ማቴዎስ 22:1-14

ማቴዎስ 22:1-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢየሱስም መለሰ ደግሞም በምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ፤ ሊመጡም አልወደዱም። ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ ‘የታደሙትን እነሆ፥ ድግሴን አዘጋጀሁ፤ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ፤ በሉአቸው፤’ አለ። እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው፤ ገደሉአቸውም። ንጉሡም ተቈጣ፤ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። በዚያን ጊዜ ባሮቹን ‘ሰርጉ ተዘጋጅቶአል፤ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤ እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ፤’ አለ። እነዚያም ባሮች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት። “ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየና ‘ወዳጄ ሆይ! የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?’ አለው እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፤’ አለ። የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።”

ማቴዎስ 22:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስም እንደ ገና እንዲህ የሚል ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ለልጁ ሰርግ የደገሰን ንጉሥ ትመስላለች፤ ንጉሡም የተጋበዙትን ሰዎች እንዲጠሩ ባሮቹን ላከ፤ እነርሱ ግን አንመጣም አሉ። “እንደ ገናም ሌሎች ባሮች ልኮ፣ ‘የተጋበዙትን፣ እነሆ፣ በሬዎችንና የሠቡ ከብቶቼን ዐርጄ ድግሱን አዘጋጅቻለሁ፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ስለ ሆነ፣ ወደ ሰርጉ ኑ በሏቸው’ አለ። “ተጋባዦቹ ግን ጥሪውን ችላ ብለው፣ አንዱ ወደ ዕርሻው ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባሮቹን በመያዝ አጕላልተው ገደሏቸው። ንጉሡም በመቈጣት ሰራዊቱን ልኮ ገዳዮቻቸውን አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። “ከዚያም ባሮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘የሰርጉ ድግስ ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የተጋበዙት የሚገባቸው ሆነው ስላልተገኙ፣ ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ድግስ ጥሩ።’ ባሮቹም ወደ ጐዳናዎች ወጥተው ያገኙትን መልካሙንም ክፉውንም ሁሉ ሰብስበው የሰርጉን አዳራሽ በእንግዶች ሞሉት። “ንጉሡም የተጋበዙትን እንግዶች ለማየት ሲገባ፣ አንድ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየ፤ እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልህ?’ ሰውየው ግን የሚመልሰው ቃል አልነበረውም። “ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤ “የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”

ማቴዎስ 22:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስም መለሰ ደግሞም በምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም። ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ፦ የታደሙትን፦ እነሆ፥ ድግሴን አዘጋጀሁ፥ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፥ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ በሉአቸው አለ። እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው ገደሉአቸውም። ንጉሡም ተቍኦጣ፥ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። በዚያን ጊዜ ባሮቹን፦ ሰርጉስ ተዘጋጅቶአል፥ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤ እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ አለ። እነዚያም ባሮች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት። ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየና፦ ወዳጄ ሆይ፥ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን፦ እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል አለ። የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።

ማቴዎስ 22:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እንደገናም ኢየሱስ በምሳሌ እንዲህ እያለ ይነግራቸው ነበር፤ “መንግሥተ ሰማይ ለልጁ የሠርግ ድግስ የደገሰውን ንጉሥ ትመስላለች። ንጉሡ የተጠሩትን ሰዎች ወደ ሠርጉ እንዲመጡ ለማሳሰብ አገልጋዮቹን ወደ እነርሱ ላከ፤ ሰዎቹ ግን ወደ ሠርጉ ሊመጡ አልፈለጉም። “ንጉሡ ሌሎች አገልጋዮችን እንደገና እንዲህ ሲል ላከ፤ ‘ወደ ተጠሩት ሰዎች ሂዱና፦ እነሆ፥ የሠርግ ድግሴን አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ፍሪዳዎቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶአል፤ ስለዚህ ወደ ሠርጉ ግብዣ ኑ!’ ብላችሁ ንገሩአቸው። እነርሱ ግን ነገሩን ችላ ብለው በየፊናቸው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ደግሞ አገልጋዮቹን ይዘው በማዋረድ ደበደቡና ገደሉአቸው፤ በዚህ ጊዜ ንጉሡ ተቈጣና ወታደሮቹን ልኮ እነዚያን ገዳዮች አስገደለ፤ ከተማቸውንም በእሳት እንዲያቃጥሉ አደረገ፤ ከዚህ በኋላ አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘እነሆ፥ የሠርጉ ድግስ ተዘጋጅቶአል፤ የተጠሩት ግን ለግብዣው የተገቡ አልሆኑም። ስለዚህ በየአውራ ጐዳናው ሂዱና ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ወደ ሠርጉ ግብዣ ጥሩ።’ አገልጋዮቹም በየመንገዱ ሄደው፥ ያገኙትን ሰው ሁሉ ክፉዎችንም፥ ደጎችንም ሰበሰቡ፤ ስለዚህ የሠርጉ አዳራሽ በተጋባዦች ተሞላ። “ነገር ግን ንጉሡ ተጋባዦቹን ለማየት ወደ አዳራሽ በገባ ጊዜ፥ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው በዚያ አየ። እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?’ ሰውየው ግን ዝም አለ። ንጉሡም አገልጋዮቹን፦ ‘እጅና እግሩን እሰሩና አውጥታችሁ በውጪ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አለ።” ቀጥሎም ኢየሱስ “ስለዚህ የተጠሩ ብዙዎች ናቸው፤ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸው” አለ።

ማቴዎስ 22:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስ አሁንም በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ የደገሰ ንጉሥን ትመስላለች። የታደሙትንም ወደ ሰርጉ እንዲጠሩ ባርያዎቹን ላከ፤ እነርሱ ግን ሊመጡ አልፈለጉም። ሌሎች ባርያዎችን ደግሞ ልኮ ‘የታደሙትን እነሆ ድግሴን አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ግብዣ ኑ፤ በሉአቸው፤’ አለ። እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም ባርያዎቹን ይዘው ሰደቡአቸው፤ ገደሉአቸውም። ንጉሡም ተቆጣ፤ ወታደሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። በዚያን ጊዜ ባርያዎቹን እንዲህ አላቸው ‘ሰርጉ ተዘጋጅቶአል፤ የታደሙት ግን የተገቡ አልሆኑም፤ ስለዚህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ።’ እነዚያም ባርያዎች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንና በጎዎችን ሰበሰቡ፤ የሰርጉም ቤት በተጋባዦች ተሞላ። “ንጉሡም ተጋባዦቹን ለማየት በገባ ጊዜ፥ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው በዚያ አየ። ‘ወዳጄ ሆይ! የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ?’ አለው እርሱም ዝም አለ። በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል፤’ አለ። የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።”