ማቴዎስ 13:1-52

ማቴዎስ 13:1-52 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤ እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር። በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው “እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾህም ወጣና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።” ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። ‘መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፤ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። በዐይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዐይናቸውንም ጨፍነዋል፤’ የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም። “እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፤ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፤ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል።” ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። የባለቤቱም ባሮች ቀርበው ‘ጌታ ሆይ! መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ?’ አሉት። እርሱም ‘ጠላት ይህን አደረገ፤’ አላቸው። ባሮቹም ‘እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን?’ አሉት። እርሱ ግን ‘እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን “እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ፤” እላለሁ’ አለ።” ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፤ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።” ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም “በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ፤” የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም። በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን፤” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው “መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፤ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፤ አጫጆችም መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፤ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፤ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ። “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት። “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዐይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፤ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ፤ ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኀጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፤ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ኢየሱስም “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው፤ “አዎን” አሉት። እርሱም “ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል፤” አላቸው።

ማቴዎስ 13:1-52 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚያ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም ስለ ከበበው በባሕሩ ዳር ትቷቸው ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ። ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱም ዘር በቂ ዐፈር በሌለበት በድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ፈጥኖ በቀለ፤ ነገር ግን ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ባለመስደዱም ደረቀ። ሌላው ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን ዐንቆ አስቀረው፤ ሌላውም ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይጨመርለታል፤ ይትረፈረፍለታልም፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤ “እያዩ፣ አያዩም፤ እየሰሙ፣ አይሰሙም ወይም አያስተውሉም፤ እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤ “ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም። የሕዝቡ ልብ ደንድኗልና፤ ጆሯቸውም አይሰማም፤ እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው፣ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’ የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙ ነቢያትና ብዙ ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየትና የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም። “እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል። ይህ እንግዲህ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ነው። በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይመስላል። ነገር ግን ሥር ባለመስደዱ ብዙ አይቈይም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት ሲመጣ ወዲያውኑ ይሰናከላል። በእሾኽ መካከል የተዘራው ዘር ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራን ሰው ይመስላል። በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።” ኢየሱስም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች። ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው በቅሎ ማፍራት ሲጀምር እንክርዳዱም ዐብሮ ብቅ አለ። “የዕርሻው ባለቤት ባሪያዎችም ወደ እርሱ ቀርበው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ በዕርሻህ ቦታ ጥሩ ዘር ዘርተህ አልነበረምን? እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። “እርሱም፣ ‘የጠላት ሥራ ነው’ አላቸው። “ባሮቹም፣ ‘እንክርዳዱን ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት። “እርሱ ግን፣ ‘አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም ዐብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ ዐብረው ይደጉ። በዚያ ጊዜ ዐጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ’ አላቸው።” ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ አንድ ሰው ወስዶ በዕርሻው ቦታ የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች። የሰናፍጭ ዘር ከሌሎች ሁሉ ያነሰች ብትሆንም፣ ስታድግ ግን ከአትክልት ሁሉ በልጣ፣ የሰማይ ወፎች መጥተው በቅርንጫፎቿ ላይ እስኪያርፉ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።” አሁንም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ በመደባለቅ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” ኢየሱስ ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። በዚህም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ።” ከዚያም ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፣ “በዕርሻው ውስጥ ስላለው እንክርዳድ የተናገርኸውን ምሳሌ ትርጕም ንገረን” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ጥሩውን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ ዕርሻውም ይህ ዓለም ነው፤ ጥሩው ዘር የእግዚአብሔርን መንግሥት ልጆች ያመለክታል፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፤ ዘርቶት የሄደው ጠላትም ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ሲሆን፣ ዐጫጆቹም መላእክት ናቸው። “እንክርዳዱ ተነቅሎ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም ለኀጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ የሚያደርጉትን ሁሉ ለቅመው ከመንግሥቱ ያወጣሉ። ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል። በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሓይ ያበራሉ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ። “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻ ውስጥ የተደበቀ ሀብት ትመስላለች፤ አንድ ሰው ባገኛት ጊዜ መልሶ ሸሸጋት፤ ከመደሰቱም የተነሣ፣ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ ያን የዕርሻ ቦታ ገዛ። “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ውብ ዕንቍ የሚፈልግ ነጋዴ ትመስላለች፤ እጅግ ውድ የሆነ ዕንቍ ባገኘም ጊዜ፣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ገዛው። “ደግሞም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር ተጥሎ የዓሣ ዐይነቶችን የያዘ መረብ ትመስላለች፤ ዓሣ አጥማጆቹ መረቡ ሲሞላላቸው ጐትተው ወደ ባሕሩ ዳር አወጡት፤ ከዚያም ተቀምጠው ጥሩ ጥሩውን እየለዩ በቅርጫት ውስጥ ጨመሩ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ጣሉት። በዓለም መጨረሻም ልክ እንደዚሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኀጢአተኞችን ከጻድቃን በመለየት፣ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል።” ኢየሱስ፣ “ይህ ሁሉ ገብቷችኋል?” አላቸው። እነርሱም፣ “አዎን” አሉት። እርሱም፣ “ስለዚህም የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር የተረዳ ማንኛውም የኦሪት ሕግ መምህር፣ ከከበረ ሀብቱ ክምችት አዲሱንም አሮጌውንም የሚያወጣ ባለንብረት ይመስላል” አላቸው።

ማቴዎስ 13:1-52 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤ እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር። በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው፦ እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፥ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፥ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም። እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፥ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። የባለቤቱም ባሮች ቀርበው፦ ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት። እርሱም፦ ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም፦ እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት። እርሱ ግን፦ እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን፦ እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፥ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች። ሌላ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች። ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም፦ በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም። በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፦ የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ደግሞ መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፥ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ። ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት። ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፥ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ኢየሱስም፦ ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን? አላቸው፤ አዎን አሉት። እርሱም፦ ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል አላቸው።

ማቴዎስ 13:1-52 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው በመሰብሰባቸው በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ፥ በባሕር ዳር ቆመው ነበር። ከዚያም በኋላ ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ እያለ ይነግራቸው ጀመር፦ “እነሆ! አንድ ገበሬ ለመዝራት ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላው ዘር ብዙ ዐፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ብዙ ዐፈር ስለሌለበት ጥልቀት አልነበረውም፤ ስለዚህ ዘሩ ወዲያውኑ በቀለ። ይሁን እንጂ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። ሌላውም ዘር በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል ወደቀ፤ እሾኻማውም ቊጥቋጦ አደገና የዘሩን ቡቃያ አንቆ አስቀረው። ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለና ብዙ ፍሬ አፈራ፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ስለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ሰው የበለጠ ይሰጠዋል፤ ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። እያዩ እንደማያዩ፥ እየሰሙ እንደማይሰሙ ወይም እንደማያስተውሉ ስለ ሆኑ እነሆ፥ እኔ በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። ስለዚህ በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በእነርሱ ላይ ይፈጸማል፦ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አታደርጉም። የእዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸው ተደፍኖአል፤ ዐይናቸውም ተጨፍነዋል፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ፥ በዐይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸውም ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኳቸው ነበር።’ “የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባረኩ ናቸው። በእውነት እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አልሰሙም። “እንግዲህ እናንተ የዘሪው ምሳሌ ምን እንደ ሆነ ስሙ፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ የማያስተውለውን ሰው ነው፤ ወዲያውኑ ሰይጣን መጥቶ በልቡ የተዘራውን ቃል ይወስድበታል፤ በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ነው። ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በልቡ ውስጥ ሥር አልሰደደም፤ ስለዚህ በቃሉ ምክንያት አንዳች ችግር ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ቶሎ ይሰናከላል። በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ለጊዜው የሚሰማውን ሰው ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብና የሀብት ፍቅር ወደ ልቡ ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል። በመልካም መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ በማስተዋል የሚቀበለውን ሰው ነው፤ እርሱ ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱ ሠላሳ ፍሬ ይሰጣል።” እንዲሁም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻው መልካም ዘር የዘራውን ሰው ትመስላለች፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ከተኛ በኋላ ጠላት መጣና በስንዴው ውስጥ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው አድጎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም በዚያኑ ወቅት ታየ። ስለዚህ የእርሻው ባለቤት አገልጋዮች ወደ እርሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፥ በእርሻህ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ፥ እንክርዳዱ ከወዴት መጣ?’ አሉት። እርሱም ‘ይህን ያደረገ ጠላት ነው’ አላቸው። አገልጋዮቹም ‘ታዲያ ሄደን እንክርዳዱን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?’ አሉት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው ‘አይሆንም እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውን አብራችሁ ትነቅላላችሁ። ስለዚህ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ ድረስ ስንዴውም እንክርዳዱም አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜ ዐጫጆችን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳት እንዲቃጠልም በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን ሰብስቡና በጐተራዬ ክተቱ’ እላቸዋለሁ።” ኢየሱስ ሌላ ምሳሌም እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማይ አንድ ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች። እርስዋ ከዘር ሁሉ ያነሰች ናት ባደገች ጊዜ ግን፥ ከአትክልቶች ሁሉ ትበልጣለች፤ ዛፍም ትሆናለች፤ ወፎችም መጥተው በቅርንጫፎችዋ ላይ ጎጆአቸውን ሠርተው ይሰፍሩባታል።” ደግሞም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማይ አንዲት ሴት ወስዳ ከሦስት መስፈሪያ ዱቄት ጋር የለወሰችውን እርሾ ትመስላለች፤ እርሾውም ሊጡን ሁሉ እንዲቦካ አደረገው።” ኢየሱስ ይህን ሁሉ ነገር በምሳሌ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ያለ ምሳሌም ምንም ነገር አልተናገራቸውም። ይህም የሆነበት ምክንያት በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው እንዲፈጸም ነው፦ “ንግግሬን በምሳሌ እገልጣለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውን እናገራለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን አሰናብቶ ወደ ቤት ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፥ “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም አስረዳን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻው ይህ ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ የሰይጣን ልጆች ናቸው። እንክርዳዱን የዘራው ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ነው፤ ዐጫጆቹ መላእክት ናቸው። ልክ እንክርዳዱ ተነቅሎና በየነዶው ታስሮ እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም የኃጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ከእርሱ መንግሥት ሰብስበው ያወጣሉ፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ጻድቃን ግን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻ ውስጥ የተሸሸገውን ሀብት ትመስላለች። አንድ ሰው ይህን ሀብት ባገኘው ጊዜ መልሶ ደበቀው፤ ከደስታውም ብዛት የተነሣ ሄደና ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛ።” እንደገናም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ደግሞ መንግሥተ ሰማይ ጥሩ ዕንቊ ለመግዛት የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ ነጋዴውም እጅግ ክቡር የሆነ ዕንቊ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያንን ዕንቊ ገዛ።” ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “እንዲሁም መንግሥተ ሰማይ ወደ ባሕር የተጣለች መረብን ትመስላለች፤ እርስዋ በየዐይነቱ ዓሣ የምትሰበስብ ናት፤ በሞላች ጊዜ ዓሣ አጥማጆቹ ወደ ባሕሩ ዳር ጐትተው ያወጡአታል፤ ተቀምጠውም መልካም መልካሙን መርጠው በዕቃ ያስቀምጣሉ፤ መጥፎ መጥፎውን ግን ወዲያ ይጥላሉ። በዓለም መጨረሻም እንዲህ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል። ክፉዎችን ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” ደግሞም ኢየሱስ፦ “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው። እነርሱም “አዎን ጌታ ሆይ!” አሉ። እርሱም “እንግዲያውስ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሕግ መምህር፦ ከዕቃ ግምጃ ቤቱ አዲስ የሆነውንና አሮጌ የሆነውን ዕቃ የሚያመጣ የንብረት ባለቤትን ይመስላል” ሲል መለሰላቸው።

ማቴዎስ 13:1-52 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ፥ በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳር ቆመው ነበር። ብዙ ነገርም በምሳሌ ነገራቸው፥ እንዲህም አላቸው “እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። አንዳንዱም ብዙ አፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ነገር ግን ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። አንዳንዱም በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም በቀለና አነቀው። አንዳንዱም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።” ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ለምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለታልም፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ለዚህ ነው በምሳሌ የምነግራቸው ምክንያቱም እያዩ አያዩም፥ እየሰሙም አይሰሙም ወይም አያስተውሉም። እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። መስማትን ትሰማላችሁ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ ነገር ግን አትመለከቱም። በዓይናቸው አይተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ተመልሰው እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፥ ጆሮአቸው ደንቁሮአል፥ ዓይናቸውም ተጨፍኖአል፤ የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባኩ ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው ነበር ነገር ግን አላዩም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው ነበር ነገር ግን አልሰሙም።” እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥቱን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው መጥቶ በልቡ የተዘራውን ይነጥቀዋል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው ደግሞ ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ በራሱ ሥር የለውም፤ ነገር ግን ለትንሽ ጊዜ ይቆያል፥ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራው፥ ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ጭንቀትና የሃብት ማታለል ቃሉን ያንቃል፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ስድሳ አንዱም ሠላሳ ይሰጣል። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም አለ “መንግሥተ ሰማያት በእርሻው ላይ መልካም ዘርን የዘራ ሰውን ትመስላለች። ሰዎቹ ተኝተው ሳለ፥ ጠላት መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው በቅሎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም ያንጊዜ ታየ። የባለቤቱ ባርያዎችም ቀርበው ‘ጌታ ሆይ! በእርሻህ ላይ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። እርሱም ‘ጠላት ይህን አደረገ’ አላቸው። ባርያዎቹም ታዲያ ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው እንክርዳዱን ስትሰበስቡ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ ተዉአቸው፤ በመከር ጊዜ አጫጆቹን “አስቀድማችሁ እንክርዳዱን በእሳትም ለማቃጠል ሰብስባችሁ በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱት፤ እላቸዋለሁ።” ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው፤ እንዲህም ሲል ነገራቸው “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች፤ እርሷ ከዘሮች ሁሉ ያነሰች ናት፤ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአትክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።” ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማያት አንዲት ሴት ወስዳ ሁሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ነገራቸው፤ ያለ ምሳሌም ምንም አልነገራቸውም። ይህም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ፤” በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም ንገረን፤” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የመንግሥቱ ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ ደግሞ የክፉው ልጆች ናቸው፤ የዘራው ጠላት ደግሞ ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፤ አጫጆቹ መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ ከመንግሥቱም እንቅፋቶችን ሁሉና ዓመፃን ይሰበስባሉ፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። “መንግሥተ ሰማያት አንድ ሰው በእርሻ ውስጥ አግኝቶ መልሶ የሸሸገው የተሰወረ መዝገብ ትመስላለች፤ ከደስታውም ብዛት ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጦ ያንን እርሻ ገዛው። “ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ክቡር ዕንቁ የሚፈልግ ነጋዴን ትመስላለች፤ ዋጋዋ እጅግ ውድ የሆነ አንዲት ዕንቁ ባገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት። “ደግሞም መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለችና ከሁሉም ዓይነት ዓሣ የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤ በሞላች ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፤ ተቀምጠውም መልካሞቹን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አስቀመጡ፤ ክፉውን ግን ጣሉት። በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ክፉዎችን ከጻድቃን ይለዩአቸዋል፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያም ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” “ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን?” አላቸው፤ “አዎን” አሉት። እርሱም “ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀመዝሙር የሆነ ጸሐፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል፤” አላቸው።