ማቴዎስ 25:1-30

ማቴዎስ 25:1-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ፥ ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩል ሌሊትም ሲሆን ‘እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፤ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ፤’ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን፤’ አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው ‘ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ፤’ አሉአቸው። ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፤ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን፤’ አሉ። እርሱ ግን መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም፤’ አለ። ቀኒቱንና ስዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። “ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዐቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት፤ ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት፤’ አለ። ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፥ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ፤’ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት፤’ አለ። ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ፤’ አለው። አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ፤’ አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው ‘አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፤ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት ዐሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፤ ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።’

ማቴዎስ 25:1-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“በዚያ ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ ዐሥር ልጃገረዶችን ትመስላለች። ከእነርሱም ዐምስቱ ልጃገረዶች ዝንጉዎች፣ ዐምስቱ ደግሞ አስተዋዮች ነበሩ፤ ዝንጉዎቹ መብራት ይዘው መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር። አስተዋዮቹ ግን ከመብራታቸው ጋራ መጠባበቂያ ዘይት በማሰሮ ይዘው ነበር። ሙሽራው በዘገየ ጊዜ፣ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ። “እኩለ ሌሊት ላይ፣ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጥሪ ተሰማ። “በዚህ ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሥተው መብራቶቻቸውን እየተረኰሱ መዘጋጀት ያዙ። ዝንጉዎቹ አስተዋዮቹን፣ ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለ ሆነ፣ ከዘይታችሁ ስጡን’ አሏቸው። “አስተዋዮቹ ልጃገረዶች ግን መልሰው፣ ‘ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፣ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ’ አሏቸው። “ዘይት ሊገዙ እንደ ሄዱ፣ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ልጃገረዶችም ወደ ሰርጉ ግብዣ ዐብረውት ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። “ዘግየት ብለው ሌሎቹ ልጃገረዶች መጥተው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በሩን ክፈትልን’ አሉ። “እርሱ ግን መልሶ፣ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው። “እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ። “የእግዚአብሔር መንግሥት ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት በዐደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሊሄድ የተነሣ አንድ ሰውን ትመስላለች፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በመደልደል ለአንዱ ዐምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጥቶ ጕዞውን ቀጠለ። ዐምስት ታላንት የተቀበለው ሰው፣ ወዲያው በገንዘቡ ንግድ ጀምሮ ዐምስት ታላንት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሁለት አተረፈ፤ አንድ ታላንት የተቀበለው ግን መሬት ቈፍሮ የጌታውን ገንዘብ ደበቀ። “የባሪያዎቹም ጌታ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከሄደበት ተመልሶ የሰጣቸውን ገንዘብ ተሳሰበ። ዐምስት ታላንት የተቀበለውም፣ ሌላ ዐምስት ተጨማሪ ታላንት ይዞ በመቅረብ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ዐምስት ታላንት ዐደራ ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸውልህ ዐምስት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ ባሪያ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “እንዲሁም ሁለት ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ሁለት ታላንት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ይኸው ሁለት ተጨማሪ ታላንት አትርፌአለሁ’ አለው። “ጌታውም፣ ‘ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ ባሪያ፤ በትንሽ ነገር ላይ ታማኝ ስለ ሆንህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። “አንድ ታላንት የተቀበለው አገልጋይ ቀርቦ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁህ፤ ሄጄም መሬት ቈፍሬ ታላንትህን ጕድጓድ ውስጥ ደበቅሁት፤ ገንዘብህ ይኸውልህ’ አለው። “ጌታውም መልሶ፣ ‘አንተ ክፉ፣ ሰነፍ ባሪያ፤ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ መሆኔን ታውቅ ኖሯል? ታዲያ፣ በምመለስበት ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እንዳገኘው ለለዋጮች መስጠት ይገባህ ነበር። “ ‘በሉ እንግዲህ ታላንቱን ወስዳችሁ ዐሥር ታላንት ላለው ስጡ፤ ላለው ይጨመርለታል፤ ይትረፈረፍለታልም፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ይህን የማይረባ ባሪያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት’ አለ።

ማቴዎስ 25:1-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው። ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቍኦነጃጅት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ። እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ። ቀኒቱንና ስዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ። አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቍኦፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ፦ ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ። ጌታውም፦ መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው። አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ። ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር። ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።

ማቴዎስ 25:1-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማይ መብራታቸውን ይዘው፥ ሙሽራ ለመቀበል የወጡትን ዐሥር ልጃገረዶች ትመስላለች። ከእነርሱ አምስቱ ሞኞች፥ አምስቱ ብልኆች ነበሩ። ሞኞቹ ልጃገረዶች መብራታቸውን ቢይዙም ለመብራቱ የሚሆን ትርፍ ዘይት አልያዙም ነበር። ብልኆቹ ልጃገረዶች ግን ከመብራታቸው ጋር ትርፍ ዘይት በዕቃ ይዘው ነበር፤ ሙሽራው በመዘግየቱ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጭኖአቸው ተኙ። “እኩለ ሌሊት ሲሆን ግን ‘እነሆ፥ ሙሽራው መጣ! ውጡና ተቀበሉት!’ የሚል ውካታ ተሰማ። በዚያን ጊዜ ልጃገረዶቹ ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሞኞቹ ልጃገረዶች ብልኆቹን መብራታችን መጥፋቱ ስለ ሆነ እባካችሁ ከዘይታችሁ ስጡን አሏቸው። ብልኆቹ ልጃገረዶች ግን ‘ለእኛና ለእናንተ የሚበቃ ዘይት የለንም። ይልቅስ ወደ ሱቅ ሂዱና ለእናንተ የሚሆን ዘይት ግዙ’ ሲሉ መለሱላቸው። ሞኞቹ ልጃገረዶች፥ ዘይት ለመግዛት በሄዱበት ወቅት ሙሽራው መጣ። ተዘጋጅተው የነበሩትም ልጃገረዶች ከሙሽራው ጋር ወደ ሠርጉ ግብዣ አዳራሽ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። “በኋላም የቀሩት ልጃገረዶች መጡና፦ ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! እባክህ ክፈትልን!’ አሉት። እርሱ ግን፥ ‘በእውነት እላችኋለሁ፤ እኔ አላውቃችሁም!’ ሲል መለሰላቸው። ስለዚህ ቀኑንና ሰዓቱን ስለማታውቁ ተግታችሁ ጠብቁ።” ኢየሱስም እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦ “በዚያን ጊዜ ወደ መንግሥተ ሰማይ የመግባት ሁኔታ እንዲህ ይሆናል፦ አንድ ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው አገልጋዮቹን ጠርቶ ንብረቱን እንዳስረከባቸው ዐይነት ይሆናል። ጌትዮው ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው በማካፈል፥ ለአንዱ አምስት መክሊት፥ ለአንዱ ሁለት መክሊት፥ ለአንዱ ደግሞ አንድ መክሊት ሰጠና ወደ ሌላ አገር ሄደ። አምስት መክሊት የተቀበለው ወዲያውኑ ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ። ሁለት መክሊት የተቀበለውም እንዲሁ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፈ። አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሄደና መሬት ቆፍሮ የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። “ከብዙ ጊዜ በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ መጣና ከአገልጋዮቹ ጋር መተሳሰብ ጀመረ። አምስት መክሊት የተቀበለው አገልጋይ ወደ ጌታው መጣና አምስት መክሊት አቅርቦ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ! ሌላ አምስት መክሊት አትርፌአለሁ!’ አለ። ጌታውም ‘መልካም አደረግህ፤ አንተ ታማኝና ደግ አገልጋይ! በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ና የጌታህን ደስታ ለመካፈል ግባ!’ አለው። ሁለት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ ሌላ ሁለት መክሊት አትርፌአለሁ!’ አለ። ጌታውም ‘መልካም ነው! አንተ ታማኝና መልካም አገልጋይ በጥቂት ነገር ታማኝ ሆነህ ስለ ተገኘህ በብዙ ነገር ላይ እሾምሃለሁ፤ ና የጌታህን ደስታ ለመካፈል ግባ!’ አለው። አንድ መክሊት የተቀበለውም ቀርቦ፥ ‘ጌታ ሆይ! ካልዘራህበት የምታጭድ፥ ካልበተንክበት የምትሰበስብ፥ ጨካኝ ሰው መሆንክን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ ፈራሁና ሄጄ ገንዘብህን በመሬት ውስጥ ቀበርኩት፤ ይኸውልህ ገንዘብህ!’ አለው። ጌታው ግን እንዲህ አለው፤ ‘አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ! ካልዘራሁበት እንደማጭድ ካልበተንኩበት እንደምሰበስብ የምታውቅ ከሆነ፥ ገንዘቤን በባንክ ማስቀመጥ ነበረብህ፤ እኔም በመጣሁ ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እወስድ ነበር። በሉ ገንዘቡን ተቀበሉና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት። ላለው ሰው ሁሉ ይጨመርለታል ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ይህን የማይረባ አገልጋይ ግን በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።’

ማቴዎስ 25:1-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ለመቀበል የወጡትን ዐሥር ደናግል ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሞኞች አምስቱ ደግሞ ብልሆች ነበሩ። ሞኞቹ መብራታቸውን ይዘው ነገር ግን ዘይት አልያዙም ነበር፤ ብልሆቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮ ዘይት ይዘው ነበር። ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ፥ ሁሉም እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ። እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ ‘እነሆ ሙሽራው፤ ልትቀበሉት ውጡ’ የሚል ጩኸት ተሰማ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ደናግል ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሞኞቹ ብልሆቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ነውና ከዘይታችሁ ስጡን’ አሉአቸው። ብልሆቹ ግን ‘ለእኛና ለእናንተ ላይበቃ ይችላል፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ’ ሲሉ መለሱላቸው። ሊገዙ በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፤ ተዘጋጅተው የነበሩት ከእርሱ ጋር ወደ ሰርጉ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። ከዚህ በኋላ የቀሩቱ ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ! ጌታ ሆይ! ክፈትልን’ አሉት። እርሱ ግን ‘እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም’ ሲል መለሰላቸው። ቀኑንና ሰዓቱን አታውቁምና ነቅታችሁ ጠብቁ። “እንግዲህ ወደ ሌላ አገር ሊሄድ ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ንብረት እንደሰጣቸው ሰው ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፥ ለአንዱ አምስት መክሊት፥ ለአንዱ ሁለት፥ ለአንዱ ደግሞ አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ወደ ሌላ አገር ሄደ። አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት አተረፈ፤ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ የተቀበለው ግን ሄደና ምድርን ቆፍሮ የጌታውን ገንዘብ ቀበረ። ከብዙ ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባርያዎች ጌታ መጥቶ ከእነርሱ ጋር መተሳሰብ ጀመረ። አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አምጥቶ ‘ጌታ ሆይ! አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁ’ አለ። ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ መልካምና ታማኝ አገልጋይ፥ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። ባለ ሁለት መክሊቱም ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁ’ አለ። ጌታውም ‘መልካም፥ አንተ መልካምና ታማኝ አገልጋይ፥ በጥቂቱ ታምነሃልና በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ’ አለው። አንድ መክሊት የተቀበለውም ደግሞ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! ካልዘራህበት የምታጭድ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንህ አውቃለሁ፤ ስለፈራሁም ሄጄ መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ የራስህ ይኸውልህ’ አለ። ጌታውም እንዲህ ሲል መለሰለት ‘አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባርያ፥ ካልዘራሁበት እንደማጭድ ካልበተንሁበትም እንደምሰበስብ ታውቃለህን? ስለዚህ ገንዘቤን ለገንዘብ ለዋጮች መስጠት ነበረብህ፤ እኔም በመጣሁ ጊዜ ያለኝን ከነወለዱ እወስደው ነበር። በሉ እንግዲህ መክሊቱን ውሰዱበትና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፤ ይበዛለታልም፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። የማይረባውን ባርያ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።’