ማቴዎስ 17:22-27

ማቴዎስ 17:22-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ እነርሱ ይገድሉታል፤ ነገር ግን በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣል።” ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር እጅግ አዘኑ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም በደረሱ ጊዜ የቤተ መቅደስ ግብር ተቀባዮች ወደ ጴጥሮስ ቀረቡና፥ “መምህራችሁ የቤተ መቅደስ ግብር አይከፍልምን?” ሲሉ ጠየቁት። ጴጥሮስም “ኧረ ይከፍላል” አላቸው። ጴጥሮስ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ “ስምዖን ጴጥሮስ ሆይ! ምን ይመስልሃል? የዚህ ዓለም መንግሥታት ቀረጥና ግብር የሚቀበሉት ከማን ነው? ከልጆቻቸው ነውን ወይስ ከውጪ አገር ሰዎች?” ሲል ጠየቀው። ጴጥሮስም “ከውጪ አገር ሰዎች ነው” ሲል መለሰ። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እንግዲያውስ ልጆቻቸው ግብር ከመክፈል ነጻ ናቸው ማለት ነዋ? ነገር ግን ለእነርሱ እንቅፋት እንዳንሆንባቸው ወደ ባሕር ሂድና መንጠቆ ጣል፤ በመጀመሪያ የሚወጣውን ዓሣ ያዝ፤ አፉንም ስትከፍት በውስጡ ገንዘብ ታገኛለህ፤ ያንንም ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ክፈል።”