ማቴዎስ 26:57-68

ማቴዎስ 26:57-68 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ አላገኙም፤ ብዙም የሐሰት ምስክሮች ምንም ቢቀርቡ አላገኙም። በኋላም ሁለት ቀርበው “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ፤’ ብሎአል፤” አሉ። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ “እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤” አለው። ኢየሱስም “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኀይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ፤” አለው። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ “ተሳድቦአል፤ እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” አለ። እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ በፊቱ ተፉበት፤ ጐሰሙትም፤ ሌሎችም በጥፊ መትተው “ክርስቶስ ሆይ! በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገርልን፤” አሉ።

ማቴዎስ 26:57-68 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚህ ጊዜ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፣ የኦሪት የሕግ መምህራንና የሕዝብ ሽማግሌዎች ተሰብስበው ወደ ነበሩበት፣ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ነገር ግን ጴጥሮስ ከርቀት ሆኖ እስከ ሊቀ ካህናቱ ቅጥር ግቢ ይከተለው ነበር፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የሁኔታውን መጨረሻ ለማየት ከጠባቂዎቹ ጋራ ተቀመጠ። በዚህ ጊዜ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ በሙሉ ኢየሱስን ለማስገደል የሐሰት ማስረጃ ይፈልጉ ነበር፤ ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም በቂ ማስረጃ አላገኙም። በኋላ ግን ሁለት ሰዎች ቀርበው፣ “ይህ ሰው፣ ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ፣ በሦስት ቀን ውስጥ መልሼ ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል” በማለት ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ተነሥቶ በመቆም፣ “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም፣ “በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ፤ አንተ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ ንገረን” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተው ራስህ ብለኸዋል፤ ነገር ግን ለሁላችሁም ልንገራችሁ፤ ወደ ፊት የሰው ልጅ በኀያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው። በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀድዶ፣ “በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሯል፤ ከዚህ ሌላ ምን ምስክርነት ያስፈልገናል? በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል መናገሩን እናንተው ራሳችሁ ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” አላቸው። እነርሱም፣ “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። በዚህ ጊዜ ፊቱ ላይ እየተፉ በጡጫ መቱት፤ ሌሎቹም በጥፊ እየመቱት፣ “ክርስቶስ ሆይ፤ ማነው የመታህ? እስኪ ትንቢት ንገረን!” አሉት።

ማቴዎስ 26:57-68 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፥ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጕኦውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙም፤ ብዙም የሐሰት ምስክሮች ምንም ቢቀርቡ አላገኙም። በኋላም ሁለት ቀርበው፦ ይህ ሰው፦ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ ብሎአል አሉ። ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ፦ እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን? አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም፦ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው። ኢየሱስም፦ አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ፦ ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም፦ ሞት ይገባዋል ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ በፊቱ ተፉበት፤ ጕኦሰሙትም፥ ሌሎችም በጥፊ መትተው፦ ክርስቶስ ሆይ፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው? ትንቢት ተናገርልን አሉ።

ማቴዎስ 26:57-68 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ኢየሱስን የያዙት ሰዎች ወደ ካህናት አለቃው ወደ ቀያፋ ወሰዱት፤ በዚያም የሕግ መምህራንና ሽማግሌዎች ተሰብስበው ነበር። ጴጥሮስ ግን እስከ ካህናት አለቃው ግቢ ድረስ ኢየሱስን በሩቅ ተከተለው፤ ወደ ውስጥ ገብቶም የነገሩን ፍጻሜ ለማየት ከዘበኞች ጋር ተቀመጠ። የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሸንጎ አባሎች ሁሉ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ለማስፈረድ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር። ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢቀርቡም፥ ሞት የሚያስፈርድበት ምስክርነት አላገኙም፤ በመጨረሻ ሁለት ምስክሮች ቀርበው፥ “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሎአል” ሲሉ ተናገሩ። የካህናት አለቃውም ተነሣና “እነዚህ ሰዎች ለሚመሰክሩብህ ሁሉ ምንም መልስ አትሰጥምን?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። የካህናት አለቃውም እንደገና ኢየሱስን “በሕያው እግዚአብሔር ስም ይዤሃለሁ! አንተ የእግዚአብሔር ልጅ መሲሕ እንደ ሆንክ ንገረን!” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንተ እንዳልከው ነው፤ ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኀያሉ እግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ታዩታላችሁ፤ እንዲሁም በሰማይ ደመና ሆኖ ሲመጣ ታዩታላችሁ እላችኋለሁ።” በዚህ ጊዜ የካህናት አለቃው በብስጭት ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ተናግሮአል! እናንተም ስድቡን ሰምታችኋል! ከዚህ የበለጠ ምን ምስክር ያስፈልጋል! ታዲያ፥ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ሲሉ መለሱ። በዚያን ጊዜ ምራቃቸውን ተፉበት፤ ጎሸሙት፤ በጥፊም እየመቱት፥ “መሲሕ ሆይ! ማን ነው የመታህ? እስቲ ትንቢት ተናገር” ይሉት ነበር።

ማቴዎስ 26:57-68 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስን የያዙት ሰዎች፥ ጻፎችና ሽማግሌዎች ወደ ተሰበሰቡበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት። ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህኑ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፤ የነገሩንም ፍጻሜ ለማየት ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ። ሊቃነ ካህናትና ሸንጎው ሁሉ ሊገድሉት ፈልገው በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን አላገኙም፤ብዙ የሐሰት ምስክሮች ቢመጡም ምንም አላገኙም፤ በመጨረሻም ሁለት መጥተው፥ “ይህ ሰው ‘የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ’ ብሏል፤” አሉ። ሊቀ ካህኑም ተነሥቶ “እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን?” አለው። ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህኑም “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ከሆንህ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” አለው። ኢየሱስም “አንተ አልህ፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥና በሰማይ ደመና ሲመጣ ታዩታላችሁ” አለው። በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህኑ ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ “ተሳድቦአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን መያዝ ለምን ያስፈልገናል? እነሆ አሁን ስድቡን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል?” እነርሱም “ሞት ይገባዋል!” ብለው መለሱ። በዚያን ጊዜ ፊቱ ላይ ተፉበት፥ መቱት፥ በጥፊም መቱት እንዲህም አሉት “ክርስቶስ ሆይ! እስቲ ትንቢት ተናገርልን፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው?”