ማቴዎስ 12:15-21 - Compare All Versions
ማቴዎስ 12:15-21 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ኢየሱስ ሐሳባቸውን ዐውቆ ከዚያ ዘወር አለ። እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ ሕመምተኞችን ሁሉ ፈወሰ፤ ማንነቱን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው። ይህም የሆነው በነቢዩ በኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፤ “እነሆ፤ የመረጥሁት፣ የምወድደውና ነፍሴ ደስ የተሠኘችበት ብላቴናዬ፣ መንፈሴን በርሱ ላይ አኖራለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍትሕን ያውጃል። አይጨቃጨቅም ወይም አይጮኽም፤ ድምፁም በአደባባይ አይሰማም። ፍትሕን ለድል እስኪያበቃ ድረስ፣ የተቀጠቀጠውን ሸንበቆ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጧፍ ክር አያጠፋም። አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”
ማቴዎስ 12:15-21 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ኢየሱስ ግን ሤራቸውን ዐውቆ ከዚያ ቦታ ገለል አለ፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ሄዱ፤ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሳቸው። ሰዎቹን ግን ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው። “እነሆ! የመረጥኩት አገልጋዬ ይህ ነው! እርሱ እኔ የምወደውና የምደሰትበት ነው፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አደርጋለሁ፤ እርሱም ቅን ፍርድን ለሕዝቦች ያውጃል። እርሱ አይከራከርም ወይም አይጮኽም፤ በመንገዶችም ላይ ድምፁን የሚሰማ የለም። የተቀጠቀጠ ሸንበቆ እንኳ አይሰብርም፤ የሚጤሰውንም የጥዋፍ ክር አያጠፋም፤ ይህንንም የሚያደርገው፥ ቅን ፍርድ ድል እስኪነሣ ድረስ ነው። አሕዛብ በእርሱ ተስፋ ያደርጋሉ።”
ማቴዎስ 12:15-21 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፤ ሁሉንም ፈወሳቸው፤ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤ በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል “እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም፤ አይጮህምም፤ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”
ማቴዎስ 12:15-21 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤ በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል፦ እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል። አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም። አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።
ማቴዎስ 12:15-21 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ኢየሱስ ይህንን አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው። እንዳያጋልጡትም አዘዛቸው፤ ይህም በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተነገረው እንዲፈጸም ነው፤ “እነሆ የመረጥሁት አገልጋዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፤ ፍርድንም ለአሕዛብ ያውጃል። አይከራከርም አይጮህምም፤ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም። ፍርድን ወደ ድል እስኪያመጣ ድረስ፥ የተቀጠቀጠ ሸምበቆን አይሰብርም፤ የሚጤስን የጧፍ ክር አያጠፋም። አሕዛብ በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።”