ማቴዎስ 2:19-23
ማቴዎስ 2:19-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ “የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለ። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ። በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤ በነቢያት “ናዝራዊ ይባላል” የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
ማቴዎስ 2:19-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው። ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።
ማቴዎስ 2:19-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ፦ የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለ። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ። በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤ በነቢያት፦ ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
ማቴዎስ 2:19-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦለት፥ “ሕፃኑን ለመግደል የሚፈልጉት ሰዎች ስለ ሞቱ፥ ተነሥና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዘህ፥ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለው። ዮሴፍም ተነሣና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዞ፥ ወደ እስራኤል አገር ተመለሰ። ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ምትክ በይሁዳ ምድር ላይ መንገሡን በሰማ ጊዜ፥ ዮሴፍ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ሆኖም በሕልም መመሪያ ስለ ተሰጠው፥ ወደ ገሊላ ምድር ሄደ። “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ በነቢያት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
ማቴዎስ 2:19-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሄሮድስ ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለው፦ “ተነሣ፤የሕፃኑን ነፍስ የሚፈልጉት ሞተዋልና ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ሂድ።” እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ። አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ፈንታ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልም ተገልጦለት ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ በነቢያት “ናዝራዊ ይባላል” የተባለው እንዲፈጸም፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።