ማቴዎስ 14:6-12
ማቴዎስ 14:6-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች፤ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። እርስዋም በእናትዋ ተመክራ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ፤” አለችው። ንጉሡም አዘነ፤ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት፤ አዘዘ፤ ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው። ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፤ ወደ እናትዋም ወሰደችው። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፤ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት።
ማቴዎስ 14:6-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሄሮድስ የልደቱን ቀን ሲያከብር፣ የሄሮድያዳ ልጅ በዘፈን ደስ ስላሠኘችው፣ የምትጠይቀውን ሁሉ ሊሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። ልጅቷም በእናቷ ተመክራ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በሳሕን ላይ አድርገህ አሁኑኑ ስጠኝ” አለችው። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ዐዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከርሱ ጋራ ስለ ነበሩ እንግዶች ሲል ጥያቄዋ እንዲፈጸምላት አዘዘ። ልኮም በወህኒ ውስጥ እንዳለ የዮሐንስን ራስ አስቈረጠ። የተቈረጠውም ራስ በሳሕን ላይ ተደርጎ ለብላቴናዪቱ ተሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም አስከሬኑን ወስደው ቀበሩት፤ ከዚያም ሄደው ለኢየሱስ ነገሩት።
ማቴዎስ 14:6-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። እርስዋም በእናትዋ ተመክራ፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው። ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ፤ ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው። ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፥ ወደ እናትዋም ወሰደችው። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፥ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት።
ማቴዎስ 14:6-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የሄሮድስ ልደት በሚከበርበት ቀን የሄሮድያዳ ልጅ መጥታ በተጋባዦች መካከል እየጨፈረች ሄሮድስን አስደሰተች። ስለዚህም ሄሮድስ፦ “የምትፈልጊውን ነገር ጠይቂኝ! እኔም እሰጥሻለሁ!” ሲል በመሐላ ቃል ገባላት። እርስዋም በእናቷ ተመክራ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በሳሕን አሁኑኑ ስጠኝ!” አለችው። ንጉሡ በዚህ ነገር አዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር በማእድ ተቀምጠው ስለ ነበሩት ሰዎች ይሉኝታ ብሎ የዮሐንስ ራስ እንዲሰጣት አዘዘ። ስለዚህ ወደ ወህኒ ቤት ሰው ልኮ የዮሐንስን ራስ በወህኒ ቤት አስቈረጠ። የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን አምጥተው ለልጅቱ ሰጡአት፤ እርስዋም ለእናትዋ ወስዳ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት፤ ሄደውም ይህን ነገር ለኢየሱስ ነገሩት።
ማቴዎስ 14:6-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን ሄሮድስ የልደት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ጨፈረች፥ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ የምትለምነውን ሁሉ እንደሚሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። እርሷም በእናትዋ ተመክራ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ ሳሕን አሁን ስጠኝ” አለችው። ንጉሡም አዘነ፤ ነገር ግን ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ስለ ነበሩት ሰዎች ሲል እንዲሰጡአት አዘዘ፤ ልኮም የዮሐንስን ራስ በእስር ቤት አስቆረጠው። ራሱን በሳሕን መጥቶ ለልጅቱ ተሰጣት፤ እርሷም ወደ እናትዋ ወሰደችው። ደቀ መዛሙርቱም መጥተው በድኑን ወሰደው ቀበሩት፤ መጥተውም ለኢየሱስ ነገሩት።