ማቴዎስ 19:1-12
ማቴዎስ 19:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢየሱስም ይህን ነገር ከፈጸመ በኋላ፥ ከገሊላ ሄዶ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ መጣ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፤ በዚያም ፈወሳቸው። ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት “ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን?” አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ አለም ‘ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤’ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።” እነርሱም “እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ?” አሉት። እርሱም “ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል፤” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “የባልና የሚስት ሥርዐት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም፤” አሉት። እርሱ ግን “ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፤ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው አላቸው።”
ማቴዎስ 19:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢየሱስ ይህን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ገሊላን ትቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ በዚያም ፈወሳቸው። ፈሪሳውያንም ሊፈትኑት ቀርበው፣ “አንድ ሰው በማንኛውም ምክንያት ሚስቱን እንዲፈታ ተፈቅዷልን?” ሲሉ ጠየቁት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? እንዲህም አለ፤ ‘ስለዚህ፣ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋራ ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።” እነርሱም፣ “ታዲያ፣ ሙሴ አንድ ወንድ የፍችውን ጽሕፈት ሰጥቶ ሚስቱን እንዲያሰናብት ለምን አዘዘ?” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ የልባችሁን ጥንካሬ አይቶ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ ፈቀደላችሁ እንጂ ከመጀመሪያው እንዲህ አልነበረም፤ እላችኋለሁ፤ ዝሙት ፈጽማ እስካልተገኘች ድረስ፣ ሚስቱን ፈትቶ ሌላ ሴት የሚያገባ ሁሉ አመንዝራ ይሆናል፤ እርሷንም አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም ሴት የሚያገባ ያመነዝራል።” ደቀ መዛሙርቱም፣ “የባልና የሚስት ጕዳይ እንዲህ ከሆነ አለማግባት ይሻላል” አሉት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፤ “ከተሰጣቸው በቀር ይህን ትምህርት ማንም ሊቀበል አይችልም፤ ምክንያቱም አንዳንዶች ጃንደረባ ሆነው ይወለዳሉ፤ ሌሎች በሰው እጅ ተሰልበው ጃንደረባ ይሆናሉ፤ ደግሞም ለመንግሥተ ሰማይ ሲሉ ራሳቸውን ጃንደረባ የሚያደርጉ አሉ። ይህን መቀበል የሚችል ይቀበል።”
ማቴዎስ 19:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢየሱስም ይህን ነገር ከፈጸመ በኋላ፥ ከገሊላ ሄዶ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ መጣ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ በዚያም ፈወሳቸው። ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት፦ ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ፦ ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም፦ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። እነርሱም፦ እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት። እርሱም፦ ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፦ የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት። እርሱ ግን፦ ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው አላቸው።
ማቴዎስ 19:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ይህን ተናግሮ ካበቃ በኋላ ከገሊላ ተነሥቶ፥ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ወደምትገኝ ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፤ ከእነርሱም የታመሙትን እዚያ ፈወሳቸው። በዚያን ጊዜ ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀረቡና ሊፈትኑት ፈልገው፥ “ሰው ሚስቱን በማንኛውም ምክንያት እንዲፈታ ይፈቀድለታልን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እግዚአብሔር በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? ደግሞም ‘በዚህ ምክንያት ሰው አባቱንና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይዋሓዳል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ’ ስለዚህ እነርሱ ከእንግዲህ ወዲህ አንድ አካል ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። እንግዲህ እግዚአብሔር አጣምሮ አንድ ያደረገውን ሰው አይለየው።” ፈሪሳውያንም “ታዲያ፥ ሙሴ ስለምን ‘ባል ለሚስቱ የፍችዋን የምስክር ወረቀት ሰጥቶ ይፍታት’ ይላል?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፦ “ሙሴማ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ የፈቀደላችሁ ልባችሁ ደንድኖ አስቸጋሪዎች በመሆናችሁ ምክንያት ነው፤ በመጀመሪያ ግን እንዲህ አልነበረም። “እኔ ግን፥ ‘አንድ ሰው በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በቀር ሚስቱን ፈቶ ሌላ ሴት ቢያገባ አመነዘረ’ እላችኋለሁ።” ደቀ መዛሙርቱም “የባልና የሚስት ሁኔታ እንዲህ ከሆነ አለማግባት የተሻለ ነው” አሉት። ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ልዩ ችሎታ ለተሰጣቸው ነው እንጂ ይህ ነገር ለሁሉም አይሆንም። ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፤ ሰው የሰለባቸውም አሉ፤ ለመንግሥተ ሰማይ ሲሉ ራሳቸውን እንደ ስልብ ያደረጉ አሉ፤ ስለዚህ ይህን ሊቀበል የሚችል ይቀበለው።”
ማቴዎስ 19:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ፥ ከገሊላ ወጥቶ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ ወደ ይሁዳ አውራጃ መጣ። ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፤ እርሱም እዚያ ፈወሳቸው። ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሊፈትኑት ፈልገው “ሰው በማንኛውም ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት እንዳደረጋቸው አላነበባችሁምን? ዓለም ‘በዚህ ምክንያት ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።” እነርሱም “ታዲያ ሙሴ ለምን የፍቺ ወረቀት ሰጥቶ እንዲፈታት አዘዘ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው “ሙሴ ሚስቶቻችሁን እንድትፈቱ የፈቀደላችሁ በልባችሁ ጥንካሬ ምክንያት ነው፤ ከመጀመሪያው ግን እንዲህ አልነበረም። እኔ ግን እላችኋለሁ በዝሙት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን ፈትቶ ሌላ የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።” ደቀ መዛሙርቱም “የባልና የሚስት ግንኙነት እንዲህ ከሆነስ መጋባት ጥሩ አይደለም” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው “ይህ ንግግር የተሰጠው ካልሆነ በስተቀር ሁሉም አይቀበለውም፤ ከእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፤ ሰው የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፤ ለመንግሥተ ሰማያት ሲሉ ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው።”