ማቴዎስ 6:1-6

ማቴዎስ 6:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሰዎች ይዩልን ብላችሁ መልካም ሥራችሁን በሰዎች ፊት ከማድረግ ተጠንቀቁ፤ አለበለዚያ ግን፥ በሰማይ አባታችሁ ዘንድ ምንም ዋጋ አታገኙም። ስለዚህ ለድኾች ምጽዋት በምትመጸውትበት ጊዜ፥ ግብዞች በየምኲራቡና በየመንገዱ እንደሚያደርጉት ለታይታ አታድርጉ፤ በእውነት እነግራችኋለሁ፥ እነርሱ ዋጋቸውን አስቀድመው አግኝተዋል። አንተ ግን ምጽዋት ስትመጸውት ቀኝ እጅህ የሚያደርገውን ግራ እጅህ አይወቅ። እንግዲህ ምጽዋትህ በስውር ይሁን፤ በስውር የተሠራውን የሚያየው አባትህ፥ የመልካም ሥራህን ዋጋ ይከፍልሃል። “በምትጸልዩበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ! እነርሱ ሰው እንዲያይላቸው ብለው በየምኲራቡና በየመንገዱ ዳር ቆመው መጸለይ ይወዳሉ። በእውነት እላችኋለሁ፥ እነርሱ ዋጋቸውን በቅድሚያ አግኝተዋል። አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ ክፍልህ ገብተህ፥ በርህን ዝጋና በስውር ወዳለው ወደማይታይ አባትህ ጸልይ፤ በስውር የተሠራውን የሚያይ አባትህም የመልካም ሥራህን ዋጋ ይከፍልሃል።