ማርቆስ 10:1-12

ማርቆስ 10:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚያም ተነሥቶ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አገር መጣ፤ ደግሞም ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ እንደ ልማዱም ደግሞ ያስተምራቸው ነበር። ፈሪሳውያንም ቀርበው “ሰው ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። እርሱ ግን መልሶ “ሙሴ ምን አዘዛችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ሙሴስ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቀደ፤” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው “ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ይህችን ትእዛዝ ጻፈላችሁ። ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።” በቤትም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር ጠየቁት። እርሱም “ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤ እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች፤” አላቸው።

ማርቆስ 10:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደ፤ ሕዝቡም እንደ ገና በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከዚህ ቀደም ያደርገው እንደ ነበረውም አስተማራቸው። አንዳንድ ፈሪሳውያንም መጥተው፣ “አንድ ባል ሚስቱን እንዲፈታ ተፈቅዷልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። እርሱም መልሶ፣ “ሙሴ ምን ብሎ አዘዛችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሙሴማ የፍችውን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷል” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና በመሆኑ ነው። ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ‘ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።’ ‘ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋራ ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።” እንደ ገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህንኑ አንሥተው ጠየቁት። እርሱም፣ “ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ በርሷ ላይ ያመነዝራል። እርሷም ባሏን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው።

ማርቆስ 10:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚያም ተነሥቶ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ ደግሞም ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ እንደ ልማዱም ደግሞ ያስተምራቸው ነበር። ፈሪሳውያንም ቀርበው፦ ሰው ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። እርሱ ግን መልሶ፦ ሙሴ ምን አዘዛችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ሙሴስ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቀደ አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ይህችን ትእዛዝ ጻፈላችሁ። ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። በቤትም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር ጠየቁት። እርሱም፦ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ በእርስዋ ላይ ያመነዝራል፤ እርስዋም ባልዋን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች አላቸው።

ማርቆስ 10:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ፥ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ በኩል አድርጎ ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ። እጅግ ብዙ ሰዎችም እንደገና ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ እርሱም እንደ ልማዱ ያስተምራቸው ነበር። ከፈሪሳውያንም ጥቂቶቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ሊፈትኑትም ፈልገው፦ “ሰው ሚስቱን እንዲፈታ በሕግ ተፈቅዶለታልን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም “ሙሴ ስለዚህ ነገር ምን አዘዛችሁ?” አላቸው። እነርሱም “ሙሴማ የፍችዋን የምስክር ወረቀት ሰጥቶ እንዲፈታት ፈቅዶአል፤” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሙሴስ ይህን ትእዛዝ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንድኖ ስለማትሰሙ ነው፤ ነገር ግን ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ ‘እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ ስለዚህ ሰው አባትና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ፤’ ከዚያም ወዲያ ሁለት መሆናቸው ቀርቶ አንድ ይሆናሉ። እንግዲህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።” ወደ ቤት በተመለሱ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ጉዳይ እንደገና ኢየሱስን ጠየቁት፤ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሚስቱን ፈቶ ሌላ ሴት የሚያገባ በሚስቱ ላይ አመንዝሮአል፤ እንዲሁም ባልዋን ፈታ ሌላ ወንድ የምታገባ ሴት አመንዝራ ሆናለች ማለት ነው።”

ማርቆስ 10:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ይሁዳ አገርና በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው አካባቢ ሄደ፤ ሕዝቡም እንደገና በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከዚህ ቀደም ያደርገው እንደ ነበረውም አስተማራቸው። አንዳንድ ፈሪሳውያንም መጥተው፥ “ሰው ሚስቱን መፍታት ይገባዋልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት። እርሱም መልሶ፥ “ሙሴ ምን ብሎ አዘዛችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሙሴማ የፍች ወረቀት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷአል” አሉ። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና በመሆኑ ነው። ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ማንም አይለየውም።” እንደገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፥ ደቀመዛሙርቱ ይህንኑ አንሥተው ጠየቁት። እርሱም፥ “ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ በእርሷ ላይ ያመነዝራል፤ እርሷም ባሏን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው።