ማርቆስ 11:12-21

ማርቆስ 11:12-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በማግሥቱም ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ። ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። መልሶም “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ፤” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። ወደ መቅደስም ገብቶ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያወጣ ጀመር፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጭዎችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ ዕቃም ተሸክሞ ማንም በመቅደስ ሊያልፍ አልፈቀደም። አስተማራቸውም “‘ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች፤’ ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት፤” አላቸው። የካህናት አለቆችም ጻፎችም ሰምተው፥ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ይገረሙ ስለ ነበር ይፈሩት ነበርና እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ፈለጉ። ማታ ማታም ከከተማ ወደ ውጭ ይወጣ ነበር። ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት። ጴጥሮስም ትዝ ብሎት “መምህር ሆይ! እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች፤” አለው።

ማርቆስ 11:12-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ። እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ከዚያም ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤ ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ። ሲያስተምራቸውም፣ “ ‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት!’” አላቸው። የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና። በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ። በማግስቱም ጧት በመንገድ ሲያልፉ፣ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ። ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምሃት በለስ ደርቃለች!” አለው።

ማርቆስ 11:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በማግሥቱም ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ። ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፥ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። መልሶም፦ ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ አላት። ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። ወደ መቅደስም ገብቶ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያወጣ ጀመር፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጭዎችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ ዕቃም ተሸክሞ ማንም በመቅደስ ሊያልፍ አልፈቀደም። አስተማራቸውም፦ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። የካህናት አለቆችም ጻፎችም ሰምተው፥ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ይገረሙ ስለ ነበር ይፈሩት ነበርና እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ፈለጉ። ማታ ማታም ከከተማ ወደ ውጭ ይወጣ ነበር። ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት። ጴጥሮስም ትዝ ብሎት፦ መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው።

ማርቆስ 11:12-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በማግስቱም ከቢታንያ ሲመለሱ ኢየሱስ ተራበ። ቅጠልዋ የለመለመ የበለስ ዛፍም በሩቅ አይቶ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደ ሆነ በማለት ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ወደ እርስዋ በቀረበ ጊዜ በለስ የሚያፈራበት ወራት ስላልነበረ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ስለዚህ ኢየሱስ የበለስዋን ዛፍ፥ “ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ!” አላት። ይህንንም ሲናገር ደቀ መዛሙርቱ ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌም በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በውስጡ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ያስወጣ ጀመር፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ ማንም ሰው ምንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ግቢ ውስጥ እንዲተላለፍ አልፈቀደም። እንዲህም ሲል አስተማራቸው፤ “ ‘ቤቴ ለሕዝብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል!’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት።” የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ይህን ሲናገር ሰሙት፤ ሕዝቡም ሁሉ በትምህርቱ ይደነቁ ስለ ነበር ፈሩት፤ ስለዚህ እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ዘዴ ይፈልጉ ነበር። በመሸም ጊዜ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከከተማ ወጡ። በማግስቱ ማለዳ በመንገድ ሲያልፉ የበለሲቱ ዛፍ ከነስርዋ ደርቃ አዩአት። ጴጥሮስም ነገሩ ትዝ ብሎት ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ! እነሆ፥ የረገምሃት ዛፍ ደርቃለች” አለው።

ማርቆስ 11:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በማግሥቱ ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ። እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ከዚያም ዛፏን፥ “ከአሁን ጀምሮ ለዘለዓለም ማንም ፍሬ ከአንቺ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ። ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፥ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤ ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ። ሲያስተምራቸውም፥ “ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል፥ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን የሌቦች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው። የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፥ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና። በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ። በማግስቱ ጠዋት በመንገድ ሲያልፉ፥ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ። ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፥ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምካት በለስ ደርቃለች” አለው።