ማቴዎስ 9:18-26
ማቴዎስ 9:18-26 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህንም ሲነግራቸው አንድ መኰንን መጥቶ “ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች፤” እያለ ሰገደለት። ኢየሱስም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው። እነሆም ከዐሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ በልብዋ “ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ፤” ትል ነበረችና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና “ልጄ ሆይ! አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤” አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች። ኢየሱስም ወደ መኰንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ “ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ፤” አላቸው። በጣምም ሳቁበት። ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ ብላቴናይቱም ተነሣች። ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ።
ማቴዎስ 9:18-26 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ሰዎቹን በማናገር ላይ ሳለ፣ አንድ የምኵራብ አለቃ መጥቶ ከፊቱ ተደፍቶ፣ “ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” አለው። ኢየሱስም ተነሥቶ ዐብሮት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ከዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት ከበስተኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ነካች። እርሷም በልቧ፣ “የልብሱን ጫፍ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” ብላ ነበር። ኢየሱስም ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ሴቲቱን አያትና፣ “አይዞሽ፣ ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴቲቱም ወዲያውኑ ተፈወሰች። ኢየሱስ ወደ ሹሙ ቤት እንደ ደረሰ እንቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፣ “ዞር በሉ፤ ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው፤ እነርሱ ግን ሣቁበት። ሕዝቡም ከወጣ በኋላ ወደ ውስጥ ገብቶ እጇን ያዘ፤ ብላቴናዪቱም ተነሥታ ቆመች። ወሬውም በአካባቢው ሁሉ ተሠራጨ።
ማቴዎስ 9:18-26 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህንም ሲነግራቸው፥ አንድ መኵኦንን መጥቶ፦ ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች እያለ ሰገደለት። ኢየሱስም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው። እነሆም፥ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ በልብዋ፦ ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ፥ እድናለሁ ትል ነበረችና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና፦ ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች። ኢየሱስም ወደ መኵኦንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፦ ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ አላቸው። በጣምም ሳቁበት። ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፥ ብላቴናይቱም ተነሣች። ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ።
ማቴዎስ 9:18-26 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ይህን ሲነግራቸው ሳለ፥ አንድ የምኲራብ አለቃ ወደ እርሱ መጣ፤ በግንባሩም በኢየሱስ ፊት ተደፍቶ፥ “እነሆ፥ ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ ነገር ግን አንተ መጥተህ እጅህን ብትጭንባት ትድናለች” አለው። ኢየሱስም ተነሣና ሰውየውን ተከትሎ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም አብረው ሄዱ። እነሆ፥ ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም እየመታት ትሠቃይ የነበረች አንዲት ሴት፥ በዚያን ጊዜ ከኢየሱስ በስተኋላ መጥታ የልብሱን ጫፍ በእጅዋ ነካች። ይህንንም ያደረገችው “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ በልብዋ አስባ ስለ ነበር ነው። ኢየሱስም መለስ ብሎ አያትና “አይዞሽ ልጄ ሆይ! እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴትዮዋም ወዲያውኑ ዳነች። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ምኲራብ አለቃው ቤት በደረሰ ጊዜ የሐዘን እምቢልታ ነፊዎችንና እየተራወጡ በመጮኽ የሚያለቅሱትን ሰዎች አየ። እርሱም “ሁላችሁም ከዚህ ውጡ! ልጅትዋ አንቀላፍታለች እንጂ አልሞተችም!” አላቸው። እነርሱ ግን በማፌዝ ሳቁበት። ሰዎቹም ከወጡ በኋላ፥ ኢየሱስ ልጅትዋ ወደምትገኝበት ክፍል ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ እርሷም ተነሣች። የዚህም ነገር ዝና በዚያ አገር ሁሉ ተሰማ።
ማቴዎስ 9:18-26 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህንም ሲነግራቸው ሳለ እነሆ አንድ ገዢ መጥቶ እየሰገደ “ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች፤” አለው። ኢየሱስም ተነሥቶ ተከተለው፥ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። እነሆ ለዐሥራ ሁለት ዓመታት ደም የሚፈስሳት ሴት ከኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ በልብዋ “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ፤” ብላ ታስብ ነበርና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና “ልጄ ሆይ! አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤” አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ኢየሱስም ወደ ገዢው ቤት በደረሰ ጊዜ፥ አስለቃሾችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፥ “ልጅቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ዞር በሉ፤” አላቸው። እነርሱ ግን ሳቁበት። ነገር ግን ሕዝቡን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ ልጅቱም ተነሣች። የዚህም ወሬ ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ።