ማቴዎስ 7:1-28
ማቴዎስ 7:1-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በወንድምህም ዐይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፤ በዐይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? ወይም ወንድምህን ‘ከዐይንህ ጕድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ’ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዐይንህ ምሰሶ አለ። አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ ከዐይንህ ምሰሶውን አውጣ፤ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዐይን ጕድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ። በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ። “ለምኑ፤ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፤ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፤ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልገውም ያገኛል፤ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ወይስ ልጁ እንጀራ ቢለምነው ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው! እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና። “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፤ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው። “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውስጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፤ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?’ ይሉኛል። የዚያን ጊዜም ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ አመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ’ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፤ በዐለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።” ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን፥
ማቴዎስ 7:1-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበትም ፍርድ ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል። “በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ ሳትመለከት፣ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለምን ታያለህ? ወይም በዐይንህ ውስጥ ግንድ እያለ ወንድምህን፣ ‘ዐይንህ ውስጥ ያለውን ጕድፍ ላውጣልህ’ ማለት እንዴት ትችላለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ በዐይንህ ውስጥ ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጕድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ። “በእግሮቻቸው እንዳይረግጡት፣ ተመልሰውም ነክሰው እንዳይቦጫጭቋችሁ፣ የተቀደሰ ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቈቻችሁንም በዕሪያ ፊት አትጣሉ። “ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል። የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። “ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው፣ ድንጋይ የሚሰጥ አለን? ወይም ዓሣ ቢለምነው እባብ የሚሰጥ ይኖራልን? እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፣ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታን መስጠት ካወቃችሁበት፣ የሰማዩ አባታችሁ ታዲያ ለሚለምኑት መልካም ስጦታን እንዴት አብልጦ አይሰጥ? ሌሎች ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም አድርጉላቸው፤ ኦሪትም፣ ነቢያትም በዚህ ይጠቃለላሉና። “በጠባቡ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው መንገድ ትልቅ፣ በሩም ሰፊ ነውና፤ ብዙዎችም በዚያ ይገባሉ። ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን፣ በሩም ጠባብ ነው፤ የሚገቡበትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው። “በውስጣቸው ነጣቂ ተኵላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው መካከላችሁ በመግባት ከሚያሸምቁ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾኽ ቍጥቋጦ ወይን፣ ከኵርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁም ጥሩ ዛፍ ሁሉ ጥሩ ፍሬ፣ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። ጥሩ ዛፍ መጥፎ ፍሬ፣ መጥፎም ዛፍ ጥሩ ፍሬ ማፍራት አይችልም። ጥሩ ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህ በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። “በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም። በዚያ ቀን ብዙዎች፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል። በዚያ ጊዜ፣ ‘ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዐመፀኞች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ። “እንግዲህ ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የሚያውል፣ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራን ብልኅ ሰው ይመስላል። ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያን ቤት መታው፤ በዐለትም ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ይህን ቃሌን ሰምቶ በተግባር የማያውለው ግን ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራን ሞኝ ሰው ይመስላል። ዶፍ ወረደ፤ ጐርፍም ጐረፈ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ያን ቤት መታው፤ ቤቱም ወደቀ፤ አወዳደቁም የከፋ ነበር።” ኢየሱስ ማስተማሩን በፈጸመ ጊዜ፣ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ።
ማቴዎስ 7:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም? ወይም ወንድምህን፦ ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ። አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ። በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ። ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ወይስ ከእናንተ ልጁ እንጀራ ቢለምነው ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው? ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው? እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና። በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው። የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች፦ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ። ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ። ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን፥
ማቴዎስ 7:1-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “በእናንተ ላይ እንዳይፈረድባችሁ፥ በማንም ላይ አትፍረዱ፤ በሌሎች ላይ በምትፈርዱበት ፍርድ፥ በእናንተም ላይ ይፈረድባችኋል፤ እንዲሁም በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ ሳታይ፥ ስለምን በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ትመለከታለህ? ደግሞስ በአንተ ዐይን ግንድ እያለ፥ ወንድምህን ‘እስቲ በዐይንህ ያለውን ጒድፍ ላውጣልህ’ እንዴት ትለዋለህ? አንተ ግብዝ! አስቀድመህ በአንተ ዐይን ያለውን ግንድ አውጣ፤ ከዚያም በኋላ፥ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጒድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ። የተቀደሰውን ነገር ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቋችሁንም በዐሣማዎች ፊት አትጣሉ፤ ዐሣማዎቹ ዕንቋችሁን በእግራቸው ይረግጡታል፤ ውሾቹም ተመልሰው ይነክሱአችኋል። “ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ የሚለምን ሁሉ ይቀበላል፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ በር ለሚያንኳኳም ይከፈትለታል። ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው፥ ድንጋይ የሚሰጠው ማነው? ዓሣ ቢለምነውስ፥ እባብ ይሰጠዋልን? እንግዲህ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ፥ ለልጆቻችሁ መልካም ነገር መስጠትን ካወቃችሁ፤ ታዲያ፥ በሰማይ ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን አይሰጣቸውም! እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ፥ እናንተም ለእነርሱ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የሕግና የነቢያት ትምህርትም የሚሉት ይህንኑ ነው። “በጠባብዋ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚያስገባው በር ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነው። ወደዚያ የሚገቡትም ሰዎች ብዙዎች ናቸው። ወደ ሕይወት የሚያስገባው በር ግን ጠባብ ነው፤ መንገዱም አስቸጋሪ ነው፤ እርሱን የሚያገኙት ሰዎች ጥቂቶች ናቸው። “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ፥ በውስጣቸው ግን እንደ ነጣቂ ተኲላዎች ከሆኑት ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፤ እነርሱንም የምታውቁአቸው በሥራቸው ፍሬ ነው። ከእሾኽ ቊጥቋጦ የወይን ፍሬ፥ ከኮሸሽላስ የበለስ ፍሬ ይለቀማልን? እንዲሁም መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬ ያፈራል። መልካም ዛፍ መጥፎ ፍሬ ማፍራት አይችልም፤ መጥፎ ዛፍም መልካም ፍሬ ማፍራት አይችልም። መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ፥ ተቈርጦ ወደ እሳት ይጣላል። ስለዚህ፥ ሐሰተኞች ነቢያትን በሥራቸው ፍሬ ታውቁአቸዋላችሁ። ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም፤ ወደ መንግሥተ ሰማይ የሚገባው በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም ነው። በፍርድ ቀን ብዙዎች፥ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?’ ይሉኛል። እኔም በዚያ ቀን፥ ‘በጭራሽ አላውቃችሁም! እናንተ ክፉ አድራጊዎች ከእኔ ወዲያ ራቁ!’ እላቸዋለሁ። “ይህን ቃሌን ሰምቶ በሥራ ላይ የሚያውለው ሁሉ፥ ቤቱን በድንጋይ መሠረት ላይ የሠራ ብልኅ ሰውን ይመስላል። ዝናብ ዘነበ፥ ጐርፍ ጐረፈ፥ ነፋስም ነፈሰና ያን ቤት ገፋው፤ ይሁን እንጂ፥ ቤቱ በድንጋይ መሠረት ላይ ስለ ተሠራ አልወደቀም። ይህን ቃሌን ሰምቶ በሥራ ላይ የማያውለው ግን፥ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሞኝ ሰውን ይመስላል። ዝናብ ዘነበ፥ ጐርፍም ጐረፈ፥ ነፋስም ነፈሰና ያንን ቤት ገፋው፤ ቤቱም ወዲያውኑ ወደቀ፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።” ኢየሱስ እነዚህን ነገሮች ተናግሮ ባበቃ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተደነቁ።
ማቴዎስ 7:1-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋል፤ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በዓይንህ ያለውን ምሰሶ ሳትመለከት በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለምን ታያለህ? ወይም እነሆ በዓይንህ ምሰሶ እያለ ወንድምህን ‘ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣልህ ፍቀድልኝ’ እንዴት ትለዋለህ? አንተ ግብዝ፤ አስቀድመህ በዓይንህ ያለውን ምሰሶ አውጣ፤ ከዚያ በኋላ በወንድምህ ዐይን ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ ታያለህ። በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፤ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ። “ጠይቁ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል። የሚጠይቅ ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልግም ያገኛል፤ የሚያንኳኳ ይከፈትለታል። ከእናንተ መካከል ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይ የሚሰጠው ማነው? ዓሣ ቢለምነው እባብ ይሰጠዋልን? እንግዲህ እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁማ ለሚለምኑት መልካም ነገርን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም! እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግና ነቢያትም ይህ ነውና። “በጠባብዋ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ሰፊ መንገዱም ትልቅ ነውና፤ በዚያም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤ ወደ ሕይወት የሚወስደው በር ጠባብ፥ መንገዱም ቀጭን ነውና፤ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው። “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ፥ በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ናቸው። በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ፤ ከእሾህ የወይን ፍሬ፥ ከኮሸሽላስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ መጥፎ ዛፍ ግን መጥፎ ፍሬን ያፈራል። መልካም ዛፍ መጥፎ ፍሬን ማፍራት አይችልም፥ መጥፎ ዛፍም መልካም ፍሬን ማፍራት አይችልም። መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህ በፍሬአቸው ታውቋቸዋላችሁ። በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚፈጽም እንጂ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ!’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት አይገባም። በዚያ ቀን ብዙዎች ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን?’ ይሉኛል። ያንጊዜ ‘ከቶ አላውቃችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ’ እላቸዋለሁ። “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ጠቢብ ሰውን ይመስላል። ዝናብ ዘነበ፥ ጎርፍም ጎረፈ፥ ነፋስም ነፈሰ ያንንም ቤት ገፋው፤ ነገር ግን በዓለት ላይ ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ይህን ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል። ዝናብ ዘነበ፥ ጎርፍም ጎረፈ፥ ነፋስም ነፈሰ ያንንም ቤት መታው፤ ወደቀም፤ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።” ኢየሱስ ይህንን ንግግር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤