ማቴዎስ 14:1-36

ማቴዎስ 14:1-36 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፤ ለሎሌዎቹም “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፤ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል፤” አለ። ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና፤ ዮሐንስ “እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም፤” ይለው ነበርና። ሊገድለውም ወዶ ሳለ፥ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ አዩት ፈራቸው። ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች፤ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። እርስዋም በእናትዋ ተመክራ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ፤” አለችው። ንጉሡም አዘነ፤ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት፤ አዘዘ፤ ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው። ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፤ ወደ እናትዋም ወሰደችው። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፤ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት። ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት። ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው፤ ድውዮቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው “ቦታው ምድረ በዳ ነው፤ አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት፤” አሉት። ኢየሱስም “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም፤” አላቸው። እነርሱም “ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም፤” አሉት። እርሱም “እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ፤” አላቸው። ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር። ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ። ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር። ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ “ምትሐት ነው” ብለው ታወኩ፤ በፍርሃትም ጮኹ። ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና “አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤” አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንህ በውሃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ፤” አለው። እርሱም፦ ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውሃው ላይ ሄደ። ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፤ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ “ጌታ ሆይ! አድነኝ፤” ብሎ ጮኸ። ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ፤ ስለምን ተጠራጠርህ?” አለው። ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ። በታንኳይቱም የነበሩት “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤” ብለው ሰገዱለት። ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ። የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፤ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።

ማቴዎስ 14:1-36 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚያ ጊዜ የአራተኛው ክፍል ገዥ የነበረው፣ ሄሮድስ ስለ ኢየሱስ ሰማ፤ ብላቴኖቹንም፣ “እንዲህ ከሆነ መጥምቁ ዮሐንስ ከሞት ተነሥቶ መጥቷል ማለት ነው፤ ይህ ሁሉ ድንቅ ታምራት በርሱ የሚደረገውም ለዚህ ነው” አላቸው። ቀደም ሲል ሄሮድስ፣ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ ወህኒ አስገብቶት ነበር። ምክንያቱም ዮሐንስ፣ “እርሷን እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም” ይለው ነበር። ሄሮድስም ዮሐንስን ሊገድለው ፈልጎ ነበር፤ ሕዝቡ ግን እንደ ነቢይ ይመለከተው ስለ ነበር ፈራ። ሄሮድስ የልደቱን ቀን ሲያከብር፣ የሄሮድያዳ ልጅ በዘፈን ደስ ስላሠኘችው፣ የምትጠይቀውን ሁሉ ሊሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። ልጅቷም በእናቷ ተመክራ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በሳሕን ላይ አድርገህ አሁኑኑ ስጠኝ” አለችው። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ዐዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከርሱ ጋራ ስለ ነበሩ እንግዶች ሲል ጥያቄዋ እንዲፈጸምላት አዘዘ። ልኮም በወህኒ ውስጥ እንዳለ የዮሐንስን ራስ አስቈረጠ። የተቈረጠውም ራስ በሳሕን ላይ ተደርጎ ለብላቴናዪቱ ተሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም አስከሬኑን ወስደው ቀበሩት፤ ከዚያም ሄደው ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስ የሆነውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ከነበረበት ተነሥቶ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄደ። ሕዝቡም ይህን ሰምተው፣ ከየከተማው በእግር ተከተሉት። ኢየሱስም ከጀልባው ሲወርድ ብዙ ሕዝብ አይቶ ራራላቸው፤ ሕመምተኞቻቸውንም ፈወሰላቸው። ሊመሽ ሲል ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ይህ ስፍራ ምንም የማይገኝበት ምድረ በዳ ነው፤ ጊዜው እየመሸ ስለ ሆነ፣ ወደ መንደሮች ሄደው የሚበሉት ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት” አሉት። ኢየሱስ ግን፣ “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ የሚበሉትን እናንተ ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “በዚህ ያለን ዐምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው” አሉት። እርሱም፣ “እስኪ ያለውን ወደ እኔ አምጡት” አላቸው። ከዚያም ሕዝቡ በሣሩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ ዐምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ዐይኑን ወደ ሰማይ በማቅናት አመስግኖና ባርኮ እንጀራውን ቈረሰ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሰጠ፤ እነርሱም ለሕዝቡ ሰጡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ የተረፈውን ቍርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። የበሉትም ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ፣ ዐምስት ሺሕ ወንዶች ያህሉ ነበር። ወዲያውኑ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ተሳፍረው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት አዘዛቸውና እርሱ ሕዝቡን ለማሰናበት ወደ ኋላ ቀረት አለ። ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላም ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ፤ በጨለመም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር፤ በዚያ ጊዜ ጀልባዋ ከምድር ብዙ ምዕራፍ ርቃ እየተጓዘች ሳለች ነፋስ ተነሥቶ በማዕበል ትንገላታ ጀመር። ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕሩ ላይ እየተራመደ እነርሱ ወዳሉበት መጣ። ደቀ መዛሙርቱም በባሕሩ ላይ ሲራመድ ባዩት ጊዜ ፈሩ፤ እነርሱም፣ “ምትሀት ነው!” በማለት በፍርሀት ጮኹ። ኢየሱስም ወዲያውኑ፣ “አይዟችሁ፤ እኔ ነኝ አትፍሩ” አላቸው። ጴጥሮስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ከሆንህስ፣ በውሃው ላይ እየተራመድሁ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው። እርሱም፣ “ና” አለው። ጴጥሮስም፣ ከጀልባው ወርዶ በውሃው ላይ እየተራመደ ወደ ኢየሱስ አመራ። ነገር ግን የነፋሱን ኀይል ባየ ጊዜ ፈራ፤ መስጠምም ሲጀምር፣ “ጌታ ሆይ፤ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፣ “አንተ እምነት የጐደለህ፤ ለምን ተጠራጠርህ?” አለው። ኢየሱስና ጴጥሮስ ጀልባው ላይ እንደ ወጡ ነፋሱ ጸጥ አለ። ከዚያም በጀልባው ውስጥ የነበሩት፣ “በእውነት አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት። በተሻገሩም ጊዜ፣ ወደ ጌንሴሬጥ ምድር ደረሱ። ነዋሪዎቹም ኢየሱስ መሆኑን ባወቁ ጊዜ፣ በዙሪያው ወዳለ አካባቢ ሁሉ መልእክት ላኩ፤ የታመሙትን ሁሉ ወደ እርሱ በማምጣት፣ በሽተኞቹ የልብሱን ጫፍ ብቻ ይነኩ ዘንድ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ የነኩትም ሁሉ ተፈወሱ።

ማቴዎስ 14:1-36 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፥ ለሎሌዎቹም፦ ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፥ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ። ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና፤ ዮሐንስ፦ እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም ይለው ነበርና። ሊገድለውም ወዶ ሳለ፥ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ አዩት ፈራቸው። ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት። እርስዋም በእናትዋ ተመክራ፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው። ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ፤ ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው። ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፥ ወደ እናትዋም ወሰደችው። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፥ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት። ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት። ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፦ ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት። ኢየሱስም፦ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም አላቸው። እነርሱም፦ ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም አሉት። እርሱም፦ እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ አላቸው። ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፥ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር። ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ። ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር። ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ፦ ምትሐት ነው ብለው ታወኩ በፍርሃትም ጮኹ። ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና፦ አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው። ጴጥሮስም መልሶ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ አለው። እርሱም፦ ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ። ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ። ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፦ አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው። ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ። በታንኳይቱም የነበሩት፦ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት። ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ። የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፥ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።

ማቴዎስ 14:1-36 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚያን ጊዜ የገሊላ ክፍለ ሀገር ገዢ የነበረው ሄሮድስ፥ የኢየሱስን ዝና ሰማ። አገልጋዮቹን፥ “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤ እነዚህ ድንቅ ነገሮች በእርሱ አማካይነት የሚደረጉት ስለዚህ ነው” አላቸው። ሄሮድስ ዮሐንስን አስይዞ በወህኒ ቤት አሳስሮት ነበር፤ ይህንንም ያደረገው የወንድሙ የፊልጶስ ሚስት በነበረችው በሄሮዲያዳ ምክንያት ነው። ዮሐንስ ለሄሮድስ፦ “የወንድምህን ሚስት እንድታገባ ሕግ አይፈቅድልህም!” ብሎት ነበር። ስለዚህ ሄሮድስ ዮሐንስን ሊገድለው ይፈልግ ነበር፤ ነገር ግን የአይሁድ ሕዝብ እንደ ነቢይ ያዩት ስለ ነበር ሕዝቡን ፈራ። የሄሮድስ ልደት በሚከበርበት ቀን የሄሮድያዳ ልጅ መጥታ በተጋባዦች መካከል እየጨፈረች ሄሮድስን አስደሰተች። ስለዚህም ሄሮድስ፦ “የምትፈልጊውን ነገር ጠይቂኝ! እኔም እሰጥሻለሁ!” ሲል በመሐላ ቃል ገባላት። እርስዋም በእናቷ ተመክራ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በሳሕን አሁኑኑ ስጠኝ!” አለችው። ንጉሡ በዚህ ነገር አዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር በማእድ ተቀምጠው ስለ ነበሩት ሰዎች ይሉኝታ ብሎ የዮሐንስ ራስ እንዲሰጣት አዘዘ። ስለዚህ ወደ ወህኒ ቤት ሰው ልኮ የዮሐንስን ራስ በወህኒ ቤት አስቈረጠ። የተቈረጠውንም ራስ በሳሕን አምጥተው ለልጅቱ ሰጡአት፤ እርስዋም ለእናትዋ ወስዳ ሰጠች። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም መጡና በድኑን ወስደው ቀበሩት፤ ሄደውም ይህን ነገር ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስ የዮሐንስን መሞት በሰማ ጊዜ በጀልባ ተሳፈረና ወደ አንድ ገለልተኛ ቦታ ብቻውን ለመሆን ሄደ። ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ከየከተማው እየወጡ በእግር ተከተሉት። ኢየሱስ ከጀልባው በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብን አይቶ ራራላቸው፤ በሽተኞቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፥ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቶአል፤ ስለዚህ ሕዝቡ በአቅራቢያ ወዳሉት መንደሮች ሄደው ምግባቸውን እንዲገዙ አሰናብታቸው” አሉት። ኢየሱስ ግን፦ “እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ እነርሱ እንዲሁ ሊሄዱ አይገባም!” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም “እኛ እዚህ ያለን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ነው” አሉት። ኢየሱስም “እነርሱኑ ወደ እኔ አምጡልኝ!” አላቸው። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ በመስኩ ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አንሥቶ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና የምስጋና ጸሎት አደረገ፤ እንጀራውንም ቈርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ዐደሉ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውን ፍርፋሪ፥ ደቀ መዛሙርቱ በዐሥራ ሁለት መሶብ ሞልተው አነሡ። የበሉትም ሰዎች ከሴቶችና ከሕፃናት ሌላ አምስት ሺህ ያኽል ወንዶች ነበሩ። ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፥ “እኔ ሕዝቡን እስካሰናብት ድረስ በጀልባ ተሳፈሩና ቀድማችሁኝ ወደ ማዶ ተሻገሩ፤” ሲል አዘዛቸው። ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ አንድ ተራራ ላይ ወጣ፤ በመሸም ጊዜ ኢየሱስ እዚያ ብቻውን ነበር። በዚያን ጊዜ ጀልባዋ በባሕሩ መካከል ሆና ከምትሄድበት አቅጣጫ በተቃራኒ በሚነፍሰው ነፋስ እየተመታች ማዕበሉ ወዲያና ወዲህ ያንገላታት ነበር። ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ። ደቀ መዛሙርቱም በባሕሩ ላይ እየተራመደ ሲሄድ ባዩት ጊዜ በጣም ፈርተው ደነገጡ፤ “ይህ ምትሐት ነው!” ብለውም በፍርሃት ጮኹ። ኢየሱስም ወዲያውኑ “አይዞአችሁ! እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ፥ “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንክ በባሕሩ ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ!” አለው። ኢየሱስም “ና!” አለው። ስለዚህ ጴጥሮስ ከጀልባው ወርዶ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ በባሕሩ ላይ ተራመደ። ነገር ግን የነፋሱን ኀይል አይቶ ፈራ፤ ወደ ባሕሩ ውስጥ መስጠም በጀመረ ጊዜ “ጌታ ሆይ! አድነኝ!” ሲል ጮኸ። ኢየሱስ ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘውና፦ “አንተ እምነት የጐደለህ! ስለምን ተጠራጠርክ?” አለው። ኢየሱስና ጴጥሮስ ወደ ጀልባው በገቡ ጊዜ ነፋሱ ጸጥ አለ። በጀልባውም ውስጥ የነበሩት ሁሉ “በእርግጥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” ብለው ለኢየሱስ ሰገዱለት። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ባሕሩን ተሻግረው ወደ ጌንሳሬጥ ምድር ደረሱ። በዚያም አገር የነበሩ ሰዎች ኢየሱስ መሆኑን ባወቁ ጊዜ በአካባቢው ወዳሉት ስፍራዎች ተላልከው በሽተኞችን ወደ እርሱ አስመጡ። በሽተኞቹም የልብሱን ጫፍ ብቻ እንዲነኩ ለመኑት። የነኩትም ሁሉ ከበሽታቸው ተፈወሱ።

ማቴዎስ 14:1-36 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዢ የነበረው ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፤ አገልጋዮቹንም “ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሞት ተነሥቶአል፤ ኃይል በእርሱ የሚደረገውም ለዚህ ነው፤” አለ። ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮትና እስር ቤት አስገብቶት ነበርና፤ ዮሐንስ “እርሷ ለአንተ ትሆን ዘንድ ተገቢ አይደለም” ይለው ነበርና። ሊገድለው ይፈልግ ነበር፥ ነገር ግን ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያዩት ስለ ነበር ፈራቸው። ነገር ግን ሄሮድስ የልደት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ጨፈረች፥ ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ የምትለምነውን ሁሉ እንደሚሰጣት በመሐላ ቃል ገባላት። እርሷም በእናትዋ ተመክራ “የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ ሳሕን አሁን ስጠኝ” አለችው። ንጉሡም አዘነ፤ ነገር ግን ስለ መሐላውና ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ስለ ነበሩት ሰዎች ሲል እንዲሰጡአት አዘዘ፤ ልኮም የዮሐንስን ራስ በእስር ቤት አስቆረጠው። ራሱን በሳሕን መጥቶ ለልጅቱ ተሰጣት፤ እርሷም ወደ እናትዋ ወሰደችው። ደቀ መዛሙርቱም መጥተው በድኑን ወሰደው ቀበሩት፤ መጥተውም ለኢየሱስ ነገሩት። ኢየሱስም ይህን በሰማ ጊዜ ብቻውን ገለል ወዳለ ቦታ በታንኳ ከዚያ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከየከተማው በእግር ተከተሉት። በወረደም ጊዜ ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው፤ በሽተኞቻቸውንም ፈወሰ። በመሸም ጊዜ ደቀመዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው “ቦታው ምድረ በዳ ነው፤ ሰዓቱም አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብታቸው” አሉት። ኢየሱስም “መሄድ አያስፈልጋቸውም፤ እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው” አላቸው። እነርሱም “ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ ምንም የለንም” አሉት። እርሱም “እነዚያን ወደዚህ ወደ እኔ አምጡልኝ” አላቸው። ሕዝቡን በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፤ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ ሰጡ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ። የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች ውጪ አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ። ወዲያውም ሕዝቡን እስኪያሰናብት ድረስ ደቀመዛሙርቱ ወደ ጀልባ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው። ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያው ነበር። በዚህ ጊዜ ጀልባዋ ከምድር በጣም ርቃ ሳለች፥ ነፋስ በተቃራኒው አቅጣጫ ነበርና በማዕበል ትንገላታ ጀመር። ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ወደ እነርሱ መጣ። ደቀመዛሙርቱ በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ “ምትሐት ነው” ብለው ደነገጡ፤ ከፍርሃትም የተነሣ ጮኹ። ወዲያው ኢየሱስ ተናገራቸው፥ “አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤” አላቸው። ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! አንተስ ከሆንህ በውሃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” ሲል መለሰለት። እርሱም “ና” አለው። ጴጥሮስም ከጀልባዋ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ለመሄድ በውሃው ላይ ተራመደ። ነገር ግን የነፋሱን ብርታት አይቶ ፈራ፤ መስጠም በጀመረም ጊዜ “ጌታ ሆይ! አድነኝ” ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም ወዲያው እጁን ዘርግቶ ያዘውና “አንተ እምነት የጎደለህ፥ ለምን ተጠራጠርህ?” አለው። ወደ ጀልባዋ በወጡ ጊዜ ነፋሱ ፀጥ አለ። በጀልባዋ የነበሩትም “በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብለው ሰገዱለት። ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ። የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፤ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ የልብሱን ጫፍ ብቻ ለመንካት ለመኑት፤ የነኩትም ሁሉ ተፈወሱ።