ማቴዎስ 14:1-9

ማቴዎስ 14:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚያን ጊዜ የገሊላ ክፍለ ሀገር ገዢ የነበረው ሄሮድስ፥ የኢየሱስን ዝና ሰማ። አገልጋዮቹን፥ “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤ እነዚህ ድንቅ ነገሮች በእርሱ አማካይነት የሚደረጉት ስለዚህ ነው” አላቸው። ሄሮድስ ዮሐንስን አስይዞ በወህኒ ቤት አሳስሮት ነበር፤ ይህንንም ያደረገው የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት በነበረችው በሄሮዲያዳ ምክንያት ነው። ዮሐንስ ለሄሮድስ፦ “የወንድምህን ሚስት እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም!” ብሎት ነበር። ስለዚህ ሄሮድስ ዮሐንስን ሊገድለው ይፈልግ ነበር፤ ነገር ግን የአይሁድ ሕዝብ እንደ ነቢይ ያዩት ስለ ነበር ሕዝቡን ፈራ። የሄሮድስ ልደት በሚከበርበት ቀን የሄሮድያዳ ልጅ መጥታ በተጋባዦች መካከል እየጨፈረች ሄሮድስን አስደሰተች። ስለዚህም ሄሮድስ፦ “የምትፈልጊውን ነገር ጠይቂኝ! እኔም እሰጥሻለሁ!” ሲል በመሐላ ቃል ገባላት። እርስዋም በእናቷ ተመክራ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በሳሕን አሁኑኑ ስጠኝ!” አለችው። ንጉሡ በዚህ ነገር አዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር በማእድ ተቀምጠው ስለ ነበሩት ሰዎች ይሉኝታ ብሎ የዮሐንስ ራስ እንዲሰጣት አዘዘ።