ማቴዎስ 2:7-14

ማቴዎስ 2:7-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ። ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ “ሂዱ፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ” አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሄደ፤ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።

ማቴዎስ 2:7-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም ሄሮድስ ጠቢባኑን በምስጢር አስጠርቶ በማነጋገር ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ተረዳ። ጠቢባኑንም ወደ ቤተ ልሔም ልኮ፣ “ሂዱና ሕፃኑን ፈልጉ፤ እኔም ደግሞ ሄጄ እንድሰግድለት፣ እንዳገኛችሁት ወደ እኔ ተመልሳችሁ የት እንዳለ ንገሩኝ” አላቸው። ጠቢባኑ ንጉሡ ያለውን ከሰሙ በኋላ ጕዟቸውን ቀጠሉ። ይህም በምሥራቅ ያዩት ኮከብ እየመራቸው ሕፃኑ እስካለበት ድረስ ወሰዳቸው። ኮከቡንም ሲያዩ ከመጠን በላይ ተደሰቱ። ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋራ አዩ፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ሣጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤም አቀረቡለት። እግዚአብሔርም ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ መንገድ አሳብረው ወደ አገራቸው ተመለሱ። ጠቢባኑ ከሄዱ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሥ! የምትመለስበትን ጊዜ እስካስታውቅህ ድረስ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ በመሸሽ በዚያ ቈይ፤ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻልና” አለው። ስለዚህም ዮሴፍ ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሄደ፤

ማቴዎስ 2:7-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፥ ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ፦ ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ፦ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ፦ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።

ማቴዎስ 2:7-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ሄሮድስ እነዚያን የከዋክብት ተመራማሪዎች በስውር አስጠርቶ፥ ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ጠይቆ ተረዳ፤ እንዲህ ብሎም ወደ ቤተልሔም ላካቸው፦ “ሂዱና፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ፥ እኔም ሄጄ እንድሰግድለት መጥታችሁ ንገሩኝ።” እነርሱም የንጉሡን ቃል ከሰሙ በኋላ፥ ወጥተው ሄዱ፤ እነሆ! በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ በነበረበት ቦታ ላይ እስኪቆም ድረስ፥ እፊት እፊታቸው እየሄደ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ እጅግ በጣም ደስ አላቸው፤ ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር ሆኖ አዩት፤ ተደፍተውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው የወርቅ፥ የዕጣንና የከርቤ ስጦታ አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ እግዚአብሔር በሕልም ስላስጠነቀቃቸው፥ ተመራማሪዎቹ በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ተመልሰው ሄዱ። የከዋክብት ተመራማሪዎቹ ከሄዱ በኋላ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፥ “ሄሮድስ ሕፃኑን ለመግደል ስለሚፈልገው፥ ተነሥና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ቈይ” አለው። ስለዚህ ዮሴፍም በሌሊት ተነሣና፥ ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዞ፥ ወደ ግብጽ ሄደ።

ማቴዎስ 2:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ ተረዳ። እንዲህ ብሎም ወደ ቤተልሔም ላካቸው፦ “ሂዱ፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ” አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ከሰሙ በኋላ ሄዱ፤ እነሆ፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ እጅግ በጣም ደስ አላቸው። ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅ፥ ዕጣንና ከርቤ አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ስላስጠነቀቃቸው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱ ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልጋልና ተነሥ፥ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሄደ፤