ማቴዎስ 22:36-46 - ሁሉንም ስሪቶች ያወዳድሩ
ማቴዎስ 22:36-46 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
“መምህር ሆይ፤ ከሕግ ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ትእዛዝ ነው?” እርሱም እንዲህ አለው፤ “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፤’ ይህ የመጀመሪያውና ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ነው፤ ሁለተኛውም ያንኑ ይመስላል፤ ይህም፣ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚለው ነው፤ ሕግና ነቢያት በሙሉ በእነዚህ ሁለት ትእዛዞች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው።” ፈሪሳውያን ተሰብስበው ሳሉ ኢየሱስ፣ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው?” እነርሱም፣ “የዳዊት ልጅ ነው” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ታዲያ፣ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ለምን ‘ጌታዬ’ ይለዋል? ለምንስ፣ እንዲህ ይለዋል? “ ‘ጌታ ጌታዬን፤ “ጠላቶችህን ከእግሮችህ በታች እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ።” ’ ስለዚህ ዳዊት፣ ‘ጌታዬ’ ብሎ ከጠራው፣ እንዴት ልጁ ሊሆን ይችላል?” አንድ ቃል ሊመልስለት የቻለ ወይም ከዚያ ቀን ጀምሮ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።
ማቴዎስ 22:36-46 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
“መምህር ሆይ! ከሕግ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጥ ትእዛዝ የትኛው ነው?” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “ጌታ አምላክህን በሙሉ ልብህ፥ በሙሉ ነፍስህ፥ በሙሉ ሐሳብህ ውደድ፤ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ይህ ነው። ይህንንም የሚመስለው ሁለተኛው ትእዛዝ፥ ‘ጐረቤትህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤’ የሚለው ነው። የሕግና የነቢያት ትምህርት ሁሉ የተመሠረቱት በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዞች ላይ ነው።” ፈሪሳውያን ተሰብስበው ሳሉ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ “ስለ መሲሕ ምን ትላላችሁ? የማንስ ልጅ ይመስላችኋል?” እነርሱም “የዳዊት ልጅ ነው” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ታዲያ፥ ዳዊት በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርቶ በተናገረ ጊዜ እንዴት ‘ጌታ’ ብሎ ጠራው? ‘እግዚአብሔር ለጌታዬ ጠላቶችህን በእግርህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ!’ አለው። እንግዲህ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ብሎ ከጠራው ታዲያ መሲሕ እንዴት ልጁ ሊሆን ይችላል?” በዚህ አንድ ቃል እንኳ ሊመልስለት የቻለ ማንም ሰው አልነበረም፤ ከዚያን ቀን ጀምሮም ጥያቄ ሊያቀርብለት የደፈረ ማንም አልነበረም።
ማቴዎስ 22:36-46 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
“መምህር ሆይ! ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው “ ‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።’ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም ‘ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ፤’ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።” ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ “ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። “የዳዊት ልጅ ነው፤” አሉት። እርሱም “እንኪያስ ዳዊት ‘ጌታ ጌታዬን “ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ፤” አለው፤’ ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል?” አላቸው። አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፤ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።
ማቴዎስ 22:36-46 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል። ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ፦ ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት። እርሱም፦ እንኪያስ ዳዊት፦ ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው። አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፥ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።
ማቴዎስ 22:36-46 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
“መምህር ሆይ! ከሕግ ማንኛይቱ ትእዛዝ ትበልጣለች?” እርሱም እንዲህ አለው “‘ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፥ በፍጹም ነፍስህ፥ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ።’ ታላቂቱና የመጀመሪያይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርሷም ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤’ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕግና ነቢያት ሁሉ ተንጠልጥለዋል።” ፈሪሳውያን ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “ስለ ክርስቶስ ምን ትላላችሁ? የማንስ ልጅ ነው?” እነርሱም “የዳዊት ልጅ ነው” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ ታዲያ ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ እንዴት ጌታ ብሎ ጠራው እንዲህ ሲል፦ ጌታ ጌታዬን “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው፤ “ዳዊት ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ሊሆን ይችላል?” አንድም ቃል እንኳ ሊመልስለት የቻለ ማንም አልነበረም፤ ከዚያ ቀን ጀምሮ ሊጠይቀው የደፈረ አንድስ እንኳ አልነበረም።