ማቴዎስ 5:1-12

ማቴዎስ 5:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ብዙ ሕዝብ እንደ ተሰበሰበ ባየ ጊዜ፣ ወደ ተራራ ወጣና ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ መጡ። እንዲህም እያለ ያስተምራቸው ጀመር፤ “በመንፈስ ድኾች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፤ መጽናናትን ያገኛሉና። የዋሆች ብፁዓን ናቸው፤ ምድርን ይወርሳሉና። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤ ይጠግባሉና። ምሕረት የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ ምሕረትን ያገኛሉና። ልባቸው ንጹሕ የሆነ ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና። ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉና። ስለ ጽድቅ ብለው የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፤ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ናትና። “ሰዎች በእኔ ምክንያት ቢሰድቧችሁ፣ ቢያሳድዷችሁና ክፉውን ሁሉ በሐሰት ቢያስወሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። በሰማይ የምትቀበሉት ዋጋ ታላቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሤት አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንደዚሁ አሳድደዋቸዋልና።

ማቴዎስ 5:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ የሚከተለውን ብዙ ሕዝብ ባየ ጊዜ፥ ወደ ተራራ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀረቡ። እንዲህ እያለም ያስተምራቸው ጀመር፤ “መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለ ሆነች በመንፈሳዊ ኑሮአቸው ድኾች መሆናቸው የሚሰማቸው የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔር መጽናናትን ስለሚሰጣቸው የሚያዝኑ የተባረኩ ናቸው። ትሑቶች ምድርን ስለሚወርሱ የተባረኩ ናቸው። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ስለሚጠግቡ የተባረኩ ናቸው። ምሕረትን ስለሚያገኙ ምሕረትን የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔርን ስለሚያዩት ንጹሕ ልብ ያላቸው የተባረኩ ናቸው። በሰዎች መካከል ዕርቅና ሰላምን የሚያደርጉ፥ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሚባሉ የተባረኩ ናቸው። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ፥ መንግሥተ ሰማይ የእነርሱ ስለ ሆነች የተባረኩ ናቸው። “በእኔ ምክንያት ሰዎች ሲሰድቡአችሁና ሲያሳድዱአችሁ፥ በውሸትም ስማችሁን ሲያጠፉት ደስ ይበላችሁ። በመንግሥተ ሰማይ የምታገኙት ዋጋ ትልቅ ስለ ሆነ ደስ ይበላችሁ፤ ሐሴትም አድርጉ። ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንዲሁ ስደትና መከራ አድርሰውባቸዋል።”