ማርቆስ 12:28-44

ማርቆስ 12:28-44 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ “ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ ‘እስራኤል ሆይ! ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኀይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ፤’ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤’ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።” ጻፊውም “መልካም ነው፤ መምህር ሆይ! ‘አንድ ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ የለም፤’ ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኀይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው፡” አለው። ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰ አይቶ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም፤” አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ “ጻፎች ‘ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው፤’ እንዴት ይላሉ? ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ‘ጌታ ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ።’ ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር። ሲያስተምርም እንዲህ አለ “ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን፥ በገበያም ሰላምታን፥ በምኵራብም የከበሬታን ወንበር፥ በግብዣም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ የመበለቶችን ቤት የሚበሉ፤ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።” ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤ አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ “እውነት እላችኋለሁ፤ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች፤” አላቸው።

ማርቆስ 12:28-44 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፣ “ለመሆኑ ከትእዛዞች ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን፣ ጌታ አንድ ነው። አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።” ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እግዚአብሔር አንድ መሆኑን፣ ከርሱም ሌላ አለመኖሩን እውነት ተናግረሃል፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።” ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ “ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ? ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣ “ጠላቶችህን ከእግሮችህ በታች እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው። ይላል፤’ ታዲያ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ካለው፣ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር። ሲያስተምርም እንዲህ አለ፤ ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ “ዘርፋፋ ቀሚስ ለብሰው መዞርን፣ በገበያ ስፍራ የአክብሮት ሰላምታን፣ በምኵራብ የከበሬታ መቀመጫን፣ በግብዣ ቦታም የክብር ስፍራን ይፈልጋሉና፤ በረዥም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቍታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።” ኢየሱስ በመባ መክተቻው ሣጥን ትይዩ ተቀምጦ፣ ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ሲያስገቡ ይመለከት ነበር። ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ አስገቡ፤ አንዲት ምስኪን መበለት ግን ከአንድ ሳንቲም የማይበልጡ ሁለት የናስ ሳንቲሞች አስገባች። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህች ድኻ መበለት ሙዳየ መባ ውስጥ ሌሎቹ ከጨመሩት የበለጠ አስገባች። እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን ከጕድለቷ ያላትን፣ መኖሪያዋን ሁሉ ሰጠች።”

ማርቆስ 12:28-44 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ፦ ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። ጻፊውም፦ መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው አለው። ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ፦ አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ፦ ጻፎች ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ? ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር። ሲያስተምርም እንዲህ አለ፦ ረጃጅም ልብስ ለብሰው መዞርን፥ በገበያም ሰላምታን፥ በምኵራብም የከበሬታን ወንበር፥ በግብርም የከበሬታን ስፍራ ከሚወዱ ከጻፎች ተጠበቁ፤ የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ። ኢየሱስም በመዝገብ አንጻር ተቀምጦ ሕዝቡ በመዝገብ ውስጥ ገንዘብ እንዴት እንዲጥሉ ያይ ነበር፤ ብዙ ባለ ጠጎችም ብዙ ይጥሉ ነበር፤ አንዲትም ድሀ መበለት መጥታ አንድ ሳንቲም የሚያህሉ ሁለት ናስ ጣለች። ደቀ መዛሙርቱንም ጠርቶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ በመዝገብ ውስጥ ከሚጥሉት ሁሉ ይልቅ ይህች ድሀ መበለት አብልጣ ጣለች፤ ሁሉ ከትርፋቸው ጥለዋልና፥ ይህች ግን ከጕድለትዋ የነበራትን ሁሉ ትዳርዋን ሁሉ ጣለች አላቸው።

ማርቆስ 12:28-44 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከሕግ መምህራን አንዱ ክርክራቸውን ይሰማ ነበር፤ ኢየሱስ በመልካም ሁኔታ እንደ መለሰላቸው የሕግ መምህሩ አስተዋለ፤ ወደ ኢየሱስ ቀርቦም “ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ፥ ‘እስራኤል ሆይ! ስማ፤ እግዚአብሔር አምላካችን አንድ አምላክ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህ፥ በፍጹም ኀይልህ ውደድ፤’ የሚል ነው። ይህንንም የሚመስል ሁለተኛው ትእዛዝ፥ ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ የሚል ነው። ከነዚህም ከሁለቱ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።” የሕግ መምህሩም ኢየሱስን እንዲህ አለው፦ “መምህር ሆይ! ‘እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለህ የተናገርከው ልክ ነው፤ ስለዚህ ሰው በፍጹም ልቡ፥ [በፍጹም ነፍሱ፥] በፍጹም ሐሳቡ፥ በፍጹም ኀይሉ እግዚአብሔርን መውደድ ይገባዋል፤ እንዲሁም ጐረቤትን እንደ ራሱ አድርጎ መውደድ ይገባዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከማቅረብ ይልቅ እነዚህን ሁለቱን ትእዛዞች መጠበቅ ይበልጣል።” ኢየሱስም የሕግ መምህሩ በጥበብና በማስተዋል እንደ መለሰ አይቶ፥ “አንተስ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም፤” አለው። ከዚህ በኋላ ለኢየሱስ ጥያቄ ሊያቀርብለት የደፈረ ማንም የለም። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር እንዲህ ብሎ ጠየቀ፤ “የሕግ መምህራን ‘መሲሕ የዳዊት ልጅ ነው፤’ ስለምን ይላሉ? ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ፥ ‘እግዚአብሔር ለጌታዬ (ለመሲሑ)፥ ጠላቶችህን በእግርህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ፤’ ብሎታል። ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ብሎ ከጠራው ታዲያ፥ መሲሕ ለዳዊት እንዴት ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር። ኢየሱስ ሲያስተምር እንዲህ አለ፦ “ረጃጅም ልብስ ለብሰው ወዲያና ወዲህ መዞርን፥ በገበያም የክብር ሰላምታ መቀበልን ከሚወዱ ከሕግ መምህራን ተጠንቀቁ፤ እነርሱ በምኲራብ የክብር ወንበርን፥ በግብዣም የክብር ስፍራን ለማግኘት ይመርጣሉ። ለታይታ በሚያቀርቡት ረጅም ጸሎት እያመካኙ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ቤት ይበዘብዛሉ፤ ስለዚህ እነርሱ የባሰ ፍርድ ይደርስባቸዋል።” ኢየሱስ በምጽዋት መቀበያ ሣጥን ፊት ለፊት ተቀምጦ ሳለ ሕዝቡ በሣጥኑ ውስጥ ገንዘብ ሲጨምሩ ያይ ነበር፤ ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ ይጨምሩ ነበር፤ አንዲት ድኻ መበለትም መጥታ ሁለት ሳንቲም የሚያኽል የናስ ገንዘብ በዚያ ውስጥ ጨመረች። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ በሣጥኑ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሰዎች ሁሉ አብልጣ የጨመረች ይህች ድኻ መበለት ናት። ሌሎቹ ሁሉ የሰጡት ካላቸው ሀብት የተረፋቸውን ነው፤ እርስዋ ግን ድኻ ሆና ሳለች ምንም ሳታስቀር ያላትን ሁሉ ሰጠች።”

ማርቆስ 12:28-44 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፥ “ለመሆኑ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፥ እስራኤል ሆይ! ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኋይልህ ውደድ።” ሁለተኛውም ይህ ነው፤ “ጐረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።” ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም። ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፥ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም አእምሮህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኋይልህ መውደድ፥ እንዲሁም ጐረቤትህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።” ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፥ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ? ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፥ ጌታ ጌታዬን፥ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው፥ ይላል። “ታዲያ ዳዊት ራሱ ጌታ፥ ካለው፤ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?”። ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር። በሚያስተምርበትም ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ የተንዘረፈፈ ቀሚስ ለብሰው መዞርን ይወዳሉ፤ በየአደባባዩም የአክብሮት ሰላምታ ይሻሉ፤ በምኵራብ ከፍተኛውን ወንበር፥ በግብዣም ቦታ የከበሬታን ስፍራ ይፈልጋሉ፤ በረጅም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቁታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።” ኢየሱስ በገንዘብ ማስቀመጫው አንጻር ተቀምጦ ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ገንዘብ ማስቀመጫ ሳጥን ሲያስገቡ ይመለከት ነበር። ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ አስገቡ፤ አንዲት ድኻ መበለትም መጥታ ሁለት ሳንቲም የሚያክል የናስ ገንዘብ ጨመረች። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፥ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህቺ ድኻ መበለት ሳጥኑ ውስጥ ከጣሉት ከሌሎቹ የበለጠ አስገባች። እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን በድህነት ዐቅሟ ያላትን ሁሉ አውጥታ ለመኖሪያ የሚሆናትን እንዳለ ሰጠች።”