ማቴዎስ 9:1-34
ማቴዎስ 9:1-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በታንኳም ገብቶ ተሻገረና ወደ ገዛ ከተማው መጣ። እነሆም፥ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “አንተ ልጅ! አይዞህ፤ ኀጢአትህ ተሰረየችልህ፤” አለው። እነሆም ከጻፎቹ አንዳንዶቹ በልባቸው “ይህስ ይሳደባል፤” አሉ። ኢየሱስም አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ “ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ? ‘ኀጢአትህ ተሰረየችልህ’ ከማለት ወይስ ‘ተነሣና ሂድ’ ከማለት ማናቸው ይቀላል? ነገር ግን በምድር ላይ ኀጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤” በዚያን ጊዜ ሽባውን “ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም አይተው ተደነቁ፤ ለሰውም እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጠ እግዚአብሔርን አከበሩ። ኢየሱስም ከዚያ አልፎ በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው አየና “ተከተለኝ” አለው። ተነሥቶም ተከተለው። በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኀጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኀጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል?” አሉአቸው። ኢየሱስም ሰምቶ “ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤነኞች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ነገር ግን ሄዳችሁ ‘ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም፤’ ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ፤ ኀጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና፤” አላቸው። በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ የምንጦመው፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፤ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ። በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳም አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈሳል፤ አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፤ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።” ይህንም ሲነግራቸው አንድ መኰንን መጥቶ “ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች፤” እያለ ሰገደለት። ኢየሱስም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው። እነሆም ከዐሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ በልብዋ “ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ እድናለሁ፤” ትል ነበረችና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና “ልጄ ሆይ! አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤” አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች። ኢየሱስም ወደ መኰንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ “ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ፤” አላቸው። በጣምም ሳቁበት። ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ ብላቴናይቱም ተነሣች። ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ። ኢየሱስም ከዚያ ሲያልፍ ሁለት ዕውሮች “የዳዊት ልጅ ሆይ! ማረን፤” ብለው እየጮሁ ተከተሉት። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ኢየሱስም “ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን?” አላቸው። “አዎን፥ ጌታ ሆይ!” አሉት። በዚያን ጊዜ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ፤” ብሎ ዐይኖቻቸውን ዳሰሰ። ዐይኖቻቸውም ተከፈቱ። ኢየሱስም “ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ፤” ብሎ በብርቱ አዘዛቸው። እነርሱ ግን ወጥተው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ። እነርሱም ሲወጡ እነሆ ጋኔን ያደረበትን ድዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ጋኔኑንም ካወጣው በኋላ ድዳው ተናገረ። ሕዝቡም “እንዲህ ያለ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልታየም፤” እያሉ ተደነቁ። ፈሪሳውያን ግን “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል፤” አሉ።
ማቴዎስ 9:1-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ባሕሩን በጀልባ ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ መጣ። በዚያም ሰዎች አንድ ሽባ ሰው በቃሬዛ ተሸክመው ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አይዞህ አንተ ልጅ፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራን፣ “ይህማ እግዚአብሔርን መሳደብ ነው” በማለት በልባቸው አጕረመረሙ። ኢየሱስ ሐሳባቸውን ተረድቶ እንዲህ አለ፤ “ክፉ ነገር በልባችሁ ለምን ታስባላችሁ? ለመሆኑ፣ ‘ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀልላል? ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው” ብሎ፣ ሽባውን፣ “ተነሣ! ቃሬዛህን ይዘህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። ሽባውም ተነሥቶ ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተደነቁ፤ በፍርሀት ተሞልተው፣ እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው በቀረጥ መሰብሰቢያው ተቀምጦ አየና፣ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው። ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ላይ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ዐብረው ሊመገቡ ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋራ ለምን ዐብሮ ይበላል?” ብለው ጠየቋቸው። ኢየሱስም የተናገሩትን ሰምቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሐኪም የሚያስፈልገው ለሕመምተኞች እንጂ ለጤነኞች አይደለም፤ ሄዳችሁ፣ ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወድዳለሁ፤’ የሚለውን ቃል ትርጕም አጢኑ፤ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና።” የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛና ፈሪሳውያን ስንጾም፣ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን ለምን አይጾሙም?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሽራው ዐብሯቸው እያለ ዕድምተኞቹ እንዴት ሊያዝኑ ይችላሉ? ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያም ጊዜ ይጾማሉ። “በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ ቍራጭ ጨርቅ የሚጥፍ ሰው የለም፤ ይህ ከሆነ አዲሱ ዕራፊ ካረጀው ልብስ ላይ ተቦጭቆ ቀዳዳውን የባሰ ያሰፋዋል። አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ አቍማዳ ማንም አያስቀምጥም፤ ይህ ከሆነ አቍማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቍማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል። ነገር ግን አዲስ የወይን ጠጅ በአዲስ አቍማዳ ይጨመራል፤ በዚህ ሁኔታ የወይን ጠጁና አቍማዳው በደኅና ተጠብቀው ይቈያሉ።” ኢየሱስ ሰዎቹን በማናገር ላይ ሳለ፣ አንድ የምኵራብ አለቃ መጥቶ ከፊቱ ተደፍቶ፣ “ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” አለው። ኢየሱስም ተነሥቶ ዐብሮት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። ከዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት ከበስተኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ነካች። እርሷም በልቧ፣ “የልብሱን ጫፍ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” ብላ ነበር። ኢየሱስም ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ሴቲቱን አያትና፣ “አይዞሽ፣ ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴቲቱም ወዲያውኑ ተፈወሰች። ኢየሱስ ወደ ሹሙ ቤት እንደ ደረሰ እንቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፣ “ዞር በሉ፤ ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው፤ እነርሱ ግን ሣቁበት። ሕዝቡም ከወጣ በኋላ ወደ ውስጥ ገብቶ እጇን ያዘ፤ ብላቴናዪቱም ተነሥታ ቆመች። ወሬውም በአካባቢው ሁሉ ተሠራጨ። ኢየሱስም ከዚያ እንደ ሄደ ሁለት ዐይነ ስውሮች፣ “የዳዊት ልጅ፤ ማረን!” በማለት እየጮኹ ተከተሉት። ዐይነ ስውሮቹም ኢየሱስ ወደ ገባበት ቤት ተከትለው ገቡ፤ ኢየሱስም፣ “ዐይናችሁን ላበራላችሁ እንደምችል ታምናላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤” ብለው መለሱለት። ከዚያም ኢየሱስ ዐይኖቻቸውን ዳስሶ፣ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው። ዐይኖቻቸውም በሩ፤ ኢየሱስም፣ “ይህን ማንም እንዳያውቅ” ብሎ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው። እነርሱ ግን ወጥተው በአካባቢው ሁሉ ስለ ኢየሱስ አወሩ። ከዚያም ሲወጡ፣ በጋኔን የተያዘ ድዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ጋኔኑ ከወጣለት በኋላ ድዳው መናገር ጀመረ፤ ሕዝቡም ተደንቀው፣ “እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ምድር ታይቶ አያውቅም” አሉ። ፈሪሳውያን ግን፣ “አጋንንትን የሚያወጣው፣ በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ።
ማቴዎስ 9:1-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በታንኳም ገብቶ ተሻገረና ወደ ገዛ ከተማው መጣ። እነሆም፥ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፦ አንተ ልጅ፥ አይዞህ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው። እነሆም፥ ከጻፎቹ አንዳንዱ በልባቸው፦ ይህስ ይሳደባል አሉ። ኢየሱስም አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ፦ ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ? ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ፦ ተነሣና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል? ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፥ በዚያን ጊዜ ሽባውን፦ ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው። ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም አይተው ተደነቁ፥ ለሰውም እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጠ እግዚአብሔርን አከበሩ። ኢየሱስም ከዚያ አልፎ በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው አየና፦ ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው። በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን፦ መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል? አሉአቸው። ኢየሱስም ሰምቶ፦ ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤ ነገር ግን ሄዳችሁ፦ ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና አላቸው። በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው፦ እኛና ፈሪሳውያን፥ ብዙ ጊዜ የምንጦመው፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ። በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። ይህንም ሲነግራቸው፥ አንድ መኵኦንን መጥቶ፦ ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች እያለ ሰገደለት። ኢየሱስም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው። እነሆም፥ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ በልብዋ፦ ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ፥ እድናለሁ ትል ነበረችና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና፦ ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች። ኢየሱስም ወደ መኵኦንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፦ ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ አላቸው። በጣምም ሳቁበት። ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፥ ብላቴናይቱም ተነሣች። ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ። ኢየሱስም ከዚያ ሲያልፍ ሁለት ዕውሮች፦ የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረን ብለው እየጮሁ ተከተሉት። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፥ ኢየሱስም፦ ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን? አላቸው። አዎን፥ ጌታ ሆይ አሉት። በዚያን ጊዜ፦ እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ። ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ። ኢየሱስም፦ ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ ብሎ በብርቱ አዘዛቸው። እነርሱ ግን ወጥተው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ። እነርሱም ሲወጡ እነሆ፥ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ጋኔኑንም ካወጣው በኋላ ዲዳው ተናገረ። ሕዝቡም፦ እንዲህ ያለ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልታየም እያሉ ተደነቁ። ፈሪሳውያን ግን፦ በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል አሉ።
ማቴዎስ 9:1-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጀልባ በመሳፈር ባሕሩን ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ መጣ። በዚያም ሰዎች በአልጋ ላይ የተኛ አንድ ሽባ ይዘው ወደ እርሱ መጡ። እርሱም እምነታቸውን አይቶ፥ ሽባውን፥ “ልጄ ሆይ! አይዞህ፤ ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው። በዚህ ጊዜ አንዳንድ የሕግ መምህራን፥ “ይህ ሰው በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ይናገራል!” እያሉ በልባቸው አሰቡ። ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምን ይህን ክፉ ነገር በልባችሁ ታስባላችሁ? ለመሆኑ ‘ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ!’ ከማለት የትኛው ይቀላል? ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ለማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው ታውቁ ዘንድ” ሽባውን ሰው “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ወደ ቤትህ ሂድ” አለው። ሰውዬውም ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተገረሙ፤ እንዲህ ያለውንም ሥልጣን ለሰው በመስጠቱ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ኢየሱስ ከዚያ ቦታ ተነሥቶ ሲሄድ ሳለ ማቴዎስ የተባለውን ቀራጭ በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ!” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው። ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ተቀምጦ ሳለ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች፥ ወደዚያ መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በማእድ ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም ይህን አይተው ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ስለምን አብሮ ይበላል?” አሉአቸው። ኢየሱስም ይህን ሰምቶ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም። ሂዱ፤ ‘እኔ የምፈልገው ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን አይደለም’ ተብሎ የተጻፈው ምን ማለት እንደ ሆነ መርምራችሁ አስተውሉ። እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ ለመጥራት ነው” አላቸው። በዚያን ጊዜ፥ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ መጥተው፥ “እኛና ፈሪሳውያን ዘወትር እንጾማለን፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሚዜዎች ማዘን ይገባቸዋልን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። በአረጀ ልብስ ላይ አዲስ ዕራፊ የሚጥፍ ማንም የለም፤ ቢጣፍ ግን አዲሱ ዕራፊ አሮጌውን ልብስ ቦጭቆ ቀዳዳውን የባሰ ያሰፋዋል። እንዲሁም በአረጀ የውሃ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር ማንም የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ተበላሽቶ ከጥቅም ውጪ ይሆናል። ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ማኖር ይገባል፤ በዚህም ዐይነት፥ ሁለቱም በደኅና ተጠብቀው ይኖራሉ።” ኢየሱስ ይህን ሲነግራቸው ሳለ፥ አንድ የምኲራብ አለቃ ወደ እርሱ መጣ፤ በግንባሩም በኢየሱስ ፊት ተደፍቶ፥ “እነሆ፥ ልጄ አሁን ሞተችብኝ፤ ነገር ግን አንተ መጥተህ እጅህን ብትጭንባት ትድናለች” አለው። ኢየሱስም ተነሣና ሰውየውን ተከትሎ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም አብረው ሄዱ። እነሆ፥ ዐሥራ ሁለት ዓመት ሙሉ ደም እየመታት ትሠቃይ የነበረች አንዲት ሴት፥ በዚያን ጊዜ ከኢየሱስ በስተኋላ መጥታ የልብሱን ጫፍ በእጅዋ ነካች። ይህንንም ያደረገችው “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ” ብላ በልብዋ አስባ ስለ ነበር ነው። ኢየሱስም መለስ ብሎ አያትና “አይዞሽ ልጄ ሆይ! እምነትሽ አድኖሻል” አላት። ሴትዮዋም ወዲያውኑ ዳነች። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ምኲራብ አለቃው ቤት በደረሰ ጊዜ የሐዘን እምቢልታ ነፊዎችንና እየተራወጡ በመጮኽ የሚያለቅሱትን ሰዎች አየ። እርሱም “ሁላችሁም ከዚህ ውጡ! ልጅትዋ አንቀላፍታለች እንጂ አልሞተችም!” አላቸው። እነርሱ ግን በማፌዝ ሳቁበት። ሰዎቹም ከወጡ በኋላ፥ ኢየሱስ ልጅትዋ ወደምትገኝበት ክፍል ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ እርሷም ተነሣች። የዚህም ነገር ዝና በዚያ አገር ሁሉ ተሰማ። ኢየሱስ ከዚያ ቦታ ተነሥቶ ሲሄድ ሁለት ዕውሮች ተከተሉት፤ እነርሱም “የዳዊት ልጅ ሆይ! እባክህ ማረን!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ኢየሱስ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም “እኔ ይህን ማድረግ እንደምችል ታምናላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎ፥ ጌታ ሆይ!” ሲሉ መለሱ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ዐይኖቻቸውን በእጁ ዳሰሰና፦ “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ!” አላቸው። ዐይኖቻቸውም ተከፈቱ፤ ኢየሱስም “ይህን ነገር ለማንም አትንገሩ!” ሲል በጥብቅ አዘዛቸው። እነርሱ ግን ሄደው በዚያ አገር ሁሉ ስለ ኢየሱስ ዝና አወሩ። ዐይኖቻቸው የተከፈቱላቸው ሰዎች ወጥተው በሄዱ ጊዜ ሌሎች ሰዎች ጋኔን ያደረበትን አንድ ድዳ ሰው ወደ ኢየሱስ አመጡ። ጋኔኑም ከእርሱ በወጣ ጊዜ ድዳው ሰው ተናገረ፤ ሕዝቡም “እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ከቶ ታይቶ አይታወቅም!” እያሉ ተደነቁ። ፈሪሳውያን ግን “እርሱ አጋንንትን የሚያስወጣው በአጋንንት አለቃ አማካይነት ነው” አሉ።
ማቴዎስ 9:1-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ ጀልባ ገብቶ ተሻገረና ወደ ገዛ ከተማው መጣ። እነሆ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ አመጡ፤ ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “ልጄ ሆይ! ጽና፤ ኃጢአቶችህ ተሰርየውልሃል፤” አለው። እነሆ ከጻፎች አንዳንዶቹ በልባቸው “ይህስ ይሳደባል፤” አሉ። ኢየሱስ ግን ሐሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ “ስለምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ? ‘ኃጢአቶችህ ተሰርየውልሃል’ ከማለትና ‘ተነሣና ሂድ’ ከማለት የትኛው ይቀላል? ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአቶችን ሊያስተሰርይ የሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው፤” በዚያን ጊዜ ሽባውን “ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ። ሕዝቡም ይህንን አይተው ፈሩ፤ እንዲህ ያለውንም ሥልጣን ለሰው በመስጠቱ እግዚአብሔርን አከበሩ። ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ አየውና “ተከተለኝ” አለው። ተነሥቶም ተከተለው። በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ። ፈሪሳውያንም ይህንን አይተው ደቀ መዛሙርቱን “መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ለምን ይበላል?” አሉአቸው። ኢየሱስም ሰምቶ እንዲህ አላቸው፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ ሂዱና ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤’ የሚለው ምን እንደሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና፤” በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ መጥተው “እኛና ፈሪሳውያን ብዙ ጊዜ እንጾማለን፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጾሙት ለምንድን ነው?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ እድምተኞች ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። በአረጀ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ የሚጥፍ የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፤ ቀዳዳውም የባሰ ይሆናል። በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን አቁማዳው ይፈነዳል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከጥቅም ውጭ ይሆናል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖሩታል፤ ሁለቱም ይጠበቃሉ።” ይህንም ሲነግራቸው ሳለ እነሆ አንድ ገዢ መጥቶ እየሰገደ “ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች፤” አለው። ኢየሱስም ተነሥቶ ተከተለው፥ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። እነሆ ለዐሥራ ሁለት ዓመታት ደም የሚፈስሳት ሴት ከኋላው ተጠግታ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤ በልብዋ “ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እድናለሁ፤” ብላ ታስብ ነበርና። ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና “ልጄ ሆይ! አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤” አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች። ኢየሱስም ወደ ገዢው ቤት በደረሰ ጊዜ፥ አስለቃሾችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ፥ “ልጅቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ዞር በሉ፤” አላቸው። እነርሱ ግን ሳቁበት። ነገር ግን ሕዝቡን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፤ ልጅቱም ተነሣች። የዚህም ወሬ ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ። ኢየሱስ ከዚያ አልፎ ሲሄድ ሁለት ዓይነ ስውሮች “የዳዊት ልጅ ሆይ! ማረን፤” ብለው እየጮሁ ተከተሉት። ወደ ቤት በገባ ጊዜ ዓይነ ስውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ ኢየሱስም “ይህን ማድረግ እንደምችል ታምናላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉት። በዚያን ጊዜ ዐይኖቻቸውን ዳሰሰና “እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ” አላቸው። ዐይኖቻቸውም ተከፈቱ። ኢየሱስም “ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ፤” ብሎ በጥብቅ አስጠነቀቃቸው። እነርሱ ግን ሄደው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ። እየወጡ እያለ እነሆ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ጋኔኑ ከወጣ በኋላ ዲዳው ተናገረ። ሕዝቡም ተደንቀው “እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ከቶ ታይቶ አይታወቅም” አሉ። ፈሪሳውያን ግን “በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል” አሉ።