ማቴዎስ 22:1-22
ማቴዎስ 22:1-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም መለሰ ደግሞም በምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ፤ ሊመጡም አልወደዱም። ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ ‘የታደሙትን እነሆ፥ ድግሴን አዘጋጀሁ፤ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ፤ በሉአቸው፤’ አለ። እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው፤ ገደሉአቸውም። ንጉሡም ተቈጣ፤ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። በዚያን ጊዜ ባሮቹን ‘ሰርጉ ተዘጋጅቶአል፤ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤ እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ፤’ አለ። እነዚያም ባሮች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት። “ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየና ‘ወዳጄ ሆይ! የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?’ አለው እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፤’ አለ። የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።” ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ ዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ጋር ላኩበት፤ እነርሱም “መምህር ሆይ! እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፤ ለማንምም አታደላም፤ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤ እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሳር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም?” አሉት። ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ “እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? የግብሩን ብር አሳዩኝ፤” አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት። እርሱም “ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት?” አላቸው። “የቄሳር ነው፤” አሉት። በዚያን ጊዜ “እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ፤” አላቸው። ይህንም ሰምተው ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ።
ማቴዎስ 22:1-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስም እንደ ገና እንዲህ የሚል ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ለልጁ ሰርግ የደገሰን ንጉሥ ትመስላለች፤ ንጉሡም የተጋበዙትን ሰዎች እንዲጠሩ ባሮቹን ላከ፤ እነርሱ ግን አንመጣም አሉ። “እንደ ገናም ሌሎች ባሮች ልኮ፣ ‘የተጋበዙትን፣ እነሆ፣ በሬዎችንና የሠቡ ከብቶቼን ዐርጄ ድግሱን አዘጋጅቻለሁ፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ስለ ሆነ፣ ወደ ሰርጉ ኑ በሏቸው’ አለ። “ተጋባዦቹ ግን ጥሪውን ችላ ብለው፣ አንዱ ወደ ዕርሻው ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባሮቹን በመያዝ አጕላልተው ገደሏቸው። ንጉሡም በመቈጣት ሰራዊቱን ልኮ ገዳዮቻቸውን አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። “ከዚያም ባሮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘የሰርጉ ድግስ ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የተጋበዙት የሚገባቸው ሆነው ስላልተገኙ፣ ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ድግስ ጥሩ።’ ባሮቹም ወደ ጐዳናዎች ወጥተው ያገኙትን መልካሙንም ክፉውንም ሁሉ ሰብስበው የሰርጉን አዳራሽ በእንግዶች ሞሉት። “ንጉሡም የተጋበዙትን እንግዶች ለማየት ሲገባ፣ አንድ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየ፤ እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልህ?’ ሰውየው ግን የሚመልሰው ቃል አልነበረውም። “ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤ “የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።” ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ወጥተው በመሄድ በአፍ ዕላፊ እንዴት እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ወገኖች ጋራ ወደ እርሱ ልከው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛና የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት የምታስተምር እንደ ሆንህ፣ ለማንም ሳታደላ ሁሉን እኩል እንደምትመለከት እናውቃለን፤ ስለዚህ ንገረን፤ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን በመረዳት እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ግብዞች ለምን በነገር ልታጠምዱኝ ትሻላችሁ? ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስኪ አሳዩኝ።” እነርሱም አንድ ዲናር አመጡለት። እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” አሉት። እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተዉትም ሄዱ።
ማቴዎስ 22:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም መለሰ ደግሞም በምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም። ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ፦ የታደሙትን፦ እነሆ፥ ድግሴን አዘጋጀሁ፥ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፥ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ በሉአቸው አለ። እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው ገደሉአቸውም። ንጉሡም ተቍኦጣ፥ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። በዚያን ጊዜ ባሮቹን፦ ሰርጉስ ተዘጋጅቶአል፥ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤ እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ አለ። እነዚያም ባሮች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት። ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየና፦ ወዳጄ ሆይ፥ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን፦ እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል አለ። የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና። ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ መዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ጋር ላኩበት፥ እነርሱም፦ መምህር ሆይ፥ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፥ ለማንምም አታደላም፥ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤ እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? አሉት። ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ፦ እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ? የግብሩን ብር አሳዩኝ አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት። እርሱም፦ ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው። የቄሣር ነው አሉት። በዚያን ጊዜ፦ እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው። ይህንም ሰምተው ተደነቁ፥ ትተውትም ሄዱ።
ማቴዎስ 22:1-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንደገናም ኢየሱስ በምሳሌ እንዲህ እያለ ይነግራቸው ነበር፤ “መንግሥተ ሰማይ ለልጁ የሠርግ ድግስ የደገሰውን ንጉሥ ትመስላለች። ንጉሡ የተጠሩትን ሰዎች ወደ ሠርጉ እንዲመጡ ለማሳሰብ አገልጋዮቹን ወደ እነርሱ ላከ፤ ሰዎቹ ግን ወደ ሠርጉ ሊመጡ አልፈለጉም። “ንጉሡ ሌሎች አገልጋዮችን እንደገና እንዲህ ሲል ላከ፤ ‘ወደ ተጠሩት ሰዎች ሂዱና፦ እነሆ፥ የሠርግ ድግሴን አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ፍሪዳዎቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶአል፤ ስለዚህ ወደ ሠርጉ ግብዣ ኑ!’ ብላችሁ ንገሩአቸው። እነርሱ ግን ነገሩን ችላ ብለው በየፊናቸው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ደግሞ አገልጋዮቹን ይዘው በማዋረድ ደበደቡና ገደሉአቸው፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተቈጣና ወታደሮቹን ልኮ እነዚያን ገዳዮች አስገደለ፤ ከተማቸውንም በእሳት እንዲያቃጥሉ አደረገ፤ ከዚህ በኋላ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘እነሆ፥ የሠርጉ ድግስ ተዘጋጅቶአል፤ የተጠሩት ግን ለግብዣው የተገቡ አልሆኑም። ስለዚህ በየአውራ ጐዳናው ሂዱና ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ወደ ሠርጉ ግብዣ ጥሩ።’ አገልጋዮቹም በየመንገዱ ሄደው፥ ያገኙትን ሰው ሁሉ ክፉዎችንም፥ ደጎችንም ሰበሰቡ፤ ስለዚህ የሠርጉ አዳራሽ በተጋባዦች ተሞላ። “ነገር ግን ንጉሡ ተጋባዦቹን ለማየት ወደ አዳራሽ በገባ ጊዜ፥ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው በዚያ አየ። እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?’ ሰውየው ግን ዝም አለ። ንጉሡም አገልጋዮቹን፦ ‘እጅና እግሩን እሰሩና አውጥታችሁ በውጪ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አለ።” ቀጥሎም ኢየሱስ “ስለዚህ የተጠሩ ብዙዎች ናቸው፤ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው” አለ። ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው ኢየሱስን በንግግሩ እንደሚያጠምዱት ተማከሩ፤ የእነርሱንም ደቀ መዛሙርት ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ወደ ኢየሱስ ልከው፥ “መምህር ሆይ! አንተ እውነተኛ መሆንህንና የእግዚአብሔርን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፤ ሰውንም በመፍራት የምታደርገው ነገር የለም፤ ለሰውም አታዳላም” ካሉት በኋላ፥ እንዲህ ብለው ጠየቁት። “በል እስቲ ንገረን ምን ይመስልሃል? ለሮማው ንጉሠ ነገሥት ግብር መክፈል ሕጋዊ ነውን ወይስ አይደለም?” ኢየሱስ ግን ክፋታቸውን ዐውቆ፥ “እናንተ ግብዞች! ስለምን ትፈትኑኛላችሁ? ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስቲ አሳዩኝ!” አላቸው። ስለዚህ እነርሱ አንድ ዲናር አምጥተው አሳዩት። እርሱም፥ “በዚህ ገንዘብ ላይ የተቀረጸው መልክና የተጻፈው ስም የማን ነው?” ሲል ጠየቃቸው፤ እነርሱም፥ “የሮማው ንጉሠ ነገሥት ነው!” አሉት፤ እርሱም፥ “እንግዲያውስ የንጉሡን ለንጉሡ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ፤” አላቸው። እነርሱም ከሰሙት በኋላ በአነጋገሩ ተደንቀው ትተውት ሄዱ።
ማቴዎስ 22:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስ አሁንም በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ የደገሰ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም ወደ ሰርጉ እንዲጠሩ ባርያዎቹን ላከ፤ እነርሱ ግን ሊመጡ አልፈለጉም። ሌሎች ባርያዎችን ደግሞ ልኮ ‘የታደሙትን እነሆ ድግሴን አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ግብዣ ኑ፤ በሉአቸው፤’ አለ። እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባርያዎቹን ይዘው ሰደቡአቸው፤ ገደሉአቸውም። ንጉሡም ተቆጣ፤ ወታደሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። በዚያን ጊዜ ባርያዎቹን እንዲህ አላቸው ‘ሰርጉ ተዘጋጅቶአል፤ የታደሙት ግን የተገቡ አልሆኑም፤ ስለዚህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ።’ እነዚያም ባርያዎች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንና በጎዎችን ሰበሰቡ፤ የሰርጉም ቤት በተጋባዦች ተሞላ። “ንጉሡም ተጋባዦቹን ለማየት በገባ ጊዜ፥ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው በዚያ አየ። ‘ወዳጄ ሆይ! የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?’ አለው እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፤’ አለ። የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።” ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በንግግሩ እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ሰዎች ጋር ላኩበት፤ እነርሱም እንዱህ አሉት “መምህር ሆይ! እውነተኛ እንደሆንህ የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፤ ለማንምም አታደላም፤ የሰውን ፊት አታይምና፤ ምን ይመስልሃል? እስቲ ንገረን፥ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው “እናንተ ግብዞች፥ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? ለግብር የሚከፈለውን ብር አሳዩኝ።” እነርሱም ዲናር አመጡለት። እርሱም “ይህ መልክና ጽሑፉ የማን ነው?” አላቸው። እነርሱም “የቄሣር ነው” አሉት። እርሱም “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” አላቸው። ይህንንም ሰምተው ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ።