ማቴዎስ 1:18-24
ማቴዎስ 1:18-24 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” በነቢይ ከጌታ ዘንድ፥ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤” የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፤ ትርጓሜውም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤” የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤
ማቴዎስ 1:18-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ታሪክ እንዲህ ነው፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳይገናኙ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። ዕጮኛዋ ዮሴፍ ጻድቅ ሰው ስለ ነበርና ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በስውር ሊተዋት ወሰነ። በዚህ ሐሳብ ሳለ፣ የጌታ መልአክ በሕልም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፤ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፤ ዕጮኛህን ማርያምን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ፤ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና። ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና።” ጌታ በነቢዩ እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ፤ “እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ይሉታል፤” ትርጕሙም፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ” ማለት ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቃ፤ ከዚያም የጌታ መልአክ እንዳዘዘው ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት።
ማቴዎስ 1:18-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ። እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፦ የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ፥ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤
ማቴዎስ 1:18-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ሁኔታ እንዲህ ነበር፦ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች፥ ሳይገናኙ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍ ደግ ሰው ስለ ነበረ፥ ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት አልፈለገም፤ ስለዚህ በስውር ሊተዋት አሰበ። ነገር ግን ይህን ነገር ሲያስብ ሳለ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “የዳዊት ዘር ዮሴፍ ሆይ! እጮኛህ ማርያም የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ስለ ሆነ፥ እርስዋን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ። እርስዋ ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ስለሚያድን ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” ይህም ሁሉ የሆነው ጌታ እንዲህ ሲል በነቢይ አማካይነት የተናገረው እንዲፈጸም ነው፤ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙም ‘ዐማኑኤል’ ተብሎ ይጠራል።” ዐማኑኤል ማለትም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው” ማለት ነው። ዮሴፍ ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ፥ የጌታ መልአክ ባዘዘው መሠረት እጮኛውን ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት።
ማቴዎስ 1:18-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት እንዲህ ነበር፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳለች ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች። እጮኛዋ ዮሴፍ ጻድቅ ስለ ነበረ ሊያጋልጣት አልፈለገም፥ በስውርም ሊተዋት አሰበ። እርሱ ይህን ሲያስብ ሳለ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፤ እንዲህም አለው “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ! ከእርሷ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” ይህ ሁሉ የሆነው ጌታ በነቢዩ እንዲህ ሲል የተናገረው እንዲፈጸም ነው፦ “እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤” ትርጉሙም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤” ማለት ነው። ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤