ማቴዎስ 11:1-30

ማቴዎስ 11:1-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ ጊዜ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ አለፈ። ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው “ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶችም ይሄዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮችም ይሰማሉ፤ ሙታንም ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው።” እነዚያም ሲሄዱ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ “ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ። ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። ‘እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤’ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል። ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ነገር ግን “ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፤ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ ‘እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ፤ ዋይ ዋይም አላላችሁም’ ይሉአቸዋል። ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ እነርሱም ‘ጋኔን አለበት’ አሉት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም ‘እነሆ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች።” በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ “ወዮልሽ ኮራዚ! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ “አባት ሆይ! የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ። አዎን አባት ሆይ! ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም። እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፤ ሸክሜም ቀሊል ነውና።”

ማቴዎስ 11:1-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኢየሱስ ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ትእዛዙን ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ፣ ለማስተማርና ለመስበክ ወደ ገሊላ ከተሞች ሄደ። ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስ በማድረግ ላይ ያለውን ነገር በሰማ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ልኮ፣ “ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀው አንተ ነህ? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀ። ኢየሱስም፣ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፤ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዐይነ ስውራን ያያሉ፤ ዐንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም የምሥራች እየተሰበከ ነው፤ በእኔ የማይሰናከል ሁሉ ምስጉን ነው።” የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ከሄዱ በኋላ፣ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ሸንበቆ በነፋስ ሲወዛወዝ? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ባማረ ልብስ ያጌጠ ሰው? ባማረ ልብስ ያጌጡ በነገሥታት ቤት አሉላችሁ። ታዲያ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ልታዩ? አዎን፣ እላችኋለሁ፤ ከነቢይም የሚበልጠውን ነው። እንዲህ ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ “ ‘መንገድህን በፊትህ የሚያዘጋጅ፣ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ።’ እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥተ ሰማይ በብዙ ትገፋለች፤ የሚያገኟትም ብርቱዎች ናቸው፤ ነቢያትም፣ የሙሴ ሕግም ሁሉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋልና። እንግዲህ ልትቀበሉት ከፈቀዳችሁ ይመጣል የተባለው ኤልያስ እርሱ ነው። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ። “ይህን ትውልድ በምን ልመስለው? በገበያ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እንዲህ እያሉ የሚጣሩ ልጆችን ይመስላሉ፤ “ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ አላለቀሳችሁም’ ዮሐንስ ከመብልና ከመጠጥ ተቈጥቦ በመምጣቱ፣ ‘ጋኔን አለበት’ ይሉታልና። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም፣ ‘በልቶ የማይጠግብ፣ ጠጪ እንዲሁም የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኀጢአተኞች ወዳጅ’ አሉት። ጥበብ ትክክለኛ መሆኗ ግን በሥራዋ ተረጋገጠ።” ከዚያም ኢየሱስ ብዙውን ታምራት ያደረገባቸው ከተሞች ንስሓ ባለመግባታቸው እንዲህ ሲል ወቀሳቸው፤ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረገው ታምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ገና ዱሮ ማቅ ለብሰው፣ ዐመድ ነስንሰው ንስሓ በገቡ ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ቅጣቱ ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፤ ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ልትዪ ነውን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ታምራት በሰዶም ቢደረግ ኖሮ፣ እስከ ዛሬ በቈየች ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ቅጣቱ ለሰዶም ይቀልላታል።” በዚያ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና። “ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም። “እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።”

ማቴዎስ 11:1-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ኢየሱስም አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ ጊዜ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ አለፈ። ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና፦ የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? አለው። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው። እነዚያም ሲሄዱ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ፦ ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ፥ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ። ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን። እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል። ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ፦ እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል። ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እነርሱም፦ ጋኔን አለበት አሉት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እነርሱም፦ እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች። በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ፦ ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ፦ አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና። ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም። እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።

ማቴዎስ 11:1-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ኢየሱስ እነዚህን ትእዛዞች ለዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከሰጠ በኋላ ያን ቦታ ትቶ በአቅራቢያው ወደሚገኙት ከተሞች ሊሰብክና ሊያስተምር ሄደ። መጥምቁ ዮሐንስ በወህኒ ቤት ሳለ፥ የክርስቶስን ሥራ በመሰማቱ ሁለት ደቀ መዛሙርት ልኮ፥ “ያ ይመጣል የተባለው መሲሕ አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ብለው ኢየሱስን እንዲጠይቁት አደረገ። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሂዱና ያያችሁትንና የሰማችሁትን ሁሉ ለዮሐንስ ንገሩት። እነሆ፥ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ቀጥ ብለው ይሄዳሉ፤ ለምጻሞች ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድኾችም ወንጌል ይሰበካል፤ ስለ እኔ የማይጠራጠር የተባረከ ነው።” የዮሐንስ መልእክተኞች ከሄዱ በኋላ፥ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤ “ለመሆኑ ምን ልታዩ ወደ በረሓ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸንበቆ ለማየት ነውን? ደግሞስ ምን ለማየት ወጣችሁ? የተዋበ ልብስ የለበሰውን ሰው ለማየት ነውን? የተዋበ ልብስ የሚለብሱማ በነገሥታት ቤት ይገኛሉ። ታዲያ፥ ስለምን ወጣችሁ? ነቢይ ለማየት ነውን? አዎ፥ እንዲያውም ከነቢይ በጣም የሚበልጠውን ለማየት ነው እላችኋለሁ። እርሱ ‘እነሆ፥ እፊት እፊትህ እየሄደ፥ መንገድህን የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ በፊት እልካለሁ’ ተብሎ የተጻፈለት ነው። በእውነት እላችኋለሁ፤ ሴቶች ከወለዷቸው ሰዎች መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም። ነገር ግን በመንግሥተ ሰማያት በጣም የሚያንሰው ይበልጠዋል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማይ በጣም ትገፋለች በብርቱ የሚታገሉም ያገኙአታል። “መላው የነቢያት ትምህርትና በሙሴ እጅ የተሰጠው ሕግ እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋል። እንግዲህ እነርሱ የተናገሩትን ለመቀበል ከፈቀዳችሁ፥ ያ ይመጣል የተባለው ኤልያስ እነሆ፥ ይህ ዮሐንስ ነው። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ! “ነገር ግን የዚህን ዘመን ሰዎች በምን አነጻጽራቸዋለሁ? በአደባባይ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እየጠሩ፥ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ አልጨፈራችሁም! ሙሾ አወረድንላችሁ አላለቀሳችሁም!’ የሚሉትን ልጆች ይመስላሉ። እንዲሁም መጥምቁ ዮሐንስ በመጣ ጊዜ እህል ሳይበላና የወይን ጠጅ ሳይጠጣ ቢመጣ፥ ‘ይህስ ጋኔን አለበት!’ አሉት፤ የሰው ልጅ ደግሞ እየበላና እየጠጣ ቢመጣ፥ ‘እነሆ! ይህ መብልና መጠጥ የሚወድ ነው! የቀራጮችና የኃጢአተኞችም ወዳጅ ነው!’ አሉት። ሆኖም የጥበብ ትክክለኛነት ግን በሥራዋ ይረጋገጣል።” ቀጥሎም ኢየሱስ ከሌሎች ከተሞች ይበልጥ ብዙ ተአምራት ያደረገባቸውን ከተሞች፥ ንስሓ ስላልገቡ እንዲህ ሲል ይወቅሳቸው ጀመር፦ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ! በእናንተ የተደረጉት ተአምራት፥ በጢሮስና በሲዶና ከተሞች ተደርገው ቢሆን ኖሮ በዚያ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች የሐዘን ልብስ ለብሰውና ዐመድ በላያቸው ላይ ነስንሰው ገና ዱሮ ንስሓ በገቡ ነበር! ስለዚህ በፍርድ ቀን፥ ከእናንተ ይልቅ በጢሮስና በሲዶና ይኖሩ ለነበሩት ቅጣቱ ይቀልላቸዋል እላችኋለሁ። አንቺም እስከ ሰማይ ከፍ ያልሽው ቅፍርናሆም! ወደ ሲኦል ትወርጂአለሽ! በአንቺ የተደረጉት ተአምራት፥ በሰዶም ተደርገው ቢሆን ኖሮ ያቺ ከተማ ሳትጠፋ፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበር! ስለዚህ በእውነት እልሻለሁ፤ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ቅጣቱ ይቀልላታል!” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ! ይህን ነገር ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለአላዋቂዎች ስለ ገለጥክላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎ! አባት ሆይ! ይህን ለማድረግ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኖአል። አባቴ ሁሉን ነገር ሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ ማንም የለም። እንዲሁም ከወልድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም፤ ማንም ወልድ ካልገለጠለት በቀር አብን ሊያውቅ አይችልም። “እናንተ በጉልበት ሥራ የደከማችሁ! ሸክምም የከበደባችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ! እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህና ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ ነው፤ ሸክሜም ቀላል ነው።”

ማቴዎስ 11:1-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ በኋላ፥ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ሄደ። ዮሐንስ በእስር ቤት ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና “የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” አለው። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው “ሄዳችሁ ያያችሁትንና የሰማችሁትን ለዮሐንስ ንገሩት፤ ዕውሮች ያያሉ፤ አንካሶች ይራመዳሉ፤ ለምጻሞችም ይነጻሉ፤ ደንቆሮዎች ይሰማሉ፤ ሙታን ይነሣሉ፤ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔ የማይሰናከል ሁሉ የተባረከ ነው።” እነርሱ ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ “ወደ ምድረ በዳ ምን ልታዩ ወጣችሁ? በነፋስ የሚወዛወዘውን ሸምበቆ? ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ። ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን ነውን? አዎን፥ ከነቢይም የሚበልጠውን እላችኋለሁ። “እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚያዘጋጅ መልእክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤” ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል። ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም በኃይል ይወስዱአታል። ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናግረዋልና፤ ልትቀበሉት ከፈቀዳችሁ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ እርሱ ነው። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። “ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ ተቀምጠው እርስ በእርሳቸው እንዲህ እያሉ የሚጠሩ ልጆችን ይመስላሉ፤ ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ አልጨፈራችሁም፥ ሙሾ አወረድንላችሁ አላለቀሳችሁም’ ይሉአቸዋል። ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ እነርሱም ‘ጋኔን አለበት’ አሉት። የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤ እነርሱም ‘እነሆ በላተኛና ጠጪ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ’ አሉት። ጥበብ በሥራዋ ጸደቀች።” በዚያን ጊዜ ብዙ ተአምራት ያደረገባቸውን ከተሞች ንስሓ ስላልገቡ ይነቅፋቸው ጀመር፤ “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፥ ማቅ ለብሰው፥ አመድ ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል። አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን ኖሮ እስከ ዛሬ በቆየች ነበር። ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ይቀልላታል።” በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ “የሰማያትና የምድር ጌታ አባት ሆይ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ። አዎን አባት ሆይ! ይህ በፊትህ በጎ ፈቃድ ሆኖአልና። ሁሉም ነገር በአባቴ ለእኔ ተሰጥቶአል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅደው በቀር አብን የሚያውቅ የለም። እናንተ ደካሞችና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፥ ከእኔም ተማሩ፤ ምክንያቱም እኔ የዋህ በልብም ትሑት ነኝ፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፥ ሸክሜም ቀላል ነውና።”