ማርቆስ 12:28-37

ማርቆስ 12:28-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ “ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ ‘እስራኤል ሆይ! ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኀይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ፤’ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤’ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።” ጻፊውም “መልካም ነው፤ መምህር ሆይ! ‘አንድ ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ የለም፤’ ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኀይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው፡” አለው። ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰ አይቶ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም፤” አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ “ጻፎች ‘ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው፤’ እንዴት ይላሉ? ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ‘ጌታ ጌታዬን ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ።’ ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር።

ማርቆስ 12:28-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፣ “ለመሆኑ ከትእዛዞች ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን፣ ጌታ አንድ ነው። አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’ ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።” ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እግዚአብሔር አንድ መሆኑን፣ ከርሱም ሌላ አለመኖሩን እውነት ተናግረሃል፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።” ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ “ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ? ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣ “ጠላቶችህን ከእግሮችህ በታች እስከማደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው። ይላል፤’ ታዲያ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ካለው፣ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር።

ማርቆስ 12:28-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ፦ ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፦ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥ አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም። ጻፊውም፦ መልካም ነው፥ መምህር ሆይ፤ አንድ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ የለም ብለህ በእውነት ተናገርህ፤ በፍጹም ልብ በፍጹም አእምሮም በፍጹም ነፍስም በፍጹም ኃይልም እርሱን መውደድ፥ ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው አለው። ኢየሱስም በአእምሮ እንደ መለሰ አይቶ፦ አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም አለው። ከዚህም በኋላ ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም። ኢየሱስም በመቅደስ ሲያስተምር መልሶ እንዲህ አለ፦ ጻፎች ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው እንዴት ይላሉ? ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው አለ። ዳዊትም ራሱ ጌታ አለው፤ እንዴትስ ልጁ ይሆናል? ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር።

ማርቆስ 12:28-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከሕግ መምህራን አንዱ ክርክራቸውን ይሰማ ነበር፤ ኢየሱስ በመልካም ሁኔታ እንደ መለሰላቸው የሕግ መምህሩ አስተዋለ፤ ወደ ኢየሱስ ቀርቦም “ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ፥ ‘እስራኤል ሆይ! ስማ፤ እግዚአብሔር አምላካችን አንድ አምላክ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህ፥ በፍጹም ኀይልህ ውደድ፤’ የሚል ነው። ይህንንም የሚመስል ሁለተኛው ትእዛዝ፥ ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ የሚል ነው። ከነዚህም ከሁለቱ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።” የሕግ መምህሩም ኢየሱስን እንዲህ አለው፦ “መምህር ሆይ! ‘እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ከእርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለህ የተናገርከው ልክ ነው፤ ስለዚህ ሰው በፍጹም ልቡ፥ [በፍጹም ነፍሱ፥] በፍጹም ሐሳቡ፥ በፍጹም ኀይሉ እግዚአብሔርን መውደድ ይገባዋል፤ እንዲሁም ጐረቤትን እንደ ራሱ አድርጎ መውደድ ይገባዋል፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከማቅረብ ይልቅ እነዚህን ሁለቱን ትእዛዞች መጠበቅ ይበልጣል።” ኢየሱስም የሕግ መምህሩ በጥበብና በማስተዋል እንደ መለሰ አይቶ፥ “አንተስ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም፤” አለው። ከዚህ በኋላ ለኢየሱስ ጥያቄ ሊያቀርብለት የደፈረ ማንም የለም። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሲያስተምር እንዲህ ብሎ ጠየቀ፤ “የሕግ መምህራን ‘መሲሕ የዳዊት ልጅ ነው፤’ ስለምን ይላሉ? ዳዊት ራሱ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ፥ ‘እግዚአብሔር ለጌታዬ (ለመሲሑ)፥ ጠላቶችህን በእግርህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ፤’ ብሎታል። ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ብሎ ከጠራው ታዲያ፥ መሲሕ ለዳዊት እንዴት ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰሙት ነበር።

ማርቆስ 12:28-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፥ “ለመሆኑ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፥ “ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፥ እስራኤል ሆይ! ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤ አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኋይልህ ውደድ።” ሁለተኛውም ይህ ነው፤ “ጐረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።” ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም። ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፥ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤ እርሱን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም አእምሮህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ኋይልህ መውደድ፥ እንዲሁም ጐረቤትህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።” ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፥ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ? ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፥ ጌታ ጌታዬን፥ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው፥ ይላል። “ታዲያ ዳዊት ራሱ ጌታ፥ ካለው፤ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?”። ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር።