ማቴዎስ 6:9-18

ማቴዎስ 6:9-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“እናንተ ግን እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፤ “ ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፤ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች፣ እንዲሁ በምድር ትሁን። የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን። እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፣ በደላችንን ይቅር በለን። ወደ ፈተናም አታግባን ከክፉው አድነን እንጂ፤ መንግሥት፣ ኀይል፣ ክብርም ለዘላለሙ ያንተ ነውና፤ አሜን።’ እናንተ የበደሏችሁን ይቅር ብትሉ የሰማዩ አባታችሁ ደግሞ እናንተን ይቅር ይላችኋል። ነገር ግን የሰዎችን በደል ይቅር የማትሉ ከሆነ፣ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይልላችሁም። “ስትጾሙ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ እነርሱ መጾማቸው እንዲታወቅላቸው ሆነ ብለው በፊታቸው ላይ የሐዘን ምልክት ያሳያሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፤ እንዲህ የሚያደርጉ ዋጋቸውን በሙሉ ተቀብለዋል። አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ በዚህም መጾምህ በስውር ያለው አባትህ ብቻ የሚያውቀው፣ ከሰዎች ግን የተሰወረ ይሆናል፤ በስውር የተደረገውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።

ማቴዎስ 6:9-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ስለዚህ እናንተ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ፦ ‘በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ! ስምህ ይመስገን፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነ፥ እንዲሁም በምድር ይሁን። የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን። እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል፥ በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉ አድነን እንጂ፥ ወደ ፈተና አታግባን፤ [መንግሥት፥ ኀይልና ክብር ለዘለዓለም ያንተ ነው፤ አሜን።’] “የሰዎችን በደል ይቅር ብትሉላቸው፥ እናንተንም የሰማዩ አባታችሁ ይቅር ይልላችኋል። የሰዎችን በደል ይቅር ባትሉላቸው ግን የእናንተንም በደል የሰማዩ አባታችሁ ይቅር አይልላችሁም።” ኢየሱስም ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “በምትጾሙበት ጊዜ፥ መጾማቸውን ሰዎች እንዲያውቁላቸው፥ ፊታቸውን እንደሚለውጡት እንደ ግብዞች፥ ፊታችሁን አታጠውልጉ፤ በእውነት እላችኋለሁ፥ እነርሱ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን በምትጾምበት ጊዜ ፊትህን ታጠብ፤ ራስህንም ተቀባ፤ በዚህ አኳኋን፥ መጾምህን በስውር ካለው አባትህ በቀር ሌላ ማንም አያውቅም። በስውር የተሠራውን የሚያይ አባትህም ዋጋህን ይከፍልሃል።”