ማቴዎስ 27:1-14

ማቴዎስ 27:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤ አስረውም ወሰዱት፤ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፤ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ፤” አለ። እነርሱ ግን “እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ፤” አሉ። ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ። የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው “የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም፤” አሉ። ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት። ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” ተባለ። በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው “ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፤ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት።” የሚል ተፈጸመ። ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም “የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ አልህ፤” አለው። የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ “ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን?” አለው። ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም።

ማቴዎስ 27:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጧት በማለዳ ላይ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ሁሉ ኢየሱስ ስለሚገደልበት ሁኔታ ተመካከሩ፤ ካሰሩትም በኋላ ወስደው ለገዢው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። አሳልፎ የሰጠው ይሁዳም ኢየሱስ እንደ ተፈረደበት ባየ ጊዜ ተጸጸተ፤ የወሰደውን ሠላሳ ጥሬ ብር ለካህናት አለቆችና ለሕዝቡ ሽማግሌዎች መልሶ በመስጠት፣ “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” አለ። እነርሱም፣ “ታዲያ እኛ ምን አገባን፤ የራስህ ጕዳይ ነው!” አሉት። ስለዚህ ይሁዳ ብሩን በቤተ መቅደስ ውስጥ ወርውሮ ወጣ፤ ሄዶም ራሱን ሰቅሎ ሞተ። የካህናት አለቆች ብሩን አንሥተው፣ “የደም ዋጋ ስለ ሆነ ወደ መባ ልንጨምረው አይፈቀድም” አሉ፤ ተመካክረውም ለእንግዶች የመቃብር ስፍራ እንዲሆን በገንዘቡ የሸክላ ሠሪውን ቦታ ገዙበት። ስለዚህም ያ ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” ተብሎ ይጠራል። በዚህም በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “ለርሱ ዋጋ ይሆን ዘንድ የእስራኤል ልጆች የገመቱትን ሠላሳ ጥሬ ብር ተቀበሉ፤ ጌታም ባዘዘኝ መሠረት ለሸክላ ሠሪው ቦታ ከፈሉ።” በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አገረ ገዥው ፊት ቀረበ፤ አገረ ገዥውም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” በማለት ጠየቀው። ኢየሱስም፣ “አንተው እንዳልኸው ነው” ሲል መለሰለት። የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲከስሱት ግን ምንም መልስ አልሰጠም። በዚህ ጊዜ ጲላጦስ፣ “ስንት ነገር አቅርበው እንደሚከስሱህ አትሰማምን?” አለው። እርሱ ግን አገረ ገዥው እስኪገረም ድረስ ለቀረበበት ክስ አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰም።

ማቴዎስ 27:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤ አስረውም ወሰዱት፥ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት። በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ፦ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ። እነርሱ ግን፦ እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ። ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ። የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው፦ የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ። ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት። ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ። በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው፦ ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት። የሚል ተፈጸመ። ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም፦ የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም፦ አንተ አልህ አለው። የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ፦ ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው። ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም።

ማቴዎስ 27:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ጠዋት በማለዳ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ ተማከሩ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስን አስረው ወሰዱና ለገዥው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። ኢየሱስ እንደተፈረደበት ባየ ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ ተጸጸተ፤ ሠላሳውንም ጥሬ ብር ለካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች እንዲህ በማለት መልሶ ሰጣቸው፤ “ንጹሑን ሰው ለሞት አሳልፌ በመስጠቴ በድዬአለሁ።” እነርሱ ግን “ታዲያ፥ እኛ ምን ቸገረን! የራስህ ጉዳይ ነው!” አሉት። እርሱም ሠላሳውን ጥሬ ብር በቤተ መቅደስ ውስጥ በትኖ፥ ትቶአቸው ወጣ፤ ሄዶም ታንቆ ሞተ። የካህናት አለቆች ሠላሳውን ጥሬ ብር አንሥተው “ይህ ገንዘብ የደም ዋጋ ስለ ሆነ ከቤተ መቅደስ መባ ጋር ልንቀላቅለው አይፈቀድም” አሉ። ስለዚህ ከተመካከሩ በኋላ ለእንግዶች የመቃብር ቦታ እንዲሆን የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት። በዚህ ምክንያት ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ “የደም መሬት” እየተባለ ይጠራል። በዚህ ሁኔታ “የእስራኤል ልጆች የገመቱትን ለእርሱ ዋጋ የሚሆን ሠላሳ ጥሬ ብር ወሰዱ፤ ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉት” ተብሎ በነቢዩ ዘካርያስ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ወደ ገዢው ወደ ጲላጦስ ፊት ቀረበ፤ ገዢውም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ እንዳልከው ነው” ሲል መለሰ። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች ሲወነጅሉት ምንም መልስ አልሰጠም። ከዚህ በኋላ ጲላጦስ “በስንት ነገር ሲወነጅሉህ አትሰማምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ገዢው እስኪደነቅ ድረስ ለአንዲት ክስ እንኳ ቃል አልመለሰለትም።

ማቴዎስ 27:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በነጋም ጊዜ ሊቃነ ካህናትና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ሁሉ ኢየሱስን ሊገድሉት ተማከሩ፤ አስረውም ወሰዱት፤ ለገዢው ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት። በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፤ ሠላሳውንም ብር ለሊቃነ ካህናቱና ለሽማግሌዎቹ መለሰላቸው፤ እንዲህም አለ “ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ።” እነርሱ ግን “ታዲያ እኛ ምን አገባን? ጉዳዩ የራስህ ነው፤” አሉት። ብሩን በቤተ መቅደስ ጥሎ ወጣ፤ ሄዶም ታንቆ ሞተ። ሊቀ ካህናቱም ብሩን አንሥተው “የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አይፈቀድም” አሉ። ተማክረውም ለእንግዶች የመቃብር ስፍራ እንዲሆን የሸክላ ሠሪውን መሬት ገዙበት። በዚህም ምክንያት ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተብሎ ይጠራል። በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተነገረው ተፈጸመ “ከእስራኤል ልጆች አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ወሰዱ፤ ጌታም እንዳዘዘኝ ለሸክላ ሠሪው መሬት ከፈሉት።” ኢየሱስ በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?” ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም “አንተ አልህ” አለው። በሊቃነ ካህናትና በሽማግሌዎች ሲከሰስ ምንም አልመለሰም። በዚያን ጊዜ ጲላጦስ “ስንት ነገር እንደሚመሰክሩብህ አትሰማምን?” አለው። እርሱ ግን አንዲት ቃል እንኳ አልመለሰለትም፤ በዚህም ገዢው እጅግ ተደነቀ።