ማቴዎስ 21:33-44

ማቴዎስ 21:33-44 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፤ መጥመቂያም ማሰለት፤ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱንም ገደሉት፤ ሌላውንም ወገሩት። ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፤ እንዲሁም አደረጉባቸው። በኋላ ግን ‘ልጄንስ ያፍሩታል፤’ ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፤ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ፤’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል?” እነርሱም “ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል፤” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’ የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች፤ ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።”

ማቴዎስ 21:33-44 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ አንድ የዕርሻ ባለቤት የወይን ተክል ተከለ፤ በዙሪያውም ዐጥር ዐጠረ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠራ፤ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል ባሮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው። “ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች ባሮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም፣ ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከ። “ነገር ግን ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ ዕርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “ታዲያ የወይኑ ዕርሻ ባለቤት ሲመጣ፣ እነዚያን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” እነርሱም፣ “እነዚያን ክፉዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ከወይኑ ዕርሻ ተገቢውን ፍሬ በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። ኢየሱስም፣ “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማእዘን ራስ ሆነ፤ ጌታ ይህን አድርጓል፤ ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው።’ ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን አላነበባችሁምን?” አላቸው። “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች፤ በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ ደግሞ የሚወድቅበትን ማንኛውንም ሰው ይፈጨዋል።”

ማቴዎስ 21:33-44 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት። ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው። በኋላ ግን፦ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፦ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል? እነርሱም፦ ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።

ማቴዎስ 21:33-44 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ የወይን አትክልት የተከለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ በወይኑ አትክልት ዙሪያ አጥር ዐጠረ፤ የወይን መጭመቂያ የሚሆን ጒድጓድ ቆፍሮ አበጀ፤ ለወይኑ ጥበቃ የሚያገለግል ረዥም ግንብ ሠራ፤ ከዚህ በኋላ የአትክልቱን ቦታ ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የፍሬ ወራት በደረሰ ጊዜ ድርሻውን እንዲቀበሉለት አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹ ግን አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። የወይኑ አትክልት ባለቤት እንደገና ቊጥራቸው ከፊተኞቹ የሚበልጥ ሌሎችን አገልጋዮች ደግሞ ላከ። ገበሬዎቹ በእነርሱም ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም የወይኑ አትክልት ጌታ ‘ልጄንስ ያከብሩታል!’ በማለት ልጁን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እኛ እንውረስ!’ ተባባሉ። ልጁንም ይዘው ከወይን አትክልቱ ቦታ ውጪ ወሰዱና ገደሉት። “ታዲያ፥ የወይኑ አትክልት ባለቤት በመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” እነርሱም “የእነዚህን ክፉ ሰዎች ፍጻሜ የከፋ ያደርገዋል። የወይኑንም ተክል ቦታ ፍሬውን በየጊዜው ለሚሰጡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “በቅዱሳት መጻሕፍት ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ ዋና የማእዘን ራስ ሆነ፤ ይህም የጌታ ሥራ ነው፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’ ተብሎ የተጻፈውን ከቶ አላነበባችሁምን? “ስለዚህ እንዲህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬ ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች። [ በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበት ሰው ግን ይጨፈለቃል።”]

ማቴዎስ 21:33-44 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ የወይን አትክልት የተከለ አንድ የእርሻ ባለቤት ነበረ፤ እርሱም ቅጥር ቀጠረለት፤ መጭመቂያም ማሰለት፤ ግንብም ሠራለት፤ እርሻውንም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበት ወራት በደረሰ ጊዜ፥ ፍሬውን እንዲቀበሉለት ባርያዎቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹም ባርያዎቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበዙ ሌሎች ባርያዎችን ላከ፤ እነርሱንም እንዲሁ አደረጉባቸው። በመጨረሻም ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፤ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት ሥፍራ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ሥፍራ ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” እነርሱም “ክፉዎችን በክፉ ሁኔታ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት ሥፍራ ፍሬውን በየጊዜው ለሚሰጡት ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’ የሚለውን ከቶ በመጽሕፍት አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ያደቅቀዋል።”