ማቴዎስ 5:1-43

ማቴዎስ 5:1-43 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ፦ “ንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤መፅናናትን ያገኛሉና። የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ምድርን ይወርሳሉና። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ይጠግባሉና። የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፤ይማራሉና። ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፤እግዚአብሔርን ያዩታልና። የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፤የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። “ቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፤ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።” እናንተ “ድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። “ንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል፤በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። “ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፤ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፤ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ። እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል። እላችኋለሁና ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። “ለቀደሙት ‘አትግደል’ እንደተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፤አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ። አብረኸው በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራ ለዳኛ እንዳይሰጥህ ዳኛም ለሎሌው፤ወደ ወህኒም ትጣላለህ፤ እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም። “ ‘አታመንዝር’ ዝንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዐይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና። “ ‘ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት’ ተባለ። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። “ደግሞ ለቀደሙት ‘በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፤ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው። “ ‘ዐይን ስለ ዐይን ጥርስም ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል። “ ‘ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

ማቴዎስ 5:1-43 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ብዙ ሕዝብ እንደ ተሰበሰበ ባየ ጊዜ፣ ወደ ተራራ ወጣና ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ መጡ። እንዲህም እያለ ያስተምራቸው ጀመር፤ “በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና። የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ ይጠግባሉና። ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና። ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና። ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና። ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና። “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳድደዋቸዋልና። “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው ጣዕሙን ቢያጣ ጨውነቱን መልሶ ሊያገኝ ይችላልን? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ጥቅም አይኖረውም። “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤ ሰዎችም መብራት አብርተው ከእንቅብ በታች አያስቀምጡትም፤ በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል እንጂ። እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ። “ሕግንና የነቢያትን ቃል ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ፊደል ወይም አንዲት ነጥብ እንኳ አትሻርም። ስለዚህ ማንም ከእነዚህ ትእዛዞች አነስተኛዪቱን እንኳ ቢተላለፍ፣ ሌሎችንም እንዲተላለፉ ቢያስተምር፣ በመንግሥተ ሰማይ ታናሽ ተብሎ ይጠራል፤ ነገር ግን እነዚህን ትእዛዞች እየፈጸመ ሌሎችም እንዲፈጽሙ የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይባላል። ጽድቃችሁ ከፈሪሳውያንና ከኦሪት ሕግ መምህራን ጽድቅ ልቆ ካልተገኘ መንግሥተ ሰማይ መግባት አትችሉም። “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወንድሙን ያለ አግባብ የሚቈጣ ይፈረድበታል፤ ማንም ወንድሙን ‘ጅል’ የሚል በሸንጎ ፊት ይጠየቅበታል፤ ‘ደደብ’ የሚለው ደግሞ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይጠብቀዋል። “ስለዚህ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ፣ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣ መባህን በዚያው በመሠዊያው ፊት ተወው፤ በመጀመሪያ ሄደህ ከወንድምህ ጋራ ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ። “የከሰሰህ ባላጋራህ እንዳያስፈርድብህ፣ ዳኛውም ለአገልጋዩ አሳልፎ እንዳይሰጥህ፣ ወደ ወህኒ እንዳትጣል፣ በመንገድ ላይ ሳለህ ከባላጋራህ ጋራ ፈጥነህ ተስማማ። እውነት እልሃለሁ፤ ካስፈረደብህ ግን የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከዚያ አትወጣም። “ ‘አታመንዝር’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሴትን በምኞት ዐይን የተመለከተ ሁሉ በልቡ ከርሷ ጋራ አመንዝሯል። ቀኝ ዐይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ ቢያሰናክልህ ቈርጠህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። “ ‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍችውን ጽሕፈት መስጠት አለበት’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ፣ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ በዚህ ሁኔታ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል። “ለቀደሙት ሰዎች፣ ‘በሐሰት አትማል፤ በጌታ ፊት የማልኸውንም ጠብቅ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ፈጽሞ አትማሉ እላችኋለሁ፤ በሰማይም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም ቢሆን አትማሉ፤ የእግዚአብሔር የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም ቢሆን አትማል፤ ከጠጕራችሁ መካከል አንዲቷን እንኳ ነጭ ወይም ጥቍር ማድረግ አትችሉምና። ስለዚህ ስትነጋገሩ ቃላችሁ፣ ‘አዎን’ ከሆነ ‘አዎን’፤ ‘አይደለም’ ከሆነ ‘አይደለም’ ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ሁሉ ከክፉው የሚመጣ ነውና። “ ‘ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ‘ክፉ አድራጊውን ሰው አትቃወሙት’፤ ነገር ግን ቀኝ ጕንጭህን ለሚመታህ ሌላውን ጕንጭህን ደግሞ አዙርለት። አንድ ሰው እጀ ጠባብህን ሊወስድ ቢከስስህ ካባህን ጨምረህ ስጠው። አንድ ሰው አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ ዐብረኸው ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተም ሊበደር የሚሻውን ፊት አትንሣው። “ ‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

ማቴዎስ 5:1-43 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ፦ በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና። የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና። ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና። የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና። እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል። መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ። እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ። እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል። እላችኋለሁና፦ ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም። ለቀደሙት፦ አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ። አብረኸው በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራ ለዳኛ እንዳይሰጥህ ዳኛም ለሎሌው፥ ወደ ወህኒም ትጣላለህ፤ እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም። አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና። ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት ተባለ። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። ደግሞ ለቀደሙት፦ በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፦ ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው። ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል። ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

ማቴዎስ 5:1-43 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ የሚከተለውን ብዙ ሕዝብ ባየ ጊዜ፥ ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀረቡ። እንዲህ እያለም ያስተምራቸው ጀመር፤ “መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለ ሆነች በመንፈሳዊ ኑሮአቸው ድኾች መሆናቸው የሚሰማቸው የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔር መጽናናትን ስለሚሰጣቸው የሚያዝኑ የተባረኩ ናቸው። ትሑቶች ምድርን ስለሚወርሱ የተባረኩ ናቸው። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ስለሚጠግቡ የተባረኩ ናቸው። ምሕረትን ስለሚያገኙ ምሕረትን የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔርን ስለሚያዩት ንጹሕ ልብ ያላቸው የተባረኩ ናቸው። በሰዎች መካከል ዕርቅና ሰላምን የሚያደርጉ፥ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ የተባረኩ ናቸው። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ፥ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለ ሆነች የተባረኩ ናቸው። “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲሰድቡአችሁና ሲያሳድዱአችሁ፥ በውሸትም ስማችሁን ሲያጠፉት ደስ ይበላችሁ። በመንግሥተ ሰማይ የምታገኙት ዋጋ ትልቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንዲሁ ስደትና መከራ አድርሰውባቸዋል።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እናንተ እንደ ምድር ጨው ናችሁ፤ ነገር ግን ጨው ጣዕሙን ካጣ እንዴት ጣዕሙን መልሶ ሊያገኝ ይችላል? ወደ ውጪ ከመጣልና በሰው እግር ከመረገጥ በቀር ወደፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤ በተራራ ላይ የተሠራች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም። ሰዎች መብራት አብርተው በቤት ውስጥ ላሉት ሁሉ እንዲያበራ በከፍተኛ ቦታ ያስቀምጡታል እንጂ ከእንቅብ በታች አያኖሩትም። እንዲሁም ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው የሰማይ አባታችሁን እንዲያመሰግኑት፥ የእናንተም ብርሃን በሰው ፊት ይብራ።” ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የኦሪትን ሕግና የነቢያትን ትምህርት ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ እኔ እንዲፈጸሙ ላደርጋቸው መጣሁ እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም። በእውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ሕግ ሁሉ ይፈጸማል እንጂ ከሕግ አንዲት ጭረት ወይም አንዲት ነጥብ አትሻርም። ስለዚህ ከእነዚህ ትእዛዞች አነስተኛ የሆነችውን አንድዋን እንኳ የሚያፈርስና ሌሎችም ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስተምር ሰው በመንግሥተ ሰማይ አነስተኛ ይሆናል። ነገር ግን ትእዛዞችን ሁሉ የሚፈጽምና ሌሎችም ሰዎች እንዲሁ እንዲፈጽሙ የሚያስተምር ሰው በመንግሥተ ሰማይ ታላቅ ይሆናል። ስለዚህ የእናንተ ጽድቅ ከሕግ መምህራንና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ከቶ ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደማትገቡ እነግራችኋለሁ። “በቀድሞ ጊዜ ለነበሩ ሰዎች የተባለውን ሰምታችኋል፤ ይኸውም ‘አትግደል፤ ሰውን የገደለ ይፈረድበታል’ የሚል ነው። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ ላይ የሚቈጣ ሁሉ ይፈረድበታል፤ ደግሞም ወንድሙን፥ ‘አንተ የማትረባ!’ ብሎ የሚሳደብ በሸንጎ ይፈረድበታል፤ ‘ደደብ!’ ብሎ የሚሳደብ ሁሉ በገሃነመ እሳት ይፈረድበታል። ስለዚህ አንተ መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ፥ ያዘነብህ ወንድም መኖሩን ብታስታውስ፥ መባህን በመሠዊያው ፊት አስቀምጥና፥ ሄደህ በመጀመሪያ ከዚያ ከወንድም ጋር ታረቅ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰህ መባህን አቅርብ። ባላጋራህ ከሶህ ከእርሱ ጋር ወደ ፍርድ ቤት ስትሄድ በመንገድ ላይ ሳለህ ቶሎ ብለህ ከባላጋራህ ጋር ተስማማ። አለበለዚያ ባላጋራህ ለዳኛ፥ ዳኛውም ለአሳሪ አሳልፎ ይሰጥህና ወደ ወህኒ ቤት ትገባለህ። በእውነት እልሃለሁ፥ የተፈረደብህን የመጨረሻዋን ሳንቲም ከፍለህ እስክትጨርስ ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘አታመንዝር!’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ‘ሴትን ተመልክቶ የተመኛት ሁሉ፥ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመነዘረ’ እላችኋለሁ። የቀኝ ዐይንህ ለኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ አውጥተህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። ቀኝ እጅህ የኃጢአት ምክንያት ቢሆንብህ፥ ቈርጠህ ጣለው! ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል። “ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍችዋን ማስረጃ ይስጣት” ተብሏል። እኔ ግን “በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በቀር፥ ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ እንድታመነዝር ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል” እላችኋለሁ። ደግሞም ለቀደሙ ሰዎች “በሐሰት አትማሉ፤ ነገር ግን መሐላችሁን ለጌታ ፈጽሙ” የተባለውን ሰምታችኋል። እኔ ግን “በፍጹም አትማሉ” እላችኋለሁ። ሰማይ የእግዚአብሔር ዙፋን ስለ ሆነች፥ በሰማይም ቢሆን፥ ምድርም የጌታ እግር ማሳረፊያ ስለ ሆነች በምድርም አትማሉ፤ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ስለ ሆነች በኢየሩሳሌምም አትማሉ፤ ከጸጒርህ አንዲቱን እንኳ ነጭ ወይም ጥቊር ማድረግ ስለማትችል በራስህም ቢሆን አትማል። ስለዚህ ንግግራችሁ “አዎ” ከሆነ “አዎ፥” ወይም “አይደለም” ከሆነ “አይደለም” ይሁን። ከዚህ የተረፈ ቃል ግን ከሰይጣን ነው። “ ‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ፤ ክፉ የሚያደርግባችሁን ሰው አትበቀሉት። ነገር ግን ቀኝ ጒንጭህን ለሚመታህ፥ ግራ ጒንጭህን አዙርለት። አንድ ሰው ሸሚዝህን ለመውሰድ ፈልጎ ቢከስህ፥ ኮትህንም እንዲወስድ ተውለት። አንድ ሰው ‘ከእኔ ጋር ጥቂት መንገድ ሂድ’ ብሎ ቢያስገድድህ፥ አንተ ደግሞ እጥፍ መንገድ ሂድለት። ለሚለምንህ ስጥ፤ ከአንተ መበደር ለሚፈልግ እምቢ አትበለው።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ ‘ባልንጀራህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።

ማቴዎስ 5:1-43 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ አፉንም ከፍቶ እንዲህ ብሎ አስተማራቸው፤ በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መፅናናትን ያገኛሉና። የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ይጠግባሉና። ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና። ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና። ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። “ሲሰድቡአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።” እናንተ የምድሪቱ ጨው ናችሁ፤ ጨው ጣዕሙን ቢያጣ ግን በምን ይጣፍጣል? በሰው ለመረገጥ ወደ ውጭ ከመጣል በስተቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም። እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም። መብራትን አብርተው በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል እንጂ ከዕንቅብ በታች አያኖሩትም፤ በቤትም ላሉት ሁሉ ያበራል። መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ እንግዲህ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ። ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም። እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ ከሕግ አንዲት ኢዮታ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም። ከእነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንድዋን እንኳ ችላ የሚል ሰዎችንም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ ነገር ግን የሚፈጽመው እንዲሁም የሚያስተምር ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል። ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም እላችኋለሁ። “ለቀደሙት ‘አትግደል፥ የገደለ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወንድሙን የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙን ‘የማያስብ’ የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ‘ደደብ’ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል። መባህን በመሠዊያው ላይ በምታቀርብበት ጊዜ፥ በዚያ ሳለህ ቅር የተሰኘብህ ወንድም እንዳለ ብታስታውስ፥ መባህን እዚያው በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ፤ አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ ከዚያ በኋላ መጥተህ መባህን አቅርብ። ባላጋራህ ለዳኛ፥ ዳኛውም ለሎሌው እንዳይሰጥህ ወደ እስር ቤት እንዳትገባ፤ ከባላጋራህ ጋር በመንገድ አብረኸው ስትሄድ ሳለህ ፈጥነህ ተስማማ፤ እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።” “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወደ ሴት አይቶ የተመኛት ሁሉ ከወዲሁ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዐይንህ ብታሰናክልህ ከአንተ አውጥተህ ጣላት፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ከአንተ ቆርጠህ ጣላት፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና። “‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ ወረቀት ጽሕፈት ይስጣት’ ተብሏል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። “ደግሞም ለቀደሙት ‘በውሸት አትማል ነገር ግን የማልኸውንም ለጌታ ስጥ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በፍጹም አትማሉ፤ በሰማይ አትማሉ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አትማሉ የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፤ አንዲቱን ጠጉር እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ስለዚህ ንግግራችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከእነዚህ የተረፈ ግን ከክፉው ነው። “‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ክፉውን አትቃወሙት፤ ነገር ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ ሊከስህ ፈልጎ እጀ ጠባብህን ሊወስድ የፈለገ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ እንድትሄድ ቢያስገድድህ፥ ሁለት ምዕራፍ ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚጠይቅህ ስጥ፤ ከአንተ ሊበደር ከሚፈልገው ፊትህን አታዙር። “‘ባልንጀራህን ውደድ፥ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል።