ሆና ሳለች ምንም ሳታስቀር ያላትን ሁሉ ሰጠች።”