ማቴዎስ 6:19-34

ማቴዎስ 6:19-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። “የሰውነት መብራት ዐይን ናት። ዐይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዐይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ! “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፤ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እንግዲህ ‘ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።

ማቴዎስ 6:19-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና። “ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ መላው ሰውነትህ በብርሃን የተሞላ ይሆናል። ዐይንህ ታማሚ ከሆነ ግን መላው ሰውነትህ በጨለማ የተሞላ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ውስጥ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማው እንዴት ድቅድቅ ይሆን? “ማንም ሰው ሁለት ጌቶችን ማገልገል አይችልም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወድዳል፤ ወይም አንዱን አክብሮ ሌላውን ይንቃል። እግዚአብሔርንና ገንዘብን በአንድነት ማገልገል አይቻልም። “ስለዚህ እላችኋለሁ፣ ስለ ኑሯችሁ ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? በማለት አትጨነቁ። ሕይወት ከምግብ፣ ሰውነትስ ከልብስ አይበልጥምን? እስኪ የሰማይ ወፎችን ተመልከቱ፤ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራም አያከማቹም፤ ይሁን እንጂ የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ለመሆኑ፣ ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ላይ አንድ ሰዓት መጨመር የሚችል ማን ነው? “ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? እስኪ የሜዳ አበቦችን ተመልከቱ፤ አይለፉም፤ ወይም አይፈትሉም። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞን እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነርሱ እንደ አንዷ አልለበሰም። እናንተ እምነት የጐደላችሁ፤ እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ ነገ ወደ እሳት የሚጣለውን የሜዳ ሣር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፣ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ? ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት አጥብቀው ይሻሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፤ እነዚህም ሁሉ ይጨመሩላችኋል። ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ፤ የነገ ጭንቀት ለነገ ይደር፤ እያንዳንዱ ዕለት የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለውና።

ማቴዎስ 6:19-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና። የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ! ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም። ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው? ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤ አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት? እንግዲህ፦ ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።

ማቴዎስ 6:19-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ብልና ዝገት በሚያጠፉበት፥ ሌቦችም ሰብረው በሚሰርቁበት፥ በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ይልቅስ ብልና ዝገት ሊያጠፉት በማይችሉበት፥ ሌቦችም ሰብረው በማይሰርቁበት በሰማይ ሀብታችሁን አከማቹ። ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይገኛል። “ዐይን የሰውነት መብራት ነው፤ ስለዚህ ዐይንህ ጤናማ ከሆነ፥ ሰውነትህ በሙሉ ብርሃን ይሆናል፤ ዐይንህ ጤናማ ካልሆነ ግን፥ ሰውነትህ በሙሉ ጨለማ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማው እንዴት የባሰ ይሆን! “አንድ ሰው ለሁለት ጌቶች አገልጋይ ሊሆን አይችልም፤ ወይም አንዱን ይጠላል፥ ሌላውንም ይወዳል፤ ወይም አንዱን ያከብራል፥ ሌላውን ይንቃል፤ እንዲሁም አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ አገልጋይ መሆን አይችልም። ስለዚህ እንዲህ እላችኋለሁ፤ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ በማለት ስለ ኑሮአችሁ አትጨነቁ፤ ከምግብ ሕይወት፥ ከልብስም ሰውነት አይበልጥምን? እስቲ በሰማይ ላይ ወደሚበሩት ወፎች ተመልከቱ፤ እነርሱ አይዘሩም፤ አያጭዱም፤ በጐተራ አይከቱም፤ ነገር ግን የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከወፎች እጅግ ትበልጡ የለምን? ለመሆኑ ከእናንተ በመጨነቅ፥ በዕድሜው ላይ አንድ ቀን እንኳ መጨመር የሚችል ማን ነው? ደግሞስ ስለ ልብስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የአሸንድዬ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ እስቲ ተመልከቱ፤ እነርሱ በሥራ አይደክሙም፤ አይፈትሉም፤ ነገር ግን ሰሎሞንስ እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ፥ ከእነርሱ እንደ አንዲቱ አለበሰም እላችኋለሁ። ታዲያ ዛሬ ታይቶ ነገ በእሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር፥ እግዚአብሔር እንዲህ የሚያለብስ ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጐደላችሁ! እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም! ስለዚህ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ እያላችሁ በማሰብ አትጨነቁ። ይህን ለማግኘትማ አሕዛብም ይፈልጋሉ፤ እናንተ ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ፥ የሰማይ አባታችሁ ያውቃል። እናንተ ግን፥ አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፤ የቀረው ነገር ሁሉ ይጨመርላችኋል፤ ነገ ለራሱ ይጨነቃል፤ ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።”

ማቴዎስ 6:19-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“ብልና ዝገት በሚያጠፉት፥ ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁበት በምድር ላይ ሃብት አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልና ዝገት በማያጠፉት፥ ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁበት በሰማይ ሃብትን ሰብስቡ፤ ሃብትህ ባለበት ልብህም በዚያ ይሆናልና። “ዐይን የሰውነት መብራት ናት። ስለዚህ ዓይንህ ጤናማ ከሆነች፥ ሰውነትህ ሁሉ የበራ ይሆናል፤ ዓይንህ የታመመች ከሆነች ግን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማው እንዴት የበረታ ይሆን! “ሁለት ጌቶችን ማገልገል የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሌላውን ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።” ስለዚህ እላችኋለሁ፤ ስለ ነፍሳችሁ ምን እንደምትበሉና ምን እንደምትጠጡ፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ ምን እንደምትለብሱ አትጨነቁ፤ ነፍስ ከምግብ ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን? ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም፥ ወይም አያጭዱም፥ ወደ ጎተራም አይሰበስቡም፤ ነገር ግን የሰማዩ አባታችሁ ይመግባቸዋል፤ ታዲያ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን? ከእናንተ በመጨነቅ በዕድሜው ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል እስቲ ማን ነው? ስለ ልብስስ ለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንደሚያድጉ ተመልከቱ፤ አይለፉም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰሎሞንስ እንኳ በዚያ ሁሉ ክብሩ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም። ነገር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እግዚአብሔር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁም? ስለዚህ “ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?” ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብም እነዚህን ሁሉ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃል። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን ፈልጉ፥ እነዚህም ሁሉ ይጨመሩላችኋል። “ስለዚህ ስለነገ አትጨነቁ፥ ነገ ስለ ራሱ ይጨነቃልና፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።

ማቴዎስ 6:19-34

ማቴዎስ 6:19-34 NASVማቴዎስ 6:19-34 NASV