ማቴዎስ 20:8-16

ማቴዎስ 20:8-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን ‘ሠራተኞችን ጥራና ከኋለኞች ጀምረህ እስከ ፊተኞች ድረስ ደመወዝ ስጣቸው፤’ አለው። በአሥራ አንደኛው ሰዓትም የገቡ መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ፊተኞችም በመጡ ጊዜ አብዝተው የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ተቀብለውም ‘እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፤ የቀኑንም ድካምና ትኩሳት ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው፤’ ብለው በባለቤቱ ላይ አንጕኦራጕኦሩ። እርሱ ግን መልሶ ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው ‘ወዳጄ ሆይ! አልበደልሁህም በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን? ድርሻህን ውሰድና ሂድ፤ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ፤ በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንሁ ዐይንህ ምቀኛ ናትን? እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።’ ”

ማቴዎስ 20:8-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ባለቤት የሠራተኞቹን ተቈጣጣሪ፣ ‘ኋላ ከመጡት ጀምረህ መጀመሪያ እስከመጡት ድረስ ያሉትን ሠራተኞች በሙሉ ጥራና ደመወዛቸውን ክፈላቸው’ አለው። “በዐሥራ አንደኛው ሰዓት ገደማ የተቀጠሩት ሠራተኞች ቀርበው፣ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ዲናር ተቀበሉ። በመጀመሪያ የተቀጠሩት ሲቀርቡ ብልጫ ያለው ክፍያ የሚያገኙ መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም አንዳንድ ዲናር ተከፈላቸው። ክፍያውን ሲቀበሉ በባለቤቱ ላይ በማጕረምረም፣ ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት አንድ ሰዓት ብቻ ሲሠሩ፣ ቀኑን ሙሉ በሥራ ስንደክምና በፀሓይ ስንንቃቃ ከዋልነው ጋራ እንዴት እኩል ትከፍለናለህ?’ አሉት። “እርሱም አንደኛውን ሠራተኛ እንዲህ አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ በደል አላደረስሁብህም፤ በአንድ ዲናር ለመሥራት ከእኔ ጋራ ተስማምተህ አልነበረምን? በል ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያህል በመጨረሻ ለመጣውም ሰው መስጠት እፈልጋለሁ። ታዲያ በራሴ ገንዘብ የፈለግሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ ቸር በመሆኔ ምቀኛነት ያዘህን?’ “ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።”

ማቴዎስ 20:8-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን፦ ሠራተኞችን ጥራና ከኋለኞች ጀምረህ እስከ ፊተኞች ድረስ ደመወዝ ስጣቸው አለው። በአሥራ አንደኛው ሰዓትም የገቡ መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ፊተኞችም በመጡ ጊዜ አብዝተው የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ተቀብለውም፦ እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፥ የቀኑንም ድካምና ትኩሳት ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው ብለው በባለቤቱ ላይ አንጕኦራጕኦሩ። እርሱ ግን መልሶ ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ወዳጄ ሆይ፥ አልበደልሁህም በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን? ድርሻህን ውሰድና ሂድ፤ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ፤ በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንሁ ዓይንህ ምቀኛ ናትን? እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።

ማቴዎስ 20:8-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ባለቤት የሥራ ኀላፊውን ‘ሠራተኞቹን ጥራና በመጨረሻ ከተቀጠሩት ጀምረህ በፊት እስከ ተቀጠሩት ድረስ የሥራ ዋጋቸውን ክፈላቸው’ አለው። ስለዚህ በዐሥራ አንድ ሰዓት የተቀጠሩት ቀርበው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። በፊት የተቀጠሩት በቀረቡ ጊዜ ይበልጥ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። ገንዘቡን ተቀበሉና በወይኑ አትክልት ባለቤት ላይ እንዲህ እያሉ አጒረመረሙ፤ ‘እነዚህ በመጨረሻ መጥተው የሠሩት ለአንድ ሰዓት ብቻ ነው፤ ነገር ግን ቀኑን ሙሉ በፀሐይ ሙቀት እየተቃጠልን በሥራ ስንደክም ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግሃቸው።’ የወይኑ አትክልት ባለቤትም ከሠራተኞቹ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ወዳጄ ሆይ! ምንም አልበደልኩህም፤ የተዋዋልነው በቀን አንድ ዲናር ልከፍልህ አይደለምን? ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁትን ያኽል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈቀድኩ። በገዛ ገንዘቤ የፈለግኹትን ማድረግ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ ለጋሥ ስለ ሆንኩ አንተ ትመቀኛለህ?’ ” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ “እንዲሁም ኋለኞች የሆኑ ፊተኞች ፊተኞች የሆኑትም ኋለኞች ይሆናሉ፤” አለ።

ማቴዎስ 20:8-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ ሹሙን ‘ሠራተኞቹን ጥራና ኋላ ከመጡት ጀምረህ መጀመሪያ እስከመጡት ድረስ ደመወዝ ስጣቸው፤’ አለው። ዐሥራ አንድ ሰዓት ላይ የገቡት መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። መጀመሪያ የመጡትም በቀረቡ ጊዜ የበለጠ የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ። በተቀበሉም ጊዜ በባለቤቱ ላይ አጉረመረሙ። እንዲህም አሉት ‘እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፤ የቀኑን ድካምና ሐሩር ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው።’ እርሱ ግን ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ ሲል መለሰለት ‘ወዳጄ ሆይ! አልበደልሁህም፤ ከእኔ ጋር በአንድ ዲናር አልተስማማህምን? የአንተ የሆነውን ውሰድና ሂድ፤ ለአንተ የሰጠሁህን ያህል ለዚህ ለኋለኛውም ልሰጠው ፈለግሁ። የራሴ በሆነ ነገር ላይ የወደድሁትን ማድረግ አልችልምን? ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንኩ ትመቀኛለህን? ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።’”