ማቴዎስ 2:1-23
ማቴዎስ 2:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፤ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤ የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም “ ‘አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና’ ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው” አሉት። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ። ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ “ሂዱ፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ” አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብጽ ሄደ፤ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ያን ጊዜ እንዲህ ሲል በነቢዩ በኤርምያስ የተነገረው ተፈጸመ፤ “ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ መጽናናትም አልወደደችም፤ የሉምና።” ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ “የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለ። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ። በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤ በነቢያት “ናዝራዊ ይባላል” የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
ማቴዎስ 2:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን፣ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ይሁዳ ከተወለደ በኋላ፣ ጠቢባን ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? በምሥራቅ ኮከቡን አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና” ሲሉ ጠየቁ። ንጉሡ ሄሮድስ ይህን በሰማ ጊዜ ታወከ፤ እንዲሁም መላዪቱ ኢየሩሳሌም ዐብራ ታወከች። እርሱም የካህናት አለቆችንና የአይሁድ ሃይማኖት መምህራንን በሙሉ ሰብስቦ፣ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “በይሁዳ ቤተ ልሔም፤ ነቢዩ እንዲህ ብሎ ጽፏልና አሉ፤ “ ‘በይሁዳ ምድር የምትገኚው አንቺ ቤተ ልሔም፣ ከሌሎቹ ከይሁዳ ገዦች በምንም አታንሺም፤ የሕዝቤ የእስራኤል ጠባቂ የሚሆን፣ ከአንቺ ይወጣልና።’ ” ከዚያም ሄሮድስ ጠቢባኑን በምስጢር አስጠርቶ በማነጋገር ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ተረዳ። ጠቢባኑንም ወደ ቤተ ልሔም ልኮ፣ “ሂዱና ሕፃኑን ፈልጉ፤ እኔም ደግሞ ሄጄ እንድሰግድለት፣ እንዳገኛችሁት ወደ እኔ ተመልሳችሁ የት እንዳለ ንገሩኝ” አላቸው። ጠቢባኑ ንጉሡ ያለውን ከሰሙ በኋላ ጕዟቸውን ቀጠሉ። ይህም በምሥራቅ ያዩት ኮከብ እየመራቸው ሕፃኑ እስካለበት ድረስ ወሰዳቸው። ኮከቡንም ሲያዩ ከመጠን በላይ ተደሰቱ። ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋራ አዩ፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት። ሣጥኖቻቸውን ከፍተው ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤም አቀረቡለት። እግዚአብሔርም ወደ ሄሮድስ እንዳይመለሱ በሕልም ባስጠነቀቃቸው መሠረት፣ መንገድ አሳብረው ወደ አገራቸው ተመለሱ። ጠቢባኑ ከሄዱ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሥ! የምትመለስበትን ጊዜ እስካስታውቅህ ድረስ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ በመሸሽ በዚያ ቈይ፤ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይሻልና” አለው። ስለዚህም ዮሴፍ ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሄደ፤ በዚያም ሄሮድስ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ኖረ። በዚህም፣ “ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት” በማለት ጌታ በነቢዩ አንደበት የተናገረው ቃል ተፈጸመ። ሄሮድስ ጠቢባኑ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ በጣም ተናደደ። ከጠቢባኑ በተነገረው መሠረት፣ ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን የቤተ ልሔምንና የአካባቢዋን መንደሮች ወንድ ልጆች ሁሉ ልኮ አስገደለ። በዚህም በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “የልቅሶና የታላቅ ዋይታ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆቿ አለቀሰች፤ መጽናናትም እንቢ አለች፤ ልጆቿ ዐልቀዋልና።” ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፣ “ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ተመለስ፤ ሕፃኑን ለመግደል የሚሹት ሞተዋልና” አለው። ዮሴፍም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በመያዝ ወደ እስራኤል ምድር ተመለሰ፤ ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ቦታ በይሁዳ መንገሡን በሰማ ጊዜ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ጌታ በሕልም ስላስጠነቀቀው፣ ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ ናዝሬት ወደምትባል ከተማም ሄዶ መኖር ጀመረ። በዚህም በነቢያት፣ “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ።
ማቴዎስ 2:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል፦ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤ የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም፦ አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፥ ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ፦ ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው። ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ፦ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ፦ ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትም አልወደደችም፥ የሉምና የተባለው ተፈጸመ። ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ፦ የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለ። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ። በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤ በነቢያት፦ ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
ማቴዎስ 2:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን፥ በይሁዳ ምድር በምትገኝ በቤተልሔም ከተማ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ፥ የከዋክብት ተመራማሪዎች ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እንዲህም እያሉ ጠየቁ፦ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ለእርሱ ልንሰግድለት መጥተናል።” ንጉሡ ሄሮድስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ደነገጠ፤ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደነገጡ። የካህናት አለቆችን ሁሉና የሕዝቡን የሕግ መምህራን ሰብስቦ መሲሕ የሚወለደው ወዴት እንደ ሆነ ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “በነቢይ እንዲህ የሚል ትንቢት ስለ ተጻፈ፥ መሲሕ የሚወለደው በይሁዳ ምድር፥ በቤተልሔም ከተማ ነው፤ ‘በይሁዳ ክፍለ ሀገር የምትገኚ አንቺ ቤተልሔም ሆይ! ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መሪ ከአንቺ ስለሚወጣ፥ ከይሁዳ ታላላቅ ከተሞች በምንም አታንሺም።’ ” ከዚህ በኋላ ሄሮድስ እነዚያን የከዋክብት ተመራማሪዎች በስውር አስጠርቶ፥ ኮከቡ የታየበትን ትክክለኛ ጊዜ ጠይቆ ተረዳ፤ እንዲህ ብሎም ወደ ቤተልሔም ላካቸው፦ “ሂዱና፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ፥ እኔም ሄጄ እንድሰግድለት መጥታችሁ ንገሩኝ።” እነርሱም የንጉሡን ቃል ከሰሙ በኋላ፥ ወጥተው ሄዱ፤ እነሆ! በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ በነበረበት ቦታ ላይ እስኪቆም ድረስ፥ እፊት እፊታቸው እየሄደ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ እጅግ በጣም ደስ አላቸው፤ ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር ሆኖ አዩት፤ ተደፍተውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው የወርቅ፥ የዕጣንና የከርቤ ስጦታ አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ እግዚአብሔር በሕልም ስላስጠነቀቃቸው፥ ተመራማሪዎቹ በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ተመልሰው ሄዱ። የከዋክብት ተመራማሪዎቹ ከሄዱ በኋላ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ፥ “ሄሮድስ ሕፃኑን ለመግደል ስለሚፈልገው፥ ተነሥና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ቈይ” አለው። ስለዚህ ዮሴፍም በሌሊት ተነሣና፥ ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዞ፥ ወደ ግብጽ ሄደ። እዚያም ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ ቈየ፤ ይህም የሆነው ጌታ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” ያለው ቃል እንዲፈጸም ነው። ከዚያ በኋላ ሄሮድስ፥ የከዋክብት ተመራማሪዎቹ እንዳታለሉት በተገነዘበ ጊዜ፥ በጣም ተቈጣ፤ ወደ ቤተልሔምና በዙሪያዋም ወዳሉት መንደሮች ሁሉ ወታደሮቹን ልኮ፥ ከከዋክብት ተመራማሪዎቹ በተረዳው ዘመን መሠረት፥ ዕድሜአቸው ሁለት ዓመት የሆናቸውንና ከዚያ በታች የሆኑትን በቤተልሔምና በአካባቢው የነበሩትን ወንዶች ሕፃናትን አስገደለ። በዚያን ጊዜ፥ በነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ሲል የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፦ “ራሔል ለልጆችዋ ስታለቅስ፥ የዋይታና፥ የመራራ ለቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ልጆችዋም በሕይወት ስለሌሉ ለመጽናናት እምቢ አለች።” ሄሮድስ ከሞተ በኋላ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦለት፥ “ሕፃኑን ለመግደል የሚፈልጉት ሰዎች ስለ ሞቱ፥ ተነሥና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዘህ፥ ወደ እስራኤል አገር ሂድ” አለው። ዮሴፍም ተነሣና ሕፃኑን ከእናቱ ጋር ይዞ፥ ወደ እስራኤል አገር ተመለሰ። ነገር ግን አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ምትክ በይሁዳ ምድር ላይ መንገሡን በሰማ ጊዜ፥ ዮሴፍ ወደዚያ መሄድ ፈራ። ሆኖም በሕልም መመሪያ ስለ ተሰጠው፥ ወደ ገሊላ ምድር ሄደ። “ናዝራዊ ይባላል” ተብሎ በነቢያት የተነገረው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
ማቴዎስ 2:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፥ እንዲህም አሉ፦ “የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና።” ንጉሡ ሄሮድስ ሰምቶ ታወከ፤ መላዋ ኢየሩሳሌምም ከእርሱ ጋር ታወከች፤ ሊቃነ ካህናትንና የሕዝቡን ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት፦ በይሁዳ ቤተልሔም ነው፤ በነቢዩ እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና፤ “በይሁዳ ምድር የምትገኚ አንቺ ቤተልሔም፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መሪ ከአንቺ ይወጣልና።” ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ ተረዳ። እንዲህ ብሎም ወደ ቤተልሔም ላካቸው፦ “ሂዱ፤ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ” አላቸው። እነርሱም ንጉሡን ከሰሙ በኋላ ሄዱ፤ እነሆ፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር። ኮከቡንም ባዩ ጊዜ እጅግ በጣም ደስ አላቸው። ወደ ቤትም በገቡ ጊዜ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፤ ወድቀውም ሰገዱለት፤ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅ፥ ዕጣንና ከርቤ አቀረቡለት። ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ስላስጠነቀቃቸው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ። እነርሱ ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ “ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልጋልና ተነሥ፥ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ፤ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ” አለው። እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብጽ ሄደ፤ ሄሮድስ እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ፥ ይህም ከጌታ ዘንድ በነቢይ “ልጄን ከግብጽ ጠራሁት” የተባለው እንዲፈጸም ነው። ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ እንዳታለሉት በተረዳ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፥ ወታደሮችን ልኮ ከሰብአ ሰገል በተረዳው ዘመን መሠረት፥ ሁለት ዓመትና ከዚያም በታች የሆኑትን በቤተ ልሔምና በአካባቢዋ የነበሩትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ። ያንጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ እንዲህ ሲል የተነገረው ተፈጸመ፤ “የልቅሶና የብዙ ዋይታ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና መጽናናትን እምቢ አለች።” ሄሮድስ ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብጽ ለዮሴፍ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለው፦ “ተነሣ፤የሕፃኑን ነፍስ የሚፈልጉት ሞተዋልና ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ምድር ሂድ።” እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ ወደ እስራኤል ምድር ገባ። አርኬላዎስ በአባቱ በሄሮድስ ፈንታ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልም ተገልጦለት ወደ ገሊላ አውራጃ ሄደ፤ በነቢያት “ናዝራዊ ይባላል” የተባለው እንዲፈጸም፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።