ማቴዎስ 21:1-46
ማቴዎስ 21:1-46 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፤ እንዲህም አላቸው “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም አንዳች ቢላችሁ ‘ለጌታ ያስፈልጉታል፤’ በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።” “ለጽዮን ልጅ ‘እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፤’ በሉአት።” ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፤ ተቀመጠባቸውም። ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቍኦረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሣዕና በአርያም!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ “ይህ ማን ነው?” ብሎ ተናወጠ። ሕዝቡም “ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው፤” አሉ። ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት፤” አላቸው። በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ!” እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው “እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን?” አሉት። ኢየሱስም “እሰማለሁ፤ ‘ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ፤’ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው። ትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ፤ በዚያም አደረ። በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና “ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ፤” አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው “በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች?” ብለው ተደነቁ። ኢየሱስም መልሶ “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር፤’ ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ፤” አላቸው። ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና “በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ “እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ወይስ ከሰው?” አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ “ ‘ከሰማይ’ ብንል ‘እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰው’ ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን” አሉ። ለኢየሱስም መልሰው “አናውቅም” አሉት። እርሱም ደግሞ “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም፤” አላቸው። “ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ ‘ልጄ ሆይ! ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ፤’ አለው። እርሱም መልሶ ‘አልወድም፤’ አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ ‘እሺ ጌታዬ፤’ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው?” “ፊተኛው” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፤ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም። “ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፤ መጥመቂያም ማሰለት፤ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱንም ገደሉት፤ ሌላውንም ወገሩት። ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፤ እንዲሁም አደረጉባቸው። በኋላ ግን ‘ልጄንስ ያፍሩታል፤’ ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፤ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ፤’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል?” እነርሱም “ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል፤” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’ የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች፤ ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።” የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤ ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።
ማቴዎስ 21:1-46 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሩሳሌም መቃረቢያ ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ቤተ ፋጌ ወደተባለችው ስፍራ እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤ እንዲህ አላቸው “በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፤ እንደ ደረሳችሁም አንዲት አህያ ከነውርንጫዋ ታስራ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁም ወደ እኔ አምጧቸው። ማንም ሰው ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ ቢላችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልጋሉ፤ እርሱም ወዲያውኑ መልሶ ይልካቸዋል’ በሉት።” ይህ የሆነውም በነቢዩ እንዲህ በማለት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው። “ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሏት፤ ‘እነሆ፤ ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ፣ በአህያዪቱና በግልገሏ፣ በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል።’ ” ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። አህያዪቱንና ውርንጫዋን አምጥተው ልብሶቻቸውን በላያቸው ላይ አኖሩ፤ እርሱም ተቀመጠባቸው። ከሕዝቡም አብዛኛው ልብሶቻቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎቹም ከዛፎች ቅርንጫፍ እየዘነጠፉ በመንገዱ ላይ ያነጥፉ ነበር። ቀድሞት የሚሄደውና ይከተለው የነበረው ሕዝብም እንዲህ እያለ ይጮኽ ነበር፤ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ!” “በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!” “ሆሳዕና በአርያም!” ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም ከተማዋ በመላ፣ “ይህ ማነው?” በማለት ታወከች። ሕዝቡም፣ “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ከዚያም ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሸጡትንና የሚገዙትን አስወጣቸው፤ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ በመገለባበጥ፣ “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን፣ ‘የወንበዴዎች ዋሻ’ አደረጋችሁት” አላቸው። በቤተ መቅደሱም ውስጥ ዐይነ ስውሮችና ሽባዎች ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና የኦሪት ሕግ መምህራን ያደረጋቸውን ታምራትና፣ “ሆሳዕና፤ ለዳዊት ልጅ” እያሉ በመቅደስ የሚጮኹትን ሕፃናት ባዩ ጊዜ በቍጣ ተሞሉ። እነርሱም፣ “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህ?” አሉት። ኢየሱስም፣ “አዎን እሰማለሁ፤ እንዲህ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን? “ ‘ከልጆችና ጡት ከሚጠቡ፣ ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ።’ ” ትቷቸው ከከተማው ወጣ፤ ወደ ቢታንያም ሄዶ በዚያው ዐደረ። ኢየሱስ በማግስቱም ማለዳ ወደ ከተማዪቱ በመመለስ ላይ ሳለ ተራበ፤ በመንገድ ዳርም አንድ የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ ሲሄድ ከቅጠል በቀር ምንም ስላላገኘባት፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ፍሬ አይኑርብሽ!” አላት፤ የበለሷም ዛፍ ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም የሆነውን አይተው በመደነቅ፣ “የበለሷ ዛፍ እንዴት በአንዴ ልትደርቅ ቻለች?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩ፣ በበለሷ ዛፍ ላይ የሆነውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት እንኳ ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ።” ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በማስተማር ላይ ሳለ፣ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ቀርበው፣ “ይህን ሁሉ ነገር የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ሥልጣንስ የሰጠህ ማን ነው?” ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ መልሱን ብትነግሩኝ፣ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት የመጣው ከየት ነበር? ከሰማይ ወይስ ከሰው?” እነርሱም እርስ በርስ በመነጋገር እንዲህ ተባባሉ፤ “ ‘ከሰማይ ነው?’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰዎች ነው’ ብንል ደግሞ፣ ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ ነቢይ እንደ ሆነ ስለሚቈጥር እንፈራለን።” ስለዚህ ለኢየሱስ፣ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። እርሱም፣ “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ምን ይመስላችኋል? ሁለት ወንዶች ልጆች ያሉት አንድ ሰው ነበረ፤ ወደ መጀመሪያው ልጁ ሄዶ፣ ‘ልጄ ሆይ፤ ዛሬ ወደ ወይኑ ቦታ ሄደህ ሥራ’ አለው። “ልጁም፣ ‘አልሄድም’ አለው፤ ኋላ ግን ተጸጽቶ ሄደ። “ወደ ሁለተኛው ልጁ ሄዶ እንደዚያው አለው፤ ልጁም ‘ዕሺ ጌታዬ እሄዳለሁ’ አለው፤ ነገር ግን ሳይሄድ ቀረ። “ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነርሱም፣ “የመጀመሪያው ልጅ” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሟችኋል፤ መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ወደ እናንተ መጣ፤ እናንተ አላመናችሁትም፤ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና አመንዝራዎች ግን አመኑት። የሆነውን ካያችሁ በኋላ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም። “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ አንድ የዕርሻ ባለቤት የወይን ተክል ተከለ፤ በዙሪያውም ዐጥር ዐጠረ፤ ለወይኑ መጭመቂያ ጕድጓድ ቈፈረ፤ ለጥበቃ የሚሆን ማማ ሠራ፤ ከዚያም ዕርሻውን ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የመከር ወራት ሲደርስ፣ ፍሬውን ለመቀበል ባሮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላካቸው። “ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበልጡ ሌሎች ባሮቹን ላከ፤ ገበሬዎቹም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም፣ ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከ። “ነገር ግን ገበሬዎቹ ልጁን ባዩት ጊዜ፣ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ፣ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ ዕርሻ ውጭ አውጥተው ገደሉት። “ታዲያ የወይኑ ዕርሻ ባለቤት ሲመጣ፣ እነዚያን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” እነርሱም፣ “እነዚያን ክፉዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ ከወይኑ ዕርሻ ተገቢውን ፍሬ በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። ኢየሱስም፣ “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማእዘን ራስ ሆነ፤ ጌታ ይህን አድርጓል፤ ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው።’ ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፈውን አላነበባችሁምን?” አላቸው። “ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች፤ በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ ደግሞ የሚወድቅበትን ማንኛውንም ሰው ይፈጨዋል።” የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ፣ ስለ እነርሱ የሚናገር መሆኑን ዐወቁ። ነገር ግን ይዘው ሊያስሩት ቢፈልጉም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን እንደ ነቢይ አድርጎ ይመለከት ስለ ነበር ፈሩ።
ማቴዎስ 21:1-46 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥ እንዲህም አላቸው፦ በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም አንዳች ቢላችሁ፦ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል። ለጽዮን ልጅ፦ እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥ አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፥ ተቀመጠባቸውም። ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቍኦረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም፦ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ፦ ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ። ሕዝቡም፦ ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው አሉ። ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና፦ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው። በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም፦ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቍኦጥተው፦ እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው። ትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ በዚያም አደረ። በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ። በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና፦ ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው፦ በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው ተደነቁ። ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ፦ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው። ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና፦ በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት። ኢየሱስም መልሶ፦ እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ፦ ከሰማይ ብንል፦ እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ። ለኢየሱስም መልሰው፦ አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ፦ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው። ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ፦ ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው። እርሱም መልሶ፦ አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ፦ እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም። ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ። ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት። ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው። በኋላ ግን፦ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፦ ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል? እነርሱም፦ ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤ ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።
ማቴዎስ 21:1-46 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስና ተከታዮቹ ወደ ኢየሩሳሌም በቀረቡ ጊዜ በደብረ ዘይት ወደምትገኘው ቤተ ፋጌ ወደምትባለው መንደር ሲደርሱ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ እዚያም አንዲት የታሰረች አህያ ከነውርንጫዋ ወዲያውኑ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም ሰው አንዳች ነገር ቢላችሁ ‘ጌታ ስለሚፈልጋቸው ነው’ በሉት። እርሱም አህዮቹን ወዲያውኑ ይልካቸዋል።” ይህም የሆነው በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፦ “የጽዮን ከተማ ለምትባለው ለኢየሩሳሌም፦ ‘እነሆ! ንጉሥሽ ትሑት ሆኖ በአህያይቱና በውርንጫዋ ላይ ሆኖ ወደ አንቺ ይመጣል!’ ብላችሁ ንገሩአት።” ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። አህያዋንም ከነውርንጫዋ አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በአህዮቹ ጀርባ ላይ አደረጉ፤ ኢየሱስም በዚያ ላይ ተቀመጠ። ከሕዝቡም ብዙዎቹ ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፍ እየቀጠፉ በመንገድ ላይ ይጐዘጒዙ ነበር። ከሕዝቡም ፊት ለፊት ይሄዱ የነበሩትና ከኋላ ይከተሉ የነበሩት፥ “ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ምስጋና ይሁን! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሳዕና! ምስጋና በአርያም ለእግዚአብሔር ይሁን!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ የከተማው ሰዎች በሙሉ “ይህ ማን ነው?” በማለት ታወኩ። ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ምድር ከምትገኝ ከናዝሬት ከተማ የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዚያም የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሰዎች ሁሉ አስወጣ። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠ። “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት!” አላቸው። ኢየሱስ በቤተ መቅደስ ሳለ ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡና ፈወሳቸው። ነገር ግን የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን ኢየሱስ ያደረገውን ድንቅ ነገር በማየታቸውና ሕፃናትም በቤተ መቅደስ “ለዳዊት ልጅ ሆሳዕና! ምስጋና ይሁን!” እያሉ ሲጮኹ በመስማታቸው ተቈጡ። ስለዚህ ኢየሱስን “እነዚህ ሕፃናት የሚሉትን ትሰማለህን?” አሉት፤ እርሱም “አዎ፥ እሰማለሁ፤ ‘ከልጆችና ከሚጠቡት ሕፃናት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው፤ ትቶአቸውም ከከተማ ወጥቶ ቢታንያ ወደምትባል መንደር ሄደ፤ በዚያም ዐደረ። ኢየሱስ ጠዋት በማለዳ፥ ወደ ከተማ ተመልሶ ሲሄድ ራበው፤ አንዲት የበለስ ዛፍ በመንገድ ዳር አየና ወደ እርስዋ ሄደ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። ስለዚህ “ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ ፍሬ አይገኝብሽ!” አላት። ዛፊቱም ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ፥ “ይህች የበለስ ዛፍ በአንድ አፍታ እንዴት ደረቀች!” በማለት ተገረሙ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “በእውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ቢኖራችሁና ባትጠራጠሩ በበለሲቱ ዛፍ ላይ እንደ ተደረገው ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህንን ተራራ እንኳ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወደ ባሕር ተወርወር!’ ብትሉት ይሆንላችኋል። አምናችሁ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ታገኛላችሁ።” ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ያስተምር ነበር። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀረቡና “ይህን ሁሉ የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ይህን ሥልጣን የሰጠህስ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔም አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፤ ለጥያቄዬ መልስ ከሰጣችሁኝ እኔም ይህን ሁሉ በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። የዮሐንስ ጥምቀት ከየት መጣ? ከእግዚአብሔር ነበረ ወይስ ከሰው?” እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ሲሉ ተመካከሩ፤ “ ‘ከእግዚአብሔር ነው’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም’ ይለናል፤ ‘ከሰው ነው’ ብንል ደግሞ፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያዩት፥ ሕዝቡን እንፈራለን።” ስለዚህ “አናውቅም” ሲሉ ለኢየሱስ መለሱለት። እርሱም “እንግዲያውስ እኔም በምን ሥልጣን ይህን ሁሉ እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ታዲያ ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ከእነርሱ ወደ አንደኛው ቀርቦ፥ ‘ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ወደ ወይን አትክልት ቦታዬ ሄደህ እንድትሠራ ይሁን’ አለው። ልጁም ‘እምቢ አልሄድም’ አለ። ይሁን እንጂ በኋላ ተጸጸተና ሊሠራ ሄደ። አባትየው ወደ ሁለተኛው ልጁ ደግሞ ሄደና እርሱንም እንዲሁ እንዲሠራ አዘዘው፤ ልጁም ‘እሺ አባቴ እሄዳለሁ’ አለ። ነገር ግን አልሄደም። እንግዲህ ከነዚህ ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነርሱም “የመጀመሪያው ነዋ!” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “በእውነት እላችኋለሁ፤ ኃጢአተኞችና ዘማውያን ወደ መንግሥተ ሰማይ በመግባት ይቀድሙአችኋል። መጥምቁ ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ ቢመጣ አላመናችሁትም፤ ኃጢአተኞችና ዘማውያን ግን አመኑት፤ ይህንንም አይታችሁ እንኳ ንስሓ ገብታችሁ አላመናችሁትም።” ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ የወይን አትክልት የተከለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱ በወይኑ አትክልት ዙሪያ አጥር ዐጠረ፤ የወይን መጭመቂያ የሚሆን ጒድጓድ ቆፍሮ አበጀ፤ ለወይኑ ጥበቃ የሚያገለግል ረዥም ግንብ ሠራ፤ ከዚህ በኋላ የአትክልቱን ቦታ ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የፍሬ ወራት በደረሰ ጊዜ ድርሻውን እንዲቀበሉለት አገልጋዮቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹ ግን አገልጋዮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። የወይኑ አትክልት ባለቤት እንደገና ቊጥራቸው ከፊተኞቹ የሚበልጥ ሌሎችን አገልጋዮች ደግሞ ላከ። ገበሬዎቹ በእነርሱም ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው። በመጨረሻም የወይኑ አትክልት ጌታ ‘ልጄንስ ያከብሩታል!’ በማለት ልጁን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ ‘ይህማ ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለውና ርስቱን እኛ እንውረስ!’ ተባባሉ። ልጁንም ይዘው ከወይን አትክልቱ ቦታ ውጪ ወሰዱና ገደሉት። “ታዲያ፥ የወይኑ አትክልት ባለቤት በመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” እነርሱም “የእነዚህን ክፉ ሰዎች ፍጻሜ የከፋ ያደርገዋል። የወይኑንም ተክል ቦታ ፍሬውን በየጊዜው ለሚሰጡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “በቅዱሳት መጻሕፍት ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ ዋና የማእዘን ራስ ሆነ፤ ይህም የጌታ ሥራ ነው፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’ ተብሎ የተጻፈውን ከቶ አላነበባችሁምን? “ስለዚህ እንዲህ እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬ ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች። [ በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበት ሰው ግን ይጨፈለቃል።”] የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን እነዚህን ምሳሌዎች በሰሙ ጊዜ ኢየሱስ የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን ተገነዘቡ። ስለዚህ ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያየው ስለ ነበር ፈሩ።
ማቴዎስ 21:1-46 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወደ ኢየሩሳሌምም በቀረቡ ጊዜ ወደ ደብረዘይት ወደ ቤተ ፋጌ መጡ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤ እንዲህም አላቸው “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ በዚያን ጊዜ የታሰረች አህያ ከነውርንጫዋ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ። ማንም ምንም ቢላችሁ ‘ጌታ ይፈልጋቸዋል’ በሉ፤ ወዲያውም ይልካቸዋል።” ይህም በነቢዩ እንዲህ የብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፦ “ለጽዮን ልጅ “እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፥ በሉአት።” ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ። አህያይቱንና ውርንጫዋን አመጡለት፤ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠባቸው። እጅግ ብዙ ሕዝብም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፍ እየቆረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። ከፊቱ ይሄዱ የነበሩትና ይከተሉት የነበሩት ሕዝብ “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ! በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው! ሆሣዕና በአርያም!” እያሉ ይጮኹ ነበር። ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ “ይህ ማን ነው?” ብሎ መላው ከተማ ተናወጠ። ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው” አሉ። ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ ለዋጮችንም ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን ወንበሮች ገለበጠ፤ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው። በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ መጡ፤ እርሱም ፈወሳቸው። ነገር ግን ሊቃነ ካህናትና ጻፎች ያደረገውን ድንቅ ነገርና በመቅደስም “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ!” እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቆጡ፤ “እነዚህ የሚሉትን ትሰማለህን?” አሉት። ኢየሱስም “አዎን እሰማለሁ፤ ‘ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁምን?” አላቸው። ትቶአቸውም ከከተማ ወጥቶ ወደ ቢታንያ ሄደ፤ በዚያም አደረ። በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ራበው። በመንገድ ዳር የበለስ ዛፍ አይቶ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን ከቅጠል በስተቀር ምንም አላገኘባትም፤ “እንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ፍሬ አይገኝብሽ” አላት። የበለስዋ ዛፍም ወዲያውኑ ደረቀች። ደቀ መዛሙርቱም ይህንን አይተው በመደነቅ “የበለስዋ ዛፍ ወዲያውኑ እንዴት ደረቀች?” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “እውነት እላችኋለሁ፤ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ፥ በበለሲቱ ዛፍ እንደተደረገው ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት ይሆናል፤ አምናችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ትቀበላላችሁ።” ወደ መቅደስ ገብቶ በማስተማር ላይ ሳለ ሊቃነ ካህናትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ መጥተው “እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “እኔም ደግሞ አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተ ከነገራችሁኝ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፤ የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነበር? ከሰማይ ወይስ ከሰዎች?” እርስ በርሳቸው እንዲህ ሲሉ ተነጋገሩ “‘ከሰማይ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ ‘ከሰዎች’ ነው ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያዩት ሕዝቡን እንፈራለን” አሉ። ለኢየሱስም “አናውቅም” ብለው መለሱለት። እርሱም “እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን ነገሮች እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው። “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ መጀመሪያውም ሄዶ ‘ልጄ ሆይ! ዛሬ ወደ ወይኔ አትክልት ሥፍራ ሂድና ሥራ’ አለው። እርሱም ‘አልሄድም’ አለ፤ ቆይቶ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ሄዶ እንዲሁ አለው እርሱም ‘እሺ ጌታዬ’ ብሎ መለሰለት፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነርሱም “የመጀመሪያው” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው “እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ዘማውያን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል። ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ ወደ እናንተ መጥቶ ነበር፥ አላመናችሁትም፤ ቀራጮችና ዘማውያን ግን አመኑት፤ በመጨረሻም ይህንን አይታችሁ እንኳ ልታምኑት ንስሐ አልገባችሁም። “ሌላም ምሳሌ ስሙ፤ የወይን አትክልት የተከለ አንድ የእርሻ ባለቤት ነበረ፤ እርሱም ቅጥር ቀጠረለት፤ መጭመቂያም ማሰለት፤ ግንብም ሠራለት፤ እርሻውንም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። የሚያፈራበት ወራት በደረሰ ጊዜ፥ ፍሬውን እንዲቀበሉለት ባርያዎቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። ገበሬዎቹም ባርያዎቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ አንዱን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት። እርሱም ከፊተኞቹ የሚበዙ ሌሎች ባርያዎችን ላከ፤ እነርሱንም እንዲሁ አደረጉባቸው። በመጨረሻም ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ ብሎ ልጁን ላከባቸው። ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩት ጊዜ እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፤ እንግደለውና ርስቱን እንውረስ’ ተባባሉ። ይዘውም ከወይኑ አትክልት ሥፍራ አውጥተው ገደሉት። እንግዲህ የወይኑ አትክልት ሥፍራ ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” እነርሱም “ክፉዎችን በክፉ ሁኔታ ያጠፋቸዋል፤ የወይኑንም አትክልት ሥፍራ ፍሬውን በየጊዜው ለሚሰጡት ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል” አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው “‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፤ ለዐይኖቻችንም ድንቅ ነው፤’ የሚለውን ከቶ በመጽሕፍት አላነበባችሁምን? ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ተወስዳ ፍሬዋን ለሚያፈራ ሕዝብ ትሰጣለች። በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል፤ ድንጋዩ በላዩ ላይ የሚወድቅበትን ሁሉ ግን ያደቅቀዋል።” ሊቃነ ካህናትና ፈሪሳውያን ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አወቁ። ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያዩት ስለ ነበር ፈሩ።