ማቴዎስ 13:1-23

ማቴዎስ 13:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤ እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር። በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው “እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾህም ወጣና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።” ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። ‘መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፤ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። በዐይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዐይናቸውንም ጨፍነዋል፤’ የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም። “እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፤ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፤ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል።”

ማቴዎስ 13:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በዚያ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ። ብዙ ሕዝብም ስለ ከበበው በባሕሩ ዳር ትቷቸው ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ። ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም ሳለ፣ አንዳንዱ ዘር መንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱም ዘር በቂ ዐፈር በሌለበት በድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ፈጥኖ በቀለ፤ ነገር ግን ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ባለመስደዱም ደረቀ። ሌላው ዘር በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አደገና ቡቃያውን ዐንቆ አስቀረው፤ ሌላውም ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቷችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይጨመርለታል፤ ይትረፈረፍለታልም፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤ “እያዩ፣ አያዩም፤ እየሰሙ፣ አይሰሙም ወይም አያስተውሉም፤ እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤ “ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም። የሕዝቡ ልብ ደንድኗልና፤ ጆሯቸውም አይሰማም፤ እንዳያዩም ዐይናቸውን ጨፍነዋል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው፣ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’ የእናንተ ዐይኖች ስለሚያዩ፣ ጆሮዎቻችሁም ስለሚሰሙ ግን ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፤ ብዙ ነቢያትና ብዙ ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየትና የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ግን አልሆነላቸውም። “እንግዲህ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ ከማያስተውል ከማንኛውም ሰው ልብ ውስጥ ክፉው መጥቶ የተዘራውን ዘር ይነጥቃል። ይህ እንግዲህ በመንገድ ዳር የተዘራው ዘር ነው። በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራው፣ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይመስላል። ነገር ግን ሥር ባለመስደዱ ብዙ አይቈይም፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት ሲመጣ ወዲያውኑ ይሰናከላል። በእሾኽ መካከል የተዘራው ዘር ቃሉን ሰምቶ ለዚህ ዓለም በመጨነቅና በብልጽግና ሐሳብ በመታለል ታንቆ ያላፈራን ሰው ይመስላል። በጥሩ መሬት ላይ የተዘራው ዘር ግን ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውለውን ሰው ይመስላል፤ በርግጥም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።”

ማቴዎስ 13:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤ እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር። በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው፦ እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፥ ወፎችም መጥተው በሉት። ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፥ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው። ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው፦ ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም። በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም። እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፥ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል።

ማቴዎስ 13:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚያኑ ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ መጥተው በመሰብሰባቸው በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ፥ በባሕር ዳር ቆመው ነበር። ከዚያም በኋላ ብዙ ነገሮችን በምሳሌ እንዲህ እያለ ይነግራቸው ጀመር፦ “እነሆ! አንድ ገበሬ ለመዝራት ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ ዘር በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት። ሌላው ዘር ብዙ ዐፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ብዙ ዐፈር ስለሌለበት ጥልቀት አልነበረውም፤ ስለዚህ ዘሩ ወዲያውኑ በቀለ። ይሁን እንጂ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ ሥር ስላልነበረውም ደረቀ። ሌላውም ዘር በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል ወደቀ፤ እሾኻማውም ቊጥቋጦ አደገና የዘሩን ቡቃያ አንቆ አስቀረው። ሌላውም ዘር በመልካም መሬት ላይ ወድቆ በቀለና ብዙ ፍሬ አፈራ፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!” ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ስለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ሰው የበለጠ ይሰጠዋል፤ ይበዛለታልም፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። እያዩ እንደማያዩ፥ እየሰሙ እንደማይሰሙ ወይም እንደማያስተውሉ ስለ ሆኑ እነሆ፥ እኔ በምሳሌ እነግራቸዋለሁ። ስለዚህ በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው በእነርሱ ላይ ይፈጸማል፦ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አታደርጉም። የእዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸው ተደፍኖአል፤ ዐይናቸውም ተጨፍነዋል፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ፥ በዐይናቸው ተመልክተው፥ በጆሮአቸውም ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኳቸው ነበር።’ “የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ፥ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባረኩ ናቸው። በእውነት እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ለማየት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አላዩም፤ እናንተ የምትሰሙትንም ለመስማት ተመኝተው ነበር፤ ነገር ግን አልሰሙም። “እንግዲህ እናንተ የዘሪው ምሳሌ ምን እንደ ሆነ ስሙ፤ በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር የሚያመለክተው፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት ቃል ሰምቶ የማያስተውለውን ሰው ነው፤ ወዲያውኑ ሰይጣን መጥቶ በልቡ የተዘራውን ቃል ይወስድበታል፤ በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ ወዲያውኑ በደስታ የሚቀበለውን ሰው ነው። ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በልቡ ውስጥ ሥር አልሰደደም፤ ስለዚህ በቃሉ ምክንያት አንዳች ችግር ወይም ስደት በደረሰበት ጊዜ ቶሎ ይሰናከላል። በእሾኻማ ቊጥቋጦ መካከል የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ለጊዜው የሚሰማውን ሰው ነው፤ ይሁን እንጂ የዚህ ዓለም ሐሳብና የሀብት ፍቅር ወደ ልቡ ገብቶ ቃሉን ስለሚያንቀው ያለ ፍሬ ይቀራል። በመልካም መሬት ላይ የተዘራው የሚያመለክተው፥ ቃሉን ሰምቶ በማስተዋል የሚቀበለውን ሰው ነው፤ እርሱ ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ሥልሳ፥ አንዱ ሠላሳ ፍሬ ይሰጣል።”

ማቴዎስ 13:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕሩ አጠገብ ተቀመጠ፤ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ስለ ተሰበሰቡ፥ በጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳር ቆመው ነበር። ብዙ ነገርም በምሳሌ ነገራቸው፥ እንዲህም አላቸው “እነሆ ዘሪ ሊዘራ ወጣ። ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው በሉት። አንዳንዱም ብዙ አፈር በሌለበት በጭንጫማ መሬት ላይ ወደቀ፤ መሬቱም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፤ ነገር ግን ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። አንዳንዱም በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም በቀለና አነቀው። አንዳንዱም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።” ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው “ለምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ?” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም። ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለታልም፤ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል። ለዚህ ነው በምሳሌ የምነግራቸው ምክንያቱም እያዩ አያዩም፥ እየሰሙም አይሰሙም ወይም አያስተውሉም። እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። መስማትን ትሰማላችሁ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ ነገር ግን አትመለከቱም። በዓይናቸው አይተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ተመልሰው እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፥ ጆሮአቸው ደንቁሮአል፥ ዓይናቸውም ተጨፍኖአል፤ የእናንተ ግን ዐይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ የተባኩ ናቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው ነበር ነገር ግን አላዩም፤ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው ነበር ነገር ግን አልሰሙም።” እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ። የመንግሥቱን ቃል ሰምቶ የማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው መጥቶ በልቡ የተዘራውን ይነጥቀዋል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው። በጭንጫማ መሬት ላይ የተዘራው ደግሞ ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤ በራሱ ሥር የለውም፤ ነገር ግን ለትንሽ ጊዜ ይቆያል፥ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል። በእሾህ መካከል የተዘራው፥ ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፤ ነገር ግን የዚህ ዓለም ጭንቀትና የሃብት ማታለል ቃሉን ያንቃል፤ የማያፈራም ይሆናል። በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል፤ አንዱ መቶ፥ አንዱ ስድሳ አንዱም ሠላሳ ይሰጣል።