ማቴዎስ 13:10-16

ማቴዎስ 13:10-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይጨመርለታል፤ ይትረፈረፍለታልም፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤ “እያዩ፣ አያዩም፤ እየሰሙ፣ አይሰሙም ወይም አያስተውሉም፤ እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤ “ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም። የሕዝቡ ልብ ደንድኗልና፤ ጆሯቸውም አይሰማም፤ እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው፣ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’ የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን ብፁዓን ናቸው።

ማቴዎስ 13:10-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ስለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ሰው የበለጠ ይሰጠዋል፤ ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። እያዩ እንደማያዩ፥ እየሰሙ እንደማይሰሙ ወይም እንደማያስተውሉ ስለ ሆኑ እነሆ፥ እኔ በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። ስለዚህ በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በእነርሱ ላይ ይፈጸማል፦ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አታደርጉም። የእዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸው ተደፍኖአል፤ ዐይናቸውም ተጨፍነዋል፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ፥ በዐይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸውም ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኳቸው ነበር።’ “የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባረኩ ናቸው።