ማቴዎስ 11:20-30 - Compare All Versions
ማቴዎስ 11:20-30 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ከዚያም ኢየሱስ ብዙውን ታምራት ያደረገባቸው ከተሞች ንስሓ ባለመግባታቸው እንዲህ ሲል ወቀሳቸው፤ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረገው ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ቅጣቱ ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፤ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ልትዪ ነውን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ታምራት በሰዶም ቢደረግ ኖሮ፣ እስከ ዛሬ በቈየች ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ቅጣቱ ለሰዶም ይቀልላታል።” በዚያ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና። “ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም። “እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”
ማቴዎስ 11:20-30 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ቀጥሎም ኢየሱስ ከሌሎች ከተሞች ይበልጥ ብዙ ተአምራት ያደረገባቸውን ከተሞች፥ ንስሓ ስላልገቡ እንዲህ ሲል ይወቅሳቸው ጀመር፦ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት፥ በጢሮስና በሲዶና ከተሞች ተደርገው ቢሆን ኖሮ በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሐዘን ልብስ ለብሰውና ዐመድ በላያቸው ላይ ነስንሰው ገና ዱሮ ንስሓ በገቡ ነበር! ስለዚህ በፍርድ ቀን፥ ከእናንተ ይልቅ በጢሮስና በሲዶና ይኖሩ ለነበሩት ቅጣቱ ይቀልላቸዋል እላችኋለሁ። አንቺም እስከ ሰማይ ከፍ ያልሽው ቅፍርናሆም! ወደ ሲኦል ትወርጂአለሽ! በአንቺ የተደረጉት ተአምራት፥ በሰዶም ተደርገው ቢሆን ኖሮ ያቺ ከተማ ሳትጠፋ፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበር! ስለዚህ በእውነት እልሻለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ቅጣቱ ይቀልላታል!” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህን ነገር ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለአላዋቂዎች ስለ ገለጥክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎ! አባት ሆይ! ይህን ለማድረግ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኖአል። አባቴ ሁሉን ነገር ሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ ማንም የለም። እንዲሁም ከወልድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም፤ ማንም ወልድ ካልገለጠለት በቀር አብን ሊያውቅ አይችልም። “እናንተ በጉልበት ሥራ የደከማችሁ! ሸክምም የከበደባችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ! እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህና ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ ነው፤ ሸክሜም ቀላል ነው።”
ማቴዎስ 11:20-30 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ “ወዮልሽ ኮራዚ! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ “አባት ሆይ! የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ። አዎን አባት ሆይ! ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም። እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፤ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”
ማቴዎስ 11:20-30 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ፦ ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፦ አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም። እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።
ማቴዎስ 11:20-30 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
በዚያን ጊዜ ብዙ ተአምራት ያደረገባቸውን ከተሞች ንስሓ ስላልገቡ ይነቅፋቸው ጀመር፤ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፥ ማቅ ለብሰው፥ አመድ ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን ኖሮ እስከ ዛሬ በቆየች ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ “የሰማያትና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ። አዎን አባት ሆይ! ይህ በፊትህ በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። ሁሉም ነገር በአባቴ ለእኔ ተሰጥቶአል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅደው በቀር አብን የሚያውቅ የለም። እናንተ ደካሞችና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፥ ከእኔም ተማሩ፤ ምክንያቱም እኔ የዋህ በልብም ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፥ ሸክሜም ቀላል ነውና።”